75 ቀናት ብቻ በቀሩት የፓሪሱ ኦሊምፒክ ሀገራት የአትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድኖቻቸውን በማሳወቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በስፖርቱ ተጠባቂ ከሆኑ ሀገራት መካከል የምትመደበው ኢትዮጵያም በተለያዩ ርቀቶች እጩ አትሌቶቿን አሳውቃ ዝግጅት የተጀመረ ሲሆን፤ አጓጊው የማራቶን ቡድንም ከትናንት በስቲያ ይፋ ተደርጓል፡፡ ይኸውም አስፈሪው ማራቶን ሊያሰኘው እንደሚችል ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ጭምር እየተቀባበሉት ይገኛሉ፡፡ በተለይ የአትሌቲክስ ቤተሰቡን ቀልብ የሳበው ግን የጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ኦሊምፒክ መመለስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይፋ ባደረገው የአትሌቶች ዝርዝር መሰረት በሴቶች የማራቶን የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ፣ የዓለም ቻምፒዮናዋ አማኔ በሪሶ እንዲሁም መገርቱ ዓለሙ ሲመረጡ፤ የዓለም ቻምፒዮና ስኬታማ አትሌት ጎይተቶም ገብረስላሴ እንዲሁም ቡዜ ድሪባ ተጠባበቂ ሆነዋል፡፡ በወንዶች ደግሞ ባለፈው ወር የተካሄደውን የቦስተን ማራቶን በአሸናፊነት ያጠናቀቀው ሲሳይ ለማ፣ የዙሪክ (ሴቪሌ) ማራቶን አሸናፊው ደሬሳ ገለታ እንዲሁም ባለፈው ወር የለንደን ማራቶንን በሰከንዶች ብቻ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው ከኢትዮጵያ የምንጊዜም ጀግና አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ቀነኒሳ ተመርጠዋል፡፡ በኦሪጎን የዓለም ቻምፒዮና የነበረው አትሌት ታምራት ቶላ እና ኡሰዲን መሃመድ ተጠባበቂ አትሌቶች መሆናቸውም ታውቋል፡፡
ምርጫውን ተከትሎ በዚህ ርቀት በተጽእኖ ፈጣሪነታቸው ከሚታወቁት የምሥራቅ አፍሪካ ሀ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ፓሪስ ላይ ታሪካዊ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል ቡድን ይዛለት፡፡ ዜናውን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የእጩዎቹን ተከትሎ ስለምርጫውና መስፈርቱ ያቀረበው ዝርዝር ባይኖርም አትሌቶቹ ባላቸው ወቅታዊ ብቃትና የማራቶን ፈጣን ሰዓትን መሰረት መመረጣቸው ታውቋል፡፡ በተለይም በወንዶች በኩል አንጋፋው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በቡድኑ መካተት ውድድሩን ከወዲሁ አጓጊ አድርጎታል፡፡ የረጅም ርቀት አትሌቲክስ ንጉሱ በርካታ ክብሮችን ከተቀዳጀበት መድረክ ከራቀ ከ12 ዓመታት በኋላ ደግም የሚሮጥ ሲሆን፤ ምናልባትም የመጨረሻው ተሳትፎውም ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
ቀነኒሳ ከታወቀበት የረጅም ርቀት የመም ውድድር ወደ ጎዳና ላይ ሩጫ ከተሸጋገረ በኋላ የስፖርት ቤተሰቡ የለመደውን ስኬት ቢጠብቅም በተደጋጋሚ በሚገጥመው ጉዳት ምክንያት በማራቶን ሊነግስ አልቻለም፡፡ በእርግጥ ባለፉት ዓመታት 18 የሚሆኑ የዓለም ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች ላይ ተካፋይ በመሆን ተደጋጋሚ ድሎችን ማጣጣም ችሏል፡፡ ነገር ግን በዚህ ርቀት ክብረወሰን የመስበር ፍላጎቱ በ2ሰከንዶች መዘግየት እውን መሆን አልቻለም፡፡ እአአ በ2019 በርሊን ማራቶንን 2:01:41 በሆነ ሰዓት የገባው ቀነኒሳ በርቀቱ ሶስተኛው ባለፈጣን ሰዓት አትሌት ነው፡፡ በቀጣዩ ወር 42ኛ ዓመቱን የሚያከብረው ይህ ድንቅ አትሌት ከወራት በፊት ቫሌንሺያ ላይ 4ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ለንደን ላይ ደግሞ ለአሸናፊነት ያደረገው ብርቱ ፉክክር አስደማሚ ነበር፡፡
ስፍር ቁጥር ከሌለው የአትሌቲክስ ስኬቶቹ መካከል በሶስት የኦሊምፒክ ተሳትፎዎቹ 3 የወርቅና 1 የብር ሜዳሊያዎችን እንዲሁም አንድ ዲፕሎማ አስመዝግቧል፡፡ የመጀመሪያውን የዓለም ቻምፒዮና ተሳትፎውን በማድረግ የወርቅ እና ነሃስ ሜዳሊያዎችን ባጠለቀበት እንዲሁም የመጀመሪያውን የማራቶን ድሉን በተዋወቀበት ፓሪስ በተናፋቂው የኦሊምፒክ ተሳትፎው ዳግም ይመለሳል፡፡ ቀነኒሳ ከዓመታት በኋላ በመድረኩ ከመታየቱ ጎን ለጎን ጉዳዩን ይበልጥ ሳቢ ያደረገው ደግሞ ከመም እስከ ጎዳና የምንጊዜም ተፎካካሪው ከሆነው ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ ጋር ዳግም መገናኘታቸውም ጭምር ነው፡፡
የሁለቱ ሀገራት አትሌቶች በማራቶን ከአሸናፊነት ፍልሚያ ባለፈ ተሳትፏቸው የዓለም ክብረወሰንን ለማሻሻል ያለመ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአትሌቲክሱ ዓለም ለዓመታት ነግሰው የቆዩት ሁለቱ ድንቅ አትሌቶች የሁለት ሰከንዶች ብልጫቸውን ለማሻሻል እርስ በእርስ የሚያደርጉት ፉክክር ውድድሩን እጅግ ሊያከረው እንደሚችል ከወዲሁ ይገመታል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የማራቶን ጀግኖቹ ለወጣት አትሌቶች ታላቅ ተሞክሮና በተፎካካሪነትም ልምምድና ሞራልን የሚያዳብሩበትን አጋጣሚ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የአትሌቲክስ ቤተሰቡ ብቻም ሳይሆን በአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ሊዘነጋ የማይችል ድንቅ ትዕይንትና የኦሊምፒኩም ድምቀት የሚሆን ማራቶን ስለመሆኑ እርግጥ ነው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም