ትንሳዔ ይቅርታንና ምህረትን የምንማርበት በዓል ነው

አዲስ አበባ፡የትንሳዔ ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታና ምህረትን ለሰው ልጆች የሰጠበት፤ የጥልና የመለያየት ግድግዳን አፍርሶ ፍቅርን ያሳየበት በዓል መሆኑን ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ተናገሩ፡፡

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ትንሳዔ በዓል ክርስቶስ ከሞት የተነሳበት በመሆኑ የበዓላት ሁሉ በኩር እና የአማኞች የወደፊት ተስፋ የሚያረጋግጥ በዓል ነው ፡፡

የትንሳዔ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን ፅኑ ፍቅር በመስቀል ላይ ያሳየበት እንዲሁም ይቅርታና ምህረትን ለሰው ልጆች የሰጠበት፤ የጥልና የመለያየት ግድግዳን አፍርሶ የሰውን ልጅ የወደፊት ተስፋ ያረጋገጠበት መሆኑን አውስተዋል፡፡

በዓሉ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩት መንፈሳዊ በዓላት አንዱ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ይህ የትንሳዔ በዓል መታዘዝን፣ ይቅርታንና ምህረትን እንዲሁም አንዱ ለሌላው መተሳሰብ እንዳለበት የሚያስተምር መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በዓሉን ስናከብር መረዳዳትንና መጠያየቅን ከተለመደው ባህል ባለፈ በፍጹም መንፈሳዊነት ስሜት በጎዳና ላይ የወደቁትን በማሰብ፣ ታመው የተኙትን በማጽናናትና ካለን ላይ በማካፈልና በአብሮነት መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በደል ተላልፎ በመሰጠት የሰውን ልጆች ከጨለማ ወደ ብርሃን ነጻ ለማውጣት ዋጋ የከፈለበት በመሆኑ እኛም አቅመ ደካሞችን በመርዳትና ካለን በማካፈል፣ ለወገኖቻችን በመድረስና በመተሳሰብ በዓሉን ማከበር አለብን ነው ያሉት፡፡

ትንሳዔ የክርስትና ዋነኛው ማዕከልና ሰንደቅ ዓላማው የሆነ በዓል መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉ ከሌሎች ሁሉ በዓላት ከፍ ብሎ የሚከበር በዓል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሰሞነ ህማማት ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረውን ብሉይ ኪዳንን የሚወክል የአንድ ሳምንት ጊዜ መሆኑን አመላክተው፤ በሰሞነ ህማማት አማኞች ብሉይ ኪዳን በዓመተ ፍዳ እንዳሉ በማሰብ መስቀል ባለመሳለም፣ እስከ ምሽት በመጾም፣ የክርስቶስ መከራ፣ ሞትና ህመሙን እንደሚያስቡበት ገልጸዋል፡፡

የክርስቶስ መከራ ከሐሙስ እንደሚጀምር ተናግረው፤ በእለቱ በጌቴሴማኒ እየጸለየ ሳለ ከተያዘበት ሰዓት አንስቶ እስከ ማግስቱ 11 ሰዓት ድረስ መከራን ያለማቋረጥ ለ20 ሰዓታት ተቀብሏል ብለዋል፡፡

እንደ ዲያቆን ኃይሌ ገለጻ፤ ክርስቶስ ሁለት ፍርድ ቤቶች ቀርቧል፡፡ በለሊት የአይሁድ ሸንጎ ላይ ቀርቦ ተይዞ ምስክር ተፈልጎበታል፡፡ ብዙ መከራ፣ ግፍ እየተፈጸመበትና እየተተፋበት በጉድጓድ ውስጥ ሌሊቱን አሳልፏል፡፡

በማግስቱም የቄሳርን መንግሥት፣ ግብርን አትክፈሉ ይላል በማለት የሀሰት ክሶችን አቅርበው በቄሳር ፊት እንደከሰሱት ተናግረው፤ አማኞች ሰሞነ ሕማማትን የክርስቶስን ስቃይ እያሰቡ እንደሚያሳልፉ አስረድተዋል፡፡

ክርስቶስ በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱን ተናግረው ፤ የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳዔ በዓልን ሲያከብሩ ጌታ እርቃኑን በሆነ ጊዜ እንደገነዙት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ እርቃናቸውን የሆኑ ሰዎችን በማልበስ እና የተቸገሩ ሰዎችን ካላቸው በማካፈል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You