ሆስፒታሉ የፎሬንሲክ ምርመራ አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቀቀ

አዲስ አበባ፡- የአስክሬን (የፎሬንሲክ) እና ስነ-ምረዛ ምርመራ አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሽያላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ። ሆስፒታሉ በቅርቡ የጨረር ሕክምና አገልግሎት ማስጀመሩም ተገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሽያላይዝድ ሆስፒታል እና የሕክምና ኮሌጁ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር አለሙ ጣሚሶ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ ለመጀመሪያ ጊዜ አስክሬን (የፎሬንሲክ) እና ስነ-ምረዛ ምርመራ አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቅቋል።

በአካባቢው ከዚህ ቀደም የፎሬንሲክና ስነ-ምረዛ ምርመራ አለመኖሩንና ምርመራው ከሕግ ጋር የሚገናኝ እንደመሆኑ ከደቡብ ኦሮሚያ፣ ከሲዳማ እና ከደቡብ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ እየተላከ ምርመራ ይደረግ እንደነበር አውስተዋል።

ይህንን ታሳቢ በማድረግም የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በአሁኑ ወቅት የፎሬንሲክ እና ስነ ምረዛ ምርመራ ማዕከል ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሽያላይዝድ ሆስፒታሉ በቅርቡ የጨረር ሕክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህም የኅብረተሰቡን የሕክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ተላላፊ ያልሆኑ በተለይም ስኳር፣ ግፊት እና የካንሰር በሽታዎች እየጨመሩና ኅብረተሰቡን በእጅጉ እየጎዱ መሆኑን ጠቁመው፤ በአካባቢው የጨረር ሕክምና መጀመሩ ከዚህ ቀደም ታካሚዎች አገልግሎቱን ለማግኘት ሲሉ የሚገጥማቸውን እንግልት፡ አላስፈላጊ ወጪ እና የጊዜ ብክነትን ለማስቀረት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።

በተለይ የጨረር ሕክምና አገልግሎት በሀገሪቱ በአዲስ አበባ፣ ሐረር እና ጅማ ሲሰጥ ቆይቷል ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር አለሙ ጣሚሶ፤ ሕክምናው ለታካሚው አንዴ ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን በተደጋጋሚ የሚሰጥ እና ወጪውም ከባድ እንደመሆኑ አንድ ታካሚ እስከ መቶ ሺህ ብር ለሚደርስ ወጪ ይዳረግ እንደነበር ተናግረዋል።

የጨረር ማዕከል ሀዋሳ ላይ መጀመሩም ሕክምናው ከዚህ ቀደም በአካባቢው ባለመኖሩ ምክንያት ታካሚዎች አገልግሎቱ ወደ ሚሰጥባቸው አካባቢዎች በተደጋጋሚ በመመላለስ ይገጥማቸው የነበረውን እንግልትና ወጪ እንደሚቀንስላቸውም ገልጸዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሽያላይዝድ ሆስፒታሉ የጨረር ሕክምና ብቻ ሳይሆን ራሱን የቻለ የካንሰር ማዕከልም አቋቁሟል።

የካንሰር ማዕከሉ በከፊል አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ልዩ ልዩ የካንሰር ሕክምናዎችን በተሟላ መልኩ መስጠት እንዲችል ተደርጓልም ተብሏል።

ሁሌም ለልህቀት የሚል መርህ አንግቦ እየሠራ የሚገኘው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጤናው ዘርፍ አሁን ላይ በተለይም በሆስፒታሉ ከዚህ ቀደም ይሰጡ የነበሩ የሕክምና አገልግሎቶችን ጥራት አስጠብቆ ማስቀጠል፣ የታካሚዎችን እንግልት ማስቀረት እንዲሁም የጤና ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ታካሚዎች ሁሉንም የጤና አገልግሎቶች እንዲያገኙ ማድረግ ሲሆን፤ አዳዲስ የጤና ፕሮግራሞችን በተሟላ መልኩ ለማስጀመር እየሠራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

በአንድ ጊዜ ለ18 ታካሚዎች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን (ስታንዳርዱን) የጠበቀ የቀዶ ጥገና ሕክምና ማዕከል እየተገነባ መሆኑም ተነግሯል።

እስካሁን ከተጀመሩት የካንሰር፡ የጨረር እና የፎሬንሲክ ሕክምና አገልግሎቶችን ጨምሮ በቀጣይ የስነ-አዕምሮ፡ የኩላሊት እጥበትና ንቅለ-ተከላ እና ሌሎችንም አዳዲስ አገልግሎቶች እንደሚጀመሩም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ ሆስፒታሉ ሲመሰረት ስድስት ሚሊዮን ለሚደርሱ ታካሚዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ግን ከአስራ ስምንት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑ አዳዲስ የጤና ፕሮግራሞችን ለማስፋት የቦታ ጥበት እንደገጠመውም ነግረውናል።

በዚህም ምክንያት የስነ-አዕምሮ ሕክምና አገልግሎት ቢጀመርም አስፍቶ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት አለመቻሉን ጠቁመው፤ የቦታ ጥበትና ሌሎችንም ውስንነቶች በማስተካከል የኅብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ተደራሽት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሠራልም ተብሏል።

አምሳሉ ፈለቀ

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You