የበልግ ዝናብ በሰብሎች ጉዳት እንዳያስከትል የውሃ ማንጣፈፍ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል

አዲስአበባ ፦ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው ከፍተኛ እርጥበት በሰብሎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያስከትል የውሃ ማንጣፈፍ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መረጃ እንደገለጸው፤በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚኖረው ከፍተኛ እርጥበት በሰብሎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል ይችላል። በተለይም የአፈር ጸባያቸው ውሃ በማያሰርጉና ረባዳማ በሆኑ ቦታዎች ላይ የእርጥበት መብዛት እና ውሃ በሰብሎች ላይ መተኛት እንዳያስከትል የውሃ ማንጣፈፍ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል።

በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ፤ በምሥራቅ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በመካከለኛው፣ እንዲሁም በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖራቸው የጠቀሰው ኢንስቲትዩቱ፤ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በርካታ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁሟል።

እንደ ኢንስቲትዩቱ መረጃ፤ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚጠበቀው የእርጥበት ሁኔታ በበልግ ወቅት የሚከናወነው የግብርና ሥራ እንቅስቃሴን በተጠናከረ ሁኔታ ለማከናወን አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል። የሚገኘው እርጥበት ቀደም ብለው ለተዘሩና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁሟል። ኢንስቲትዩቱ ቀደም ብለው የሚዘሩ የመኸር ሰብሎችን ለመዝራትና ዘግይተው ለሚዘሩ የመኸር ሰብሎች የማሳ ዝግጅት ለማድረግም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመላክቷል።

የሚጠበቀው እርጥበታማ ሁኔታ ለአርብቶ አደርና ለከፊል የአርብቶ አደር አካባቢዎች ለዕጽዋት ልምላሜ፣ ለግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ከማሻሻል አንጻር ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። የሚመለከታቸው አካላትም ከአርሶ አደሮች ጋር በጋራ በመሆን የግብዓት አቅርቦቱን በወቅቱ በመጠቀም የእርሻ ሥራውን በተሟላ መልኩ ማካሄድ እንዳለባቸው ገልጿል።

በሚቀጥሉት ቀናት በአባይ፣ ተከዜ፣ ባሮ አኮቦ፣ አዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ዋቤ ሸበሌ እና ገናሌዳዋ ተፋሰሶች ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚጠበቅ እንዲሁም ከአፋር ደናክል፣ ከኦጋዴን፤ ከተከዜ ተፋሰሶች በስተቀር የተቀሩት ተፋሰሶች ከመጠነኛ እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚኖራቸው የኢንስቲትዩቱ መረጃ አመላክቷል።

በየተፋሰሶች የሚገኙት የውሃ አካላት የተሻለ የውሃ መጠን እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው በመረጃው የተመላከተ ሲሆን፤ ለመስኖም ሆነ ለኃይል ማመንጫነት የሚያገለግሉ የግድቦችን የውሃ መጠን የሚያሻሽል በመሆኑ፤ እድሉን ለመጠቀም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ከወዲሁ ማከናወን እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You