የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴያችን ውስጥ ልዩ ሚና እንዳለው ይታመናል። ዘርፉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲካሄዱ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ሥራዎች እንዲሳኩ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ይታወቃል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከሀገሪቱ የካፒታል በጀት 60 በመቶውን የሚጠቀም ግዙፍ ዘርፍ ነው። ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 23 ነጥብ 2 በመቶውንም ይሸፍናል። በቀጥታና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የሥራ እድል በመፍጠር በኩልም ከግብርናው ዘርፍ ቀጥሎ ይጠቀሳል።
ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ ግንባታዎቹን ተከትሎም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች በኩልም ለውጦች ታይተዋል። ይሁንና ዘርፉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገጠሙት አያሌ ተግዳሮቶች ሳቢያ ህልውናው አደጋ ውስጥ መውደቁ ይገለጻል። የዘርፉ ተዋንያንም ይህን ችግር በየመድረኮቹ ሲያስገነዝቡ ቆይተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማና መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቅርቡ ‹‹የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተግዳሮት፣ መውጫ መንገዶችና የሕግ አውጪው ሚና›› በሚል በምክር ቤቱ አዳራሽ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ በቀረቡ ጽሑፎችም ሆነ በተሰጡ አስተያየቶች እነዚሁ ችግሮች ተጠቁመዋል።
መድረኩን ያዘጋጀው የከተማና ትራንስፖርትና መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ሀብት የሚፈስበት በሌሎች ዘርፎች የታቀዱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሥራዎች እንዲሳኩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን አስታውቀዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከየምርጫ ክልሎች ከሚቀርቡ ጥያቄዎች አብዛኞቹ ከመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ጋር የተያያዙ ናቸው ያሉት ሰብሳቢዋ፣ በዘርፉ ያሉ ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው ዘርፉ ለብልሹ አሠራርና ሌብነት ተጋላጭነት ያለው፣ በገበያ መናር የሚቸገር፣ ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ግብዓቶች ጥገኛ የሆነ፣ የጸጥታ ችግሮች፣ የተቋራጮች አቅም ማነስ እንደሚስተዋልበት ጠቁመዋል። ተግዳሮቶቹ ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜና በጀት ማጠናቀቅን ፈታኝ አድርገውት መቆየታቸውንም አመልክተዋል። የኢንዱስትሪውን ተግዳሮቶች ለመፍታት የባለድርሻ አካላትን ትብብር እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ ሁላችንም ተገቢውን ሚና እንድንወጣ እጠይቃለሁ ሲሉ አስገንዝበዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ተዋንያን፣ አንጋፋና ወጣት የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በተገኙበት፣ በዚህ መድረክ ላይ ዘርፉን የተመለከቱ አራት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በጽሑፎቹ ላይም ተሳታፊዎች አስተያየቶችን፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።
በመድረኩ የዘርፉ ተግዳሮቶች በሚል ከቀረቡት መካከልም የተቋራጮች አቅም ማነስ፣ የክፍያ መዘግየት፣ የግዥ ሥርዓቱ ዘርፉን ታሳቢ ያላደረገ መሆን፣ ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ መሆን፣ የሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት፣ የፕሮጀክት አስተዳደር ጉድለት፣ የጸጥታ ችግር የሚሉት ይገኙበታል። የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር፣ የጥራት ጉድለት፣ የፕሮጀክት መዘግየት፣ የባለሙያ ብቃት ማነስ የሚሉትም ሌሎች በተግዳሮትነት የተጠቀሱ ናቸው።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ መድረኩን ዘርፉን ከመርገምና የነበሩትን ችግሮች ብቻ ከማውራት በመውጣት መፍትሔ ለመስጠት አንድ ደረጃ ወደፊት የተራምድንበት ነው ሲሉ ገልጸውታል። በመድረኩ ከቀረቡ ሃሳቦች አብዛኞቹን እንደ ግብዓት እንወስዳቸዋለን ሲሉ ተናግረዋል።
የዘርፉን ተግዳሮቶች ለማስወገድ በመውጫ ጉዳዮች ላይ መወያየታችን ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የመጀመሪያው የዘርፉ አቅም ተደርጎ የሚወሰደው ባለሙያው ይላሉ። የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንም ሆኑ በሴክተሩ ውስጥ ያሉት ባለሙያዎች ዘርፉ ከሚፈልገው የሙያ አቅም አኳያ ሲታዩ በጣም ብዙ ርቀት መራመድ እንዳለብን እንገነዘባለን ሲሉ አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከባለሙያዎች አቅም አኳያ ያለውን ችግር ለመፍታት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ በቂ እውቀት የሚጨብጡበትን፣ ወደ ኢንዱስትሪው ሄደው ልምምድ የሚያደርጉበትን እንዲሁም ባለሙያው ወደ ኢንዱስትሪው ሲገባም የክህሎት ስልጠና የሚወስድበትን ሥርዓት መዘርጋት ይገባል።
በአማካሪዎችና ሥራ ተቋራጮች ዘንድ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ በዋነኛነት ኮርፖሬት ባህልን/ ካልቸርን/ መፍጠር ያስፈልጋል። የኛ ተቋራጮችና አማካሪዎች የአንድ ሰው ኩባንያዎች ናቸው፤ ባለቤቱ ተስፋ የቆረጠ ወይም ደካማ የሆነ ቀን ይፈርሳሉ ሲሉ አስገንዝበዋል። ኩባንያዎቹ ለትውልድ የሚሻገሩ ኮርፓሬት ተቋማት እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ ነባር ቴክኖሎጂዎችን ማላመድ እንዲሁም አዳዲስ የግንባታ ሞዴሎችን ማምጣት ላይ መሰራት ያስፈልጋል። መንግሥት ለምርምር የሚመድበው በጀት አለ፤ ዩኒቨርሲቲዎችም በውስጥ አቅም ለሚሰሩት ምርምር በጀት ይመድባሉ። የዘርፉን ችግሮች በምርምርና ጥናት የመፍታቱ ሥራ በዚህ ብቻ የሚሸፈን አይደለም፤ ዩኒቨርሲቲዎች ለምርምርና ስልጠና በጀት መመደብ አለባቸው።
የሥራ ተቋራጮች፣ የአማካሪዎች የምህንድስና ሙያ ማህበራት ለኢንዱስትሪ ዩኒቨርስቲ / ሊንኬጅ/ መጎልበት የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ በስተቀር በዘርፉ የሚታየውን የጥራትና ተወዳዳሪነት ችግር መፍታት አይቻልም።
ሚኒስትር ዴኤታው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት ዜሮ የሚባል ዓይነት መሆኑንም ጠቅሰው፣ ኢንዱስትሪው እንደ ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚታይ አመልክተዋል። አማካሪዎች፣ ተቋራጮች ቴክኖሎጂዎችን ይታጠቁ የምንል ከሆነ ትልልቅ የፋይናንስ አቅም መፍጠርን ይጠይቃል ይላሉ።
የኢንዱስትሪውን የፋይናንስ ጥያቄ በፊሲካል ፖሊሲያችን በደንብ አይተን ዘርፉን የባንኮች አንዱ ቅድሚያ ስፍራ በማድረግ ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል ሲሉም አመልክተው፣ የውጭ ምንዛሬ ችግር የዘርፉ ማነቆ መሆኑ ታውቆ ስፋት ባለው መልኩ መታየት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳብራሩት፤ የሬጉላቶሪ አቅምንም መገንባት ያስፈልጋል። ባለፉት ሶስት አራት ዓመታት ተቋም የመገንባት ሥራዎች ተሰርተዋል፤ ተቋማትም ተፈጥረዋል፣ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ የኮንስትራክሽን ሬጉላቶሪ ፖሊሲ ወዘተን ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳሉ። የሬጉላቶሪ ተቋም የሚሰራበት የሕግ ማዕቀፍ የለም። የኮንስትራክሽን የኢንዱስትሪ አዋጅ እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎች የሚመሩበት የአሠራር ሥርዓት ሊኖር ይገባል።
ዘርፉን በአጠቃላይ መምራት የሚያስችሉ የአሠራር ሥርዓቶች፣ ማንዋሎች መመሪያዎች ያስፈልጋሉ። ይህን ከማድረግ አኳያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጣም ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። እንዲጸድቁ በማድረግ የዘርፉን ችግሮች ሥርዓት ባለው መልኩ በዘላቂነት ፈትቶ ዘርፉን ማሻገር የሚቻልበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።
በግዥ ላይ የሚታየውን ችግር መፍታት እንደሚያስፈልግም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል። አዋጅ የሚያጸድቀው ይሄ ምክር ቤት ነው። ኮንስትራክሽን የራሱ ባህሪ አለው። የዘርፉን ግዥ ማንኛውንም ሸቀጥ እንደምንገዛው የምናይ ከሆነ ዘርፉ ካለበት ችግር አይወጣም ሲሉ አስገንዝበዋል።
የዘርፉን የሕግ ማዕቀፎችን የግዥ የውልን በተመለከተ የሚመለከተው የኛ መሥሪያ ቤት ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሁሉም ነገር ተጠቅሎ እየሄደ ያለው ሌላ ቦታ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ ጉዳይ በምክር ቤቱም ታይቶ ወሳኝ ትኩረት የተሰጠበት ጉዳይ መሆኑን አስታውቀዋል። ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ እንዳይሆን በጉዳዩ ላይ በደንብ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው እንዳስታወቁት፤ መድረኩ ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ ያነቃቃል። ኢትዮጵያ በግንባታው ዘርፍ በጅምር ላይ ናት፤ ኮንስትራክሽን አሁንም አለ ወደፊትም ይቀጥላል። አድገናል በሚሉት ሀገሮችም ጭምር ኮንስትራክሽን ይቀጥላል።
ተግዳሮቶች አሉ፤ ከእነዚህ ተግዳሮቶች በስተጀርባ ደግሞ ችግር የሚወልዳቸው መልካም እድሎችም አሉ ያሉት ሚኒስትሯ፣ እኛ ስለ ሲሚንቶ፣ ብረትና ነዳጅ ውድነት እናወሳለን፤ ይህን እምናየው በተግዳሮት ነው፤ የእነዚህ ግብዓቶች እጥረት መከሰት እያደግን መሆናችንንም ያመለክታል ሲሉም ገልጸዋል።
መንግሥትም አሁን ለዘርፉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፣ ከታቀደው የብዝሀ ዘርፍ አካሄድ አኳያ ይህን እንደ ትልቅ እድል ተጠቅመን ተቀራርበን ለመሥራት እንድንችል ከሕግ አኳያ የተያያዙትን ጉዳዮች የተከበረው ምክር ቤት እንዲመለከታቸው ጠይቀዋል።
በመድረኩ የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ ሀገር በመግንባት ሂደት ትልቅ የማይተካ ሚና ባለው ዘርፍ ላይ ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፣ ቻይና በ1960ዎቹ አካባቢ የነበረችበት ሁኔታ አሁን እኛ ከነበርንበት የከፋ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም ሲሉም ጠቅሰዋል።
አቶ ተስፋዬ እንዳስታወቁት፤ በሀገሪቱ ብዙ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ይሠራሉ፤ በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ለውጦች ታይተዋል። ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ መንግሥትም ይገነዘባል፤ እስከ አሁን የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል በትኩረት ይሠራል። ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ አሁን ያሉ ተግዳሮቶችንም ማለፍ ይቻላል።
አካዳሚያና የምርምር ተቋማት የጥራትን የማስፈጸም አቅምን የፕሮጀክት ማኔጅመንትን፣ ክህሎትን፣ የማስፈጸም አቅምን በማሳደግ በኩል ጠንክረው ከሰሩ፣ በተቋራጮችና ባለሙያዎች በኩል የሀብት ብክነት እንዳይኖር ሙስናና ብልሹ አሠራርን የዋጋ ንረትና ሌሎች ችግሮች ተግዳሮቶቹን እንዳያባብሱ በጋራ መቆጣጠር የሚችሉ ከሆነ፣ ችግሮቹን ልክ እንደ ቻይና አሸንፎ መውጣት ይቻላል፤ ቻይና በ40 እና 50 ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ግዙፉን ቻይና ገንብታ አሁን አፍሪካን፣ አውሮፓን ዓለምን እየገነባች ነው። ይሄ የሆነው የሚመለከታቸው አካላት ብዙ ተግዳሮቶችን ተረድተው በተለየ ሀገር ግንባታ ላይ መሆናቸውን ተረድተው እውነት ይዘው በመሥራታቸው ነው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ‹‹ስለችግሮች ብቻ አውርተን መለያየት የለብንም፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉ የሠራው የሚታይ ሥራና ተስፋም አለ፤ ሥራው ስላለ ነው የምንነጋገረው፤ ለምሳሌ የግዥ ችግር የተፈጠረው ሥራውን እየሠራችሁ ባለበት ወቅት ነው›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
አፈ ጉባኤው በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ችግሮች እንዳሉም አመልክተዋል። ከግንባታ ጥራት፣ ከውሃና ከመንገድ ሥራዎች፣ ከዲዛይን፣ ከካሳ ክፍያ፣ ከጸጥታ፣ ከመዋቅር ከአሠራር ሥርዓት፣ ከሕግ ማዕቀፍ ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉ ሲሉም አብራርተዋል።
አፈ ጉባኤው እንዳሉት፤ በሥራ ውስጥ ያጋጠሙን ችግሮች እንዴት እንፍታ ነው ጥያቄው፤ ለእዚህ ደግሞ በምክር ቤቱ የአሠራር ሥርዓት መሠረት ቋሚ ኮሚቴዎች የምርምር ሥራዎች እንዲካሄዱ፣ ተመራማሪዎችን መጋበዝ እንዲችሉ የዚህ ዓይነት መድረኮችን እንዲፈጥሩ የምክር ቤቱ ደንብ ያዛል፤ በዚያ መነሻነት ነው ቋሚ ኮሚቴው ይህን መድረክ ያዘጋጀው።
ዛሬ እንደ አንድ ቤተሰብ ነው የምንነጋገረው፤ እኛ እንደ ሕግ አውጪ በቅርቡ በመንገዶች አፈጻጸም ላይ እዚህ ተወያይተናል፤ እየሠራን ነው፤ ተጨባጭ ለውጦችም እየተመዘገቡ ናቸው ሲሉም አመልክተው፤ ግን ደግሞ ለውጡ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድ፣ እናንተም ሥራችሁን ባግባቡ ሰርታችሁ የበለጠ ውጤታማ እንዳትሆኑ፣ ሀገሪቱም በፍጥነት እንዳትቀየር የሚያደርጉ ችግሮች መታየታቸውን ጠቅሰዋል። ከጸጥታ፣ ከካሳ ክፍያ፣ ክፍያ ከመፈጸም ጋር ባሉ ማነቆዎች ላይ ተነጋግረናል፤ እናውቃቸዋለን ብለዋል።
እኛም እንደ ሕግ አውጭ ማድረግ ያለብንን የሚያመላክቱ ነገሮች በመድረኩ በደንብ ቀርበዋል፤ በእነዚህ ላይ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር እንሠራለን ሲሉም ገልጸው፣ እናንተም ከሙያ ሥነ ምግባርና ከጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች ለመፍታት መሥራት ይኖርባችኋል ብለዋል። በተለይ የሙያ ማህበራት ይህን ጉዳይ በትኩረት መያዝ አለባችሁ ሲሉም አስገንዝበዋል።
‹‹በመነጋገር የመንግሥትን ችግር እናንተም ትረዳላችሁ፤ የእናንተንም ችግር መንግሥት ይረዳል። በዚህም ችግሩን እየፈታን እንሄዳለን። በእናንተ በኩል ያለውን በዚያ መልኩ ያዙ›› ሲሉም አስገንዝበዋል ።
እሳቸው እንዳብራሩት፣ ሁሉም የምህንድስናው ባለሙያ፤ ሥነ ምግባር፣ የሕግ ማዕቀፎች ያስፈልጋሉ፤ ስታንዳርዶች መሻሻል አለባቸው። የፋይናንስ፣ የብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት ሊኖር ይገባል፤ ግዥ ሕጉ ይህን ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል፤ መተማመንና ተጠያቂነት ያስፈልጋሉ።
‹‹እኛም እንደ መንግሥት እንደ ሕግ አውጪ መያዝ ያለብንን እንይዛለን፤ አስፈጻሚውም እንደ አስፈጻሚ መያዝ ያለበትን ይይዛል። የኛ ቋሚ ኮሚቴም ክትትል ያደርጋል፤ እናንተም በማህበራችሁ በኩል ማድረግ ባለባችሁ ላይ ተነጋገሩ፤ በዚህም ይህን የጋራ ችግራችንን እንፈታለን›› በማለት አስገንዝበዋል።
ኃይሉ ሳህለድንግል
አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም