የበኩር ልጅ ፈተና

ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች አሏት፤ መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም ይኖራል። ከመውረድ ውስጥም በትጋት መውጣት ይቻላል። አግኝቶ ማጣት እንዳለ ሁሉ አጥቶም ይገኛል። ይህ የሕይወት እውነታ ነው፤ በጥቂቶች የህይወት መውጣትና መውረዶች ውስጥ ብዙዎች ይማራሉ። የህይወትን ፈተናዎችም ያውቃሉ። በከፍታ ውስጥ የሚገኙት ‹‹እንዲህም ይኖራል እንዴ?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ። ለተቸገሩት ያዝናሉ፤ ካላቸው ቀንሰው የሌሎችን ችግር ይካፈላሉ፤ በተጨማሪም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ ከችግር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ ለመፍትሄ የሚታትሩትንም ያበረታታሉ። በመሆኑም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን በከፈትነው አምዳችን ህይወትን በየፈርጁ ታስተውሉበት፤¸አስተውላችሁም ትማሩበት ዘንድ ጋበዝናችሁ። ለአስተያየቶቻችሁ፤ ለመሰል ታሪኮች ጥቆማችሁ እንዲሁም ለድጋፋችሁ የዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ትጠቀሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።

እሷና ልጅነት…

በቤቱ ካሉት ዘጠኝ ልጆች መሀል ስድስተኛ ሆና ትቆጠራለች። ነጋዴው አባቷ መልካም አባወራ ናቸው። ልጆቻቸውን በወጉ ያስተምራሉ፣ ቤታቸውን በአግባቡ ይመራሉ። የወላይታዋ ጉብል በቤት በከተማው በመልካም ሁኔታ አድጋለች። ይህ ይሆን ዘንድ የፍላጎቷን የከለከላት የለም። እንደ ልጅ ያሻትን ለማድረግ ተሳቃ፣ ተሸማቃ አታውቅም። እንደምርጫዋ ለመማር ዕድል ከእሷ ጋር ነበረች።

ልሳን ምትኩ ለቤተሰቦቿ ልዩ አክብሮት አላት። ዘጠኝ ልጆች ተወልደው ያደጉበት ቤት ዓመታትን በፍቅርና ሰላም ዘልቋል። ሁሉም የአንድ እናት አባት ፍሬዎች ናቸውና በመተሳሳብ፣ ልምዳቸው ይታወቃሉ። ልሳን ትምህርቷን ጀምራ ያጠናቀቀችው ወላይታ ሶዶ ከተማ ላይ ነው። እንደ ማንኛውም ልጅ ነገን በመልካም ለመሻገር ስታልም ቆይታለች።

እሷ ተምራ፣ ተለውጣ የሃሳቧን መሙላት ፍላጎቷ ነው። ዋጋ ከፍለው ያስተማሯትን ወላጆች ውለታ አትዘነጋም። ሁሌም የልፋቷን ለማየት ትሻለች። ልሳን ወላይታ ላይ ያጠናቀቀችው ትምህርት በነበረችበት እንድትቆይ አላስቻላትም። ስለነገው ከፍ ብላ ብታስብ አካባቢውን መልቀቅ ግድ አላት። ወላይታን ርቃ ሀዋሳ ላይ ከተመች።

ሀዋሳና ልሳን በትምህርት ዓለም ተገናኙ። አሁንም ስለነገዋ እያሰበች ነው። ዛሬም እንደ አንዲት ወጣት ተምራ መሻሻል፣ መለወጥን ታስባለች። ውላ አድራ ምርጫዋን ለየች። ውስጧ ለሕክምናው ዘርፍ አደላ። የላብራቶሪ ቴክኒሻንነትን መርጣ ትምህርቱን ጀመረች።

ሀዋሳና ልሳን ባዕዶች አልሆኑም። አካባቢውን በወጉ ለመደች፣ ከብዙዎችም ተግባባች። የትምህርት ቆይታዋ ሲጠናቀቅ ዲፕሎማዋን ይዛ በተማረችበት መስክ ሥራ ፈላለገች። ሁኔታው እንዳሰበችው አልሆነም። ያለ አንዳች ውጤት ቀናት ተቆጠሩ፣ ወራት ተከተሉ። በሙያዋ ሥራ ለማግኘት ቸገራት።

አሁንም የልሳን ኑሮ ሀዋሳ ላይ ነው። በተማረችበት መስክ ሥራ ባታገኝም ዕድል ፊቷን አልነሳቻትም። ወደ ንግዱ መለስ ብላ መተዳደሪያዋን ፈጠረች። በንግዱ ብዙ አልዘለቀችም። ከዛሬው የትዳር አጋሯ ጋር ተዋወቀች። ጥምረታቸው መልካም ሆኖ ለ ትዳር ተሳሰቡ።

ሶስት ጉልቻን-በበኩር ልጅ

አሁን ልሳን ባለትዳር ሆናለች። ጎጆዋ ሰላማዊና በፍቅር የተሞላ ነው። ባለቤቷ በንግድ ይተዳደራል። ጥንዶቹ በመተሳሰብ፣ በመከባበር መኖር ይዘዋል። ውሎ አድሮ ይህ መልካም ትዳር በልጅ ስጦታ ተባረከ። የመጀመሪያ ሴት ልጃቸውን ወልደው ታቀፉ። እንዲህ መሆኑ የሁለቱን አንድነት አጸና። መተሳሰብ ፣ መዋደዳቸው ጨመረ።

ለቤታቸው ብርሃን፣ ለሕይወታቸው ስጦታ የሆነችውን ፍሬ ‹‹ረድኤት›› ሲሉ ሰየሟት። ረድኤት ለሁለቱም የመጀመሪያ ልጅ ነች። የእሷ መምጣት ሕይወታቸው ላይ ደስታን አክሏል። በየቀኑ በፍቅር ዓይን ይቃኟታል። ደስታዋ ሰላማቸው፣ ፈገግታዋ ድምቀታቸው ሆኗል።

ትንሽዋ ስጦታ የቤታቸው ታላቅ በረከት ሆና ሕይወታቸውን እያደመቀች ነው። ስለእሷ ስስት ፍቅራቸው ይለያል። መሽቶ በነጋ ቁጥር ልዩ ጉዳያቸው ሆናለች። ረድኤት ‹‹ዳዴ›› ማለቷን ጨርሳ ‹‹ወፌ ቆመች›› ከምትባልበት ዕድሜ ደርሳለች። ሁሉም የእሷን ቆሞ መራመድ፣ ሮጦ መንደርደር እየጠበቁ ነው።

ይህ አልፎ ቀጣዩ ጊዜ ሲመጣ በኮልታፋ ምላሷ ‹‹እማማ፣ አባባ›› ማለትን ጀመረች። ክፉን ከደግ ባትለይም እናት አባቷን በወጉ አወቀች። በየጊዜው ያላት ለውጥ በየቀኑ ዓይኖቿን እያዩ ለሚሳሱላት ወላጆች ልዩ ትርጉም ፈጠረ። ልጃቸውን ይበልጥ ወደዷት ። በየዓመቱ የልደት ቀኗ በልዩ ድምቀት መከበሩን ቀጠለ።

የትምህርት ጉጉት

አሁን ረድኤት ትምህርት ቤት የምትገባበት፣ የቀለም ሀሁን የምትቆጥርበት ወቅት ነው። ለዚህ ጊዜ መብቃቷ ለእናት አባቷ ልዩ ደስታን አቀብሏል። ጥንዶቹ በበኩር ልጃቸው ወግ ማዕረግ ማየታቸውን እያሰቡ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ያዙ። ትንሽዬዋ ልጅ ደስተኛ ነች። እንደእኩዮቿ ትምህርት ቤት ልትገባ መሆኑ ፈገግታዋን ጨምሯል።

ረድኤት የመጀመሪያ ዓመቱን የአጸደ ሕፃናት ትምህርት ጀመረች። ከቤት ወጥታ የውጭውን ዓለም ያየችው ሕፃን በየዕለቱ በሚገጥሟት ለውጦች ደስተኛ ሆነች። ከእኩዮቿ ጋር ተምራ፣ ዘምራ መመለሷ ትምህርት ቤቷን አስናፈቃት።

ሁለተኛውን ዓመት እንደጀመረች ግን ደስታዋን የሚያደበዝዝ አጋጣሚ ተፈጠረ። በመላው ዓለም የተከሰተው የኮረና በሽታ የእሷንም ውጥን ሊፈትን ግድ ሆነ። ጅምር ትምህርቷ ተቋርጦ ከቤት መዋል ያዘች። ፈታኙ ጊዜ አልፎ መልካም ዘመን ሲመጣ ረድኤት ያቋረጠችውን ትምህርት እንደ አዲስ ለመጀመር ትምህርት ቤቷ ተገኘች።

ትንሽዬዋ ልጅ በፍቅር የሚታሰቡ ምርጥ የትምህርት ጊዚያትን አሳልፋ ለፍጻሜው ቀን ደረሰች። ይህ ወቅት እሷን መሰል ሕፃናት የመመረቂያ ካባቸውን ደርበው በወላጆቻቸው ፊት የሚቆሙበት ተናፋቂ ቀን ነው። እንዲህ መሆኑ ለነገዎቹ ሀገር ተረካቢ ትውልዶች ታላቅ ዐሻራን ያሳርፋል። ከካባው በስተጀርባ ነጋቸውን እንዲያቅዱበት፣ ምክንያት ይሆናል።

የእነሱ ደስታ

ረድኤት ዛሬ በእናት አባቷ ፊት ደስታዋን ልታውጅ ጊዜው ደርሷል። እነሱን ጨምሮ መላው ቤተሰብ በውስጡ ያደረው ስሜት የተለየ ሆኗል። በርካታ ወላጆች በሚታደሙበት ድንቅ ቀን ተገኝቶ የልጅን ደስታ መካፈል ለጥንዶቹ ትርጉሙ ይለያል።

አሁን ወይዘሮ ልሳንና ባለቤቷ በልጃቸው የምርቃት ቀን ተገኝተው ዓለሟን ተካፍለዋል። በትምህርት ቤቱ ከሚገኙ ልጆች፣ ከቤተሰብና መምህራን ጋር ጥሩ የሚባል ቀን አልፎ ምርቃቱ ተከናውኗል። በቤተሰብ መሀል ስለ ደስታው የሚደረገው ሁሉ በወጉ ተከውኗል። ትንሽዬዋ ልጅ የአጸደ ሕፃናት ቆይታዋን አሳክታ በድምቀት ተመርቃለች።

እነሆ! ጊዚያት ተቆጠሩ። አሁን ረድኤት አንደኛ ክፍል ለመግባት ምዝገባዋን አጠናቃለች። ከዚህ በኋላ መደበኛ ትምህርቷን ለመቀጠል መሠረት የምትጥል ይሆናል። እናት አባት ይህን ሲያስቡ ስለነገዋ ታላቅ ሴት ያልማሉ። የሚያሻትን ሞልተው፣ የምትፈልገውን ለማድረግ የእጃቸውን አይሰስቱም።

አንዳንዴ ረድኤት ከአፍንጫዋ ነስር ይታያል። ሁኔታው ሁሌም ባለመሆኑ ‹‹ነገሬ ›› የሚለው የለም። ከዚህ ቀድሞ ታማ አታውቅምና ጉዳዩ ትኩረት አልተሰጠውም። ያዝ ለቀቅ የሚያደርገው ምልክት ከአጋጣሚዎች ተቆጥሮ ቀናት አልፈዋል።

ድንገቴው ለውጥ…

ረድኤት የአንደኛ ክፍል ትምህርቷን ከመጀመሯ በፊት የታየባት ለውጥ ቤተሰቡን አስደንግጧል። ባልተለመደ ሁኔታ ሰውነቷ እየተጎዳ አቅም እያነሳት ነው። አንዳንዶች ከምልክቱ ተነስተው ወባ መሆኑን ጠርጥረዋል። ከሰፈር ክሊኒክ ተወስዳም የተረጋገጠው ሀቅ ይኸው ሆኗል። ወደላይ እያለ የሚያስቸግራት ሕመም ከከባድ ትኩሳት ተዳምሮ እያስጨነቃት ነው።

‹‹ወባ ነው›› ተብሎ የተጀመረላት ሕክምና ለውጥ አላመጣም። የሚሰጣት መድኃኒት ትርጉም አልባ ሆኖ ትንሿን ልጅ ያዳክማት ያዘ። ይህ እውነት ዘወትር ፈገግታዋን ለሚናፍቁት ወላጆቿ እጅግ አስደንጋጭና አሳሳቢ ሆኖ ከረመ። ምርጫ ያጡት እናት አባት የሕክምናውን ደጃፍ ተመላለሱበት። የተገኘ ለውጥ አልነበረም።

እናት አባት ይሻላል ወዳሉት የግል ሐኪም ወስደው አስመረመሩ። ሐኪሙ የራሱን ምርመራ አከናውኖ ሲጨርስ ጥርጣሬውን ለወላጅ አባቷ አሳወቀ። ሕፃኗ የካንሰር ምልክት እንደሚታይባት ነገረው። ውጤቱ ገና ጥርጣሬ ቢሆንም አባት ፍጹም ያልገመተው ዱብ ዕዳ ሆነበት።

የሕፃኗን አባት ይህን ክፉ ዜና ከሰማበት ደቂቃ ጀምሮ ከራሱ ጋር ተጣላ፤ ማንነቱ ተፈተነ። እውነታውን ለባለቤቱ ደፍሮ ለመንገር ድፍረቱን ቢያጣ በሕይወቱ ላይ ሊፈርድ ወሰነ። እንደ ዓይኑ ብሌን በሚያያት የበኩር ልጁ ላይ የሆነውን አምኖ መቀበል ተሳነው። በድንገት የሰማው እውነት የብቻው ሚስጥር ሆኖ በከባድ ሀዘን ጋየ። ጉዳዩን የተረዱ የቅርብ ሰዎች መክረው፣ ተቆጥተው አጽናኑት። ከመጥፎ ሃሳቡ መልሰውም ቀጣዩን መንገድ አመላከቱት።

ቀን አልባከነም። ረድኤት ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተጻፈላት። እናት አባት ጊዜ ሳይሰጡ ወደተባለው ስፍራ በአምቡላንስ አደረሷት። በቦታው አስፈላጊው ምርመራ ተከወነ። ሕፃኗ በውስጧ በቂ የሚባል ደም አልተገኘም። በአፋጣኝ ደምና ‹‹ፕላትኔት›› ተሰጣት። ቀስ በቀስ አገገመች። ዓይኗን ገልጣ ያዩዋት ቤተሰቦች ፈገግታቸው ተመለሰ።

አስራ አምስት ቀናትን ያስቆጠረው ቆይታ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልገው ተነገራቸው። ረድኤት ከባዱን ‹‹የቦን ማሮ›› ምርመራ መወሰድ ነበረባት። ከአንድ ወር በኋላ የምርመራው ውጤት ደረሰ። እንደተሰጋው ውጤቱ የከፋ አልሆነም።

የፈዘዘ ፈገግታ…

የተሰማው እውነት ለወላጆች ደስታን አላብሶ ወደቤት መለሳቸው። ሀዋሳ ላይ ዳግም ሕይወት ተጀመረ። ትንሽዬዋ ልጅ ያቋረጠችውን የአንደኛ ክፍል ትምህርት ልትጀምር የደብተር ቦርሳዋን አነሳች። እናት አባት ዳግም ተስፋቸው ለመለመ። በምስጋና ተሞልተው የልጃቸውን የሰላም ውሎ ተመኙ።

ይህ ደስታ ብዙ አልቆየም። ረድኤት ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ ሕመሙ ተመለሰባት። ቀድሞ የነበረው ምልክት ዳግም ቢያገረሽ የቤተሰቡ ጭንቀት ጀመረ። ነስርና ትኩሳቱ ከማስመለሱ ጋር ተደራርቦ ውጭ ለመውጣት አቃታት። ቀድሞ የውጤቱን መልካም መሆን የሰሙት እነ ልሳን የአሁኑ ሕመም ወባ መሆኑን ጠርጥረው ወደ ሐኪም ቤት ፈጠኑ። አቅሟ በመዳከሙ ሆስፒታል አልጋ ይዛ መተኛት ጀመረች።

ጥቂት ሻል ባላት ጊዜ ወደ ቤት ትመለሰች። ቆይታዋ ብዙ አይሆንም። ሕመሙ እያገረሸ ያሰቃያታል። መፍትሔ የታጣለት ችግር በየግል ሆስፒታል ያንከራትታቸው ያዘ። በወቅቱ የሚሰጣት መድኃኒት የወባ ሕመም ማስታገሻ ብቻ ነበር።

ለጊዜው መለስ ያለ የሚመስለው ሕመም ስቃዩ የከፋ ነበር። ረድኤት እጅና እግሯ ያብጣል፣ ራሷን ችላ አትራመድም። በየጊዜው አቅሟ ይዳከማል። ለውጥና ፈውስ የታጣለት ሕመም አሁንም ወደ ሌላ የግል ሆስፒታል ሊያመራ ግድ ሆኗል። በዚህ ስፍራ የመረመሯት ሐኪም ወባ ብቻውን እንዲህ ሊያደርግ እንደማይችል እየነገራቸው ነው። እሱ በግሉ ከሚደርገው ምርመራ የሚገኘው ውጤትም ወሳኝነት አለው።

ለሐኪሙ በምርመራው አንገቷ ስር ያገኘው ዕብጠት በቂ ምልክት ሆኗል። ይህን ተከትሎ በአስቸኳይ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተልከዋል። ትንሽዬዋ ልጅ አሁንም እየደከመች ነው። እነሱ ውስጣቸው ቢያዝንም ተስፋ አልቆረጡም። ዳግም ፈታኙ የቦን ማሮ ምርመራ ተጀመረ።

ከጀርባ አጥንት የሚወሰደው ናሙና እጅግ ስቃይ የበዛበት ነው። ብዙዎችን ሕሙማን የሚያዳክምና ገድሎ የሚያነሳ ዓይነት ከባድ ስሜት አለው። ይህን ሁሉ ፈተና ተሻግራ ዳግም ምርመራውን የጀመረችው ሕፃን በውስጧ የካንሰር ሕመም ስለመኖሩ ተረጋግጧል።

ይህ እውነት ከሕመሙ ነፃ ሆናለች ብለው ላመኑት ለእነ ረድኤት አባት ዳግም ሀዘን ነበር። ተከታታይ ሕክምናውን ያገኘችው ረድኤት ለመኖር ከሕመም እየታገለች ነው። ዛሬም የእናት አባቷ ጭንቀት ቀጥሏል። አሁን የሕመሙ ዓይነት የደም ካንሰር መሆኑ ተረጋግጧል።

ዳግም ብርታት…

እናት ልሳን እስከዛሬ በሽፍንፍን የተደበቃትን ትክክለኛ ሕመም በግልጽ ያወቀችበት ፈታኝ ጊዜ ሆነ። ስሜቱ ከቃል፣ ከድርጊት በላይ ሆኖ አብሯት ከረመ። ለልጇ መኖር እውነቱን አምና፣ ጠንክራ ከመቆም ውጭ ምርጫ አልነበራትም። እናም አደረገችው። ብታዝንም፣ የእናትነት አንጀቷ ቢለወስም፣ ጠነከረች፣ በረታች፣ ስለበኩር ልጇ እስትንፋስ ትንፋሿን ውጣ ከጎኗ ቆመች።

ይህን ውጤት ተከትሎ የሚሰጠው የኬሞ ቴራፒ ሌላው የጭንቀትና የከባድ ሕመም ማሳያ ነው። ይህን ሁሉ የቻለችው ብላቴና ብትደክምም፣ ብትወድቅም ችግሩን በየተራ እየተወጣችው ነው።

አሁን ረድኤትና ሕክምናው በአግባቡ ተናበዋል። የሚመጣውን ችግር ሁሉ ችላ ማሸነፍ እንዳለበት የገባት ይመስላል። ትንሸዋ ልጅ በጥንካሬ መበርታት ይዛለች። አሁን ለቤተሰቡ ከሐኪሞች ሕክምናው ረጅም ጊዜ እንደሚፈልግ ተነግሯቸዋል።

እነ ልሳን በአንድ ጊዜ ታክሞ ወደቤት መመለስ እንደማይኖር አውቀዋልና ግማሽ ሕይወታቸው አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ሆኗል። ይህ ዓይነቱ ሀቅ የበርካታ ቤተሰቦችን የካንሰር ሕሙማን እውነተኛ ታሪክ ነው። ብዙዎቹ ከሀገራቸው ሲወጡ ስለሕክምናው ወጪ ቤት ንብረታቸውን፣ በሬና ላማቸውን ሸጠው ነው።

ልሳን ሆስፒታል ውስጥ ልጇን ይዛ መቆየቷ ለኢንፌክሽን እንደሚያጋልጥ ተነግሯታል። ይሁን ብላ እንዳትወጣ ቤት ኑሮዋ አዲስ አበባ አይደለም። አሁን ቤት ለመከራየት ሆቴል ለመክፈል የሚያስችል አቅም ከእሷ የለም።

እንዲህ ዓይነቱ ታሪክ በነረድኤት ቤተሰብ ሊያልፍ ግድ ቢልም በጥንካሬ ተወጥተውት ለዛሬ ደርሰዋል። ዛሬ በማቲዎስ ወንዱ የካንሰር ሶሳይቲ ቅጥር የእንግድነት ወግን አግኝተዋል። የስምንት ዓመቷ ረድኤት ከእሷ በኋላ የተወለዱ አራት እህት ወንድሞቿ ተስፋዎቿ ናቸው። በየቀጠሮ ብትለያቸውም በፍቅር ያስቧታል።

አሁን ረድኤት ፍጹም ጤነኛ ናት። ክትትል በሚኖራት ጊዜ በሆስፒታሉ ተገኝታ ትታከማለች። እናቷ ልሳን ያለፈውን ስታወሳ በዓይኖቿ ዕንባ ይሞላል። እንደትናንቱ ግን ክፉ ሃሳብ በውስጧ አያልፍም ስለበኩር ልጇ ነገ መልካም ነገር ታስባለች።

ስለነገ …

እሷ ልጇ መልኳ፣ መስታወቷ ነች። ብዙ ታሪክ አይታባታለች። እሷ የሕይወቷ ድልድይ ነች። አያልፉ ይመስሉ ፈተናዎችን ተሻግራባታለች። ዛሬም ከጎኗ ሆኗ ስለነገዋ እያለመች፣ እያሰበች ነው። ብዙ ከፈተናት ካስጨነቃት ሕመሟ ድና እንደ ልጅነቷ ህልም ዳግም በጥቁር ካባ ልታስመርቃት፣ ከደስታዋ ልትካፈል ህልም አላት። ይህ ህልሟ አንድ ቀን እንደሚፈታ ታውቃለችና።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You