”በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የተንጸባረቀው ሃሳብ ተቀባይነት የሌለው ነው”- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፡በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የተንጸባረቀው ሃሳብ ትክክል ያልሆነና ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሰሞኑን ያደረጉት ንግግር በተረጋገጠ መረጃ ላይ ያልተመሠረተና በምርጫ ወደ ስልጣን የመጣን መንግሥት እንጥላለን በሚል የሚንቀሳቀሱ፣ ንጹሐንን ከሚያግቱና ከሚያሸብሩ አካላት ጋር መንግሥትን መጥቀሳቸው ተገቢ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡

የአምባሳደሩ ንግግር የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገሪቷን እንዴት መምራት እንዳለበት ያልተጠየቀ ምክር ለመምከር የሞከረ መሆኑም በመግለጫው የተመላከተ ሲሆን፤ መልዕክቱ ከሁለቱ ሀገራት ታሪካዊና ወዳጅነት ላይ ከተመሠረተው ግንኙነት የተቃረነ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነታቸውን አጠናክረው በመቀጠል በብሔራዊ፣ ቀጣናዊና የጋራ በሆኑ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሠሩ መግለጫው ጠቅሶ፤ ኢትዮጵያ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮችን ጨምሮ ከአሜሪካ ጋር ለመሥራት ያላትን ዝግጁነት አመላክቷል፡፡

ሚኒስቴሩ በአዲስ አበባ ከሚገኘው ኤምባሲ ጋር በመሥራት የተፈጠረውን ስህተት እንዲታረም የሚያደርግ መሆኑን አመልክቶ፤ የተፈጸመውን ዲፕሎማሲያዊ ስህተት ማረም እንደሚገባም ጠቁሟል።

ኢትዮጵያ በመከባበር ላይ የተመሠረተ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር እንዲኖር ቁርጠኛ መሆኗንም መግለጫው አረጋግጧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You