የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደው አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ስድስተኛ ልዩ ስብሰባው ካስተናገዳቸው አጀንዳዎች መካከል አንደኛው የገንዘብ ሚኒስቴርን የ2011 በጀት ዓመት የአስር ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ማዳመጥ ነበር፡፡ በዚህም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የመስሪያ ቤታቸውን የአስር ወራት አፈጻጸም ለምክር ቤቱ አቅርበው አስገምግመዋል። እኛም በዛሬው ኢኮኖሚ አምድ ዝግጅታችን በቦታው ተገኝተን የሚኒስቴሩ የአስር ወራት አፈጻጸም ምን እንደሚመስል በወፍ በረር ልናስቃኛችሁ ወደናል፡፡
ማክሮ ኢኮኖሚው
የገንዘብ ሚኒስቴር ከተጣሉበት ኃላፊነቶች አንዱ በፊስካል ፖሊሲው አማካኝነት የአገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የማረጋጋት ሥራ ነው፡፡ በመሆኑም ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው እንዳቀረቡት ባለፉት አስር ወራትም መንግስት የዘረጋቸውን የልማት ዕቅዶች ለመተግበር የሚያስችል ሀብት በማሰባሰብ፣ የተሰበሰበው ሀብት በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መንገድ ሥራ ላይ እንዲውል የማድረግና አፈጻጸሙን የመከታተል ሥራ ተሰርቷል፡፡
በዚህም የበጀት ጉድለቱን ከማክሮ ኢኮኖሚ ግብ ጋር ለማጣጣም ከአገር ውስጥና ከውጭ በሚገኝ ብድር እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡ በዚህ ረገድ የተረጋጋ የዋጋ ዕድገት እንዲኖር ባለፉት አስር ወራት ውስጥ መንግስት ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከዚህ አኳያ በዋጋ ንረት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ በተደረገው ጥረት የዋጋ ንረቱን በአንድ አሃዝ እንዲገደብ ማድረግ ባይቻልም በዝቅተኛው የሁለት አሃዝ እንዲገደብ ማድረግ ተችሏል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት መኖሩን ከሚጠቁሙ የኢኮኖሚ አመልካቾች አንዱ የውጭ ክፍያ ሚዛን መዛባት መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት አስተማማኝ ምንጭ የሆነው የሸቀጦች የወጪ ንግድ በመቀነሱ ችግሩ መከሰቱን አመላክቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ውስጥ ከሸቀጦች የወጭ ንግድ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡
በዚህ የተነሳም ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ187 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ወይም በ 8 ነጥብ 2 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ከጥራጥሬ፣ ጫትና ጨርቃጨርቅ የተገኘው ገቢ ጭማሪ ከማሳየቱ በስተቀር የወጪ ንግድ አፈጻጸሙ በዋና ዋና ምርቶች ሳይቀር ቅናሽ አሳይቷል፡፡
አበረታች አፈጻጸም
በበጀት ዓመቱ የአስር ወራት አፈጻጸም አበረታች አፈጻጸም ከታየባቸው ዘርፎች መካከል አመርቂ ውጤት ተመዝግቦበታል ተብሎ በቀዳሚነት የተጠቀሰው አገሪቱ ከገጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት አኳያ የውጭ ዕዳ ክፍያ ጫናን ለማቃለልና በቀጣይ ዕዳ የመክፈል አቅምን ለማጠናከር የተሰራው ሥራ ነው፡፡
በዚህ ረገድ በተለይም ከቻይና የፋይናንስ ተቋማት ጋር እጅግ ውስብስብ የሆኑ ድርድሮችን በማድረግ የወለድ መጠን ቅነሳ፣ እፎይታና የመክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ እንዲሁም የዕዳ ሽግሽግ የሚያስገኙ ሥራዎች ተከናውነዋል፡ ፡ ይህም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከቻይና የተወሰዱ የንግድ ብድሮች የክፍያ ጫና በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ የሚያደርግ መሆኑን ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል የውጭ ቀጥታ የበጀት ድጋፍን በተመለከተ ለ2011 በጀት ዓመት የወጪ በጀት መሸፈኛ ከታቀደው ከልማት አጋሮች የሚገኝ ቀጥታ በጀት ድጋፍ 19 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በአስር ወራት ውስጥ 31 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል፡፡ ይህም ለዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር 164 በመቶ የሆነ ከፍተኛ አፈጻጸም አስመዝግቧል፡፡
የአገር ውስጥና የውጭ ብድርን በተመከተ የአገሪቱ የውጭ ብድር መጠን ሃያ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የፌዴራል መንግስት 15 ነጥብ 8 በመቶ፤ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ደግሞ 11 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ አላቸው። በበጀት ዓመቱ በመልሶ ማበደር ስምምነት ለመንግስት ልማት ድርጅቶች ከተሰጡ ብድሮች ውስጥ 243 ነጥብ 84 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በአስር ወራት ውስጥ 432 ነጥብ 78 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህም የዕቅዱን 177 ነጥብ 5 በመቶ ሲሆን ከፍተኛ አፈጻጸም ካሳዩ ዘርፎች መካከል አንደኛው ነው፡፡
በዚህ ረገድ ከልማት አጋሮች ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር በተለይም በሀገሪቱ እየተካሔደ ያለውን ለውጥ እንዲደግፉ በማድረግ በኩል በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በዚህም ባለፉት አስር ወራት ውስጥ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሁሉም የልማት አጋሮች ድጋፍ እየሰጡ ሲሆን ድጋፉ በብዛትና በጥራት እየጨመረ መምጣቱንም ነው የገንዘብ ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡
ለአብነትም የዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የፈረንሳይና ጀርመን መንግስታት በበጀት ድጋፍ መልክ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ አዲስ ድጋፍ ሰጥተዋል። ከተሰጠው ድጋፍ ውስጥም ከፊሉ ቀጥታ ወደ ትሬዠሪ የገባ ሲሆን ቀሪው በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ገቢ እንዲሆን ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ሌሎች አጋሮችም ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን ሂደቱ በድርድር ላይ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ሌሎች የልማት አጋሮች ከዚህ ቀደም በፕሮጀክትና በተናጠል በተንጠባጠበ መልኩ ይሰጡ የነበሩበትን አሰራር በመቀየር ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት የሚቆይ የማዕቀፍ አሰራር እንዲከተሉና ተገማች በሆነ መንገድ ድጋፍ መስጠት የሚችሉበት አሰራር እንዲኖር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
የልማት አጋሮች የሚያደርጉትን ድጋፍ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ድጋፍ የሚያደርጉበት አሰራር በማመቻቸት በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ እያገዙ መሆናቸውን ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡
ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአስር ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ውስጥ ድክመት የታየባቸውና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችም ተለይተው ቀርበዋል። የመንግስት ገቢ አፈጻጸም በተለይም ከታክስ የሚሰበሰበው ገቢ አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመሆኑ ቀዳሚው ነው፡፡ ምክንያቱም በ2011 በጀት ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው የፌዴራል መንግስት መደበኛ ገቢ 235 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ውስጥ በአስር ወራት መሰብሰብ የተቻለው 160 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ አፈጻጸሙም የዕቅዱን 68 በመቶ ነው፡፡
በመሆኑም አፈጻጸሙን ለማሻሻል የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ባለፉት አስር ወራት ውስጥ በርካታ የታክስ ህግ ማሻሻያ ጥናቶች አከናውኗል፡ ፡ በጥናቶቹ ውጤት ላይ በመመስረት ስምንት መመሪያዎችና ሦስት ረቂቅ ህጎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሥራ ላይ ያለው የታክስ ቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት ያስገኘውን ጥቅምና ጉዳት ለመለየት የሚያስችል ጥናት ተካሂዶ አሰራሩን ወጥ ለማድረግ የሚያግዝ የህግ ረቂቅ የተዘጋጀ ሲሆን በማሻሻያዎቹ አማካኝነት በቀጣይ ከሃያ እስከ ሰላሳ ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል፡፡
የዋጋ ግሽበት አሁንም ባለ ሁለት አሃዝ ሆኖ መቀጠሉ ሌላው ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ ሆኗል። የተረጋጋ የዋጋ ዕድገት እንዲኖር ባለፉት አስር ወራት ውስጥ መንግስት ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርግ ቢቆይም የዋጋ ንረቱን በአንድ አሃዝ እንዲገደብ ለማድረግ ባለመቻሉ በአሁኑ ወቅት አገራዊ አጠቃላይ የፍጆታ ዕቃዎች የዋጋ ዕድገት 12 ነጥብ 6 በመቶ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህ ረገድ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገሪቱን ፖለቲካ በማረጋጋትና የፍጆታ አቅርቦትን ለማሳደግ ከግብር እና ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሮች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አቶ አህመድ በሰጡት ምላሽ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም በብድርና እርዳታ የሚሰሩ የትልልቅ ፕሮጀክቶች መጓተት፣ በገቢና ወጪ ፍላጎት መካከል አለመጣጣም መኖሩ፣ ኦዲት የተደረገባቸውና ሂሳባቸው የጎላ ችግር ያለባቸው መስሪያ ቤቶች የእርምት ማስተካከያ አለማድረጋቸው፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በመልሶ ማበደር የወሰዱትን ገንዘብ ክፍያ አለመፈጸምና የውዝፍ ዕዳ እየጨመረ መምጣት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ሆነዋል፡፡
የመፍትሔ አቅጣጫዎች
ከታክስ አሰባሰብና ገቢን ከማሳደግ አኳያ የተጀመረውን የሪፎርም ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የፊስካል ፖሊሲ ዲስፕሊኑን በጠበቀ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ፣ ከፕሮጀክቶች አፈጻጸምና ግምገማ ጋር ተያይዞ ያጋጠመውን የአቅም ክፍተት ለመሙላት የክትትልና ግምገማ ሥርዓቱን ማጠናከር በሪፖርቱ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት የመፍትሔ ሃሳብ ሆነው ተጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ባሻገርም ሂሳባቸው የጎላ ችግር ያለባቸው በመሆናቸው ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት የተሰጣቸው መስሪያ ቤቶችን በተመለከተም ለሚመለከተው አካል የቀረበውን ሪፖርት አፈጻጸም በአግባቡ መከታተል እንደሚያስፈልግም ሪፖርቱ የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የታዩትን ክፍተቶች ለመሙላት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራና በተለይም የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት በጥናት የተመሰረተ ዘላቂነት ያለው መፍትሔ እንዲሰጥና እንዲሁም ሂሳባቸው የጎላ የኦዲት ችግር ያለባቸውን መስሪያ ቤቶች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ከምክር ቤቱ አባላትና ከቋሚ ኮሚቴው ጠንከር ያለ ግብረ መልስ ተሰጥቶበታል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2011
ይበል ካሳ