አሜሪካዊቷ ለሰሜን ኮሪያዊያን ‘ሪሞት’ሥራ በመስጠት ደመወዝ እንዲከፈላቸው በማድረጓ ክስ ቀረበባት

የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ሕግ አንዲት አሜሪካዊት ለሰሜን ኮሪያዊያን የርቀት ሥራ እየፈለገች ደመወዛቸውን ሰሜን ኮሪያ ስትልክላቸው ነበር ሲል ከሷል። ክሪስቲና ቻፕማን የተሰኘችው ግለሰብ እና ሌሎች ሰሜን ኮሪያዊያን የድርጊቱ ተሳታፊ በመሆናቸው ክስ ቀርቦባቸዋል።

ነዋሪነቷ አሪዞና የሆነው ግለሰቧ የአሜሪካ ዜጎችን ማንነት እየሰረቀች ለውጭ ሀገር የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ትሰጥ ነበር፤ ሰዎች ደግሞ እኒህ ማንነቶችን ተጠቅመው አሜሪካዊ መስለው በአሜሪካ ኩባንያዎች ይቀጠሩ ነበር ይላል የአቃቤ ሕግ መዝገብ።

ክሪስቲና በዘጠኝ የተለያዩ መዝገቦች የአሜሪካ መንግሥት ለማራቆት ሠርታለች የሚል ክስ ቀርቦባታል። አቃቤ ሕግ እንዳለው በማጭበርበር ሂደቱ የ60 ሰዎች ማንነት የተሰረቀ ሲሆን 7 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ ወደ ሰሜን ኮሪያ ተልኳል፤ ይህ ገንዘብ ሀገሪቱ ለምታካሂደው የጦር መሣሪያ ፕሮግራም ጥቅም ላይ ውሎ ሊሆን ይችላል።

300 የአሜሪካ ኩባንያዎች ስማቸው የተጠቀሰበት ይህ የማጭበርበር ሂደት በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2020 ነው የጀመረው የሚለው የክስ መዝገቡ “ሠራተኞች እጅግ የተካኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ናቸው” ይላል። ስለማጭበርበሩ የማያውቁት ኩባንያዎች ተጭበርብረው እንደሆነ እስካሁን ያልተነገራቸው ቢሆንም፤ አብዛኛዎቹ በጣም ግዙፍ የሚባሉ ድርጅቶች እና የቴሌቪዥን ኔትዎርኮች እንዳሉበት፤ እንዲሁም አንድ የግል ወታደራዊ ተቋም እና ታዋቂ የመኪና አምራች እንደሚገኝበት ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

የ49 ዓመቷ ክሪስቲና ከቤቷ ሆና የኮምፒውተር “እርሻ” በመዘርጋት ከኩባንያዎቹ የተሰጡ ላፕቶፖችን በመክፈት ሰሜን ኮሪያዊያኑ ሠራተኞች ልክ አሜሪካ ያሉ በማስመሰል ትሠራ ነበር ተብላለች። 57 ገፆች ያሉት የክስ መዝገብ እንደሚተነትነው ግለሰቧ የአይቲ ሠራተኞች ካሉበት ሆነው ከላፕቶፖቹ እንዲገናኙ በማድረግ ከኩባንያዎቹ ደመወዝ እንዲቀበሉ ታደርግ ነበር።

መዝገቡ አክሎ እንደሚገልጸው፤ ግለሰቧ ለዚህ ሥራዋ “በየወሩ ከአይቲ ሠራተኞቹ ወርሃዊ ክፍያ የምትቀበል ሲሆን፤ ከማጭበርበር ሂደቱ ስታተርፍም ነበር።ይሄ ክስ ከቤታቸው ሆነው የአይቲ ሥራ የሚሠሩ ሰዎችን ለሚቀጥሩ ኩባንያዎችና የመንግሥት ኤጀንሲዎች የማንቂያ ደወል ነው” ያሉት የፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ክፍል ኃላፊ ኒኮል አርጀንቲዬሪ ናቸው።

“እኒህ ወንጀሎች የሰሜን ኮሪያን መንግሥት ጠቅመዋል፤ የገቢ ምንጭ ሆነዋል፤ በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ አስፈላጊ መረጃዎች እንዲሾልኩ አድርገዋል” ሲሉ አክለዋል። ባለሥልጣናት እንደሚሉት፤ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2020 ነው ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ክሪስቲና ቀርበው የኩባንያቸው “የአሜሪካ ተወካይ” እንድትሆን የጠየቋት።

ክሪስቲና ሰሜን ኮሪያዊ ዜግነት ካላቸው ጂሆ ሀን፣ ቹንጂ ጂን እና ሀዋራን ዡ ጋር የተከሰሰች ሲሆን፤ ሰሜን ኮሪያዊያኑ እስካሁን በቁጥጥር ሥር አልዋሉም። የአሜሪካ የፍትሕ ሚኒስቴር እንደሚለው፤ ሦስቱ ግለሰቦች ከሰሜን ኮሪያው መሥሪያ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ ይህ ተቋም ባለስቲክ ሚሳዔል እና የጦር መሣሪያ ምርትን የሚቆጣጠር ነው።

ሚኒስቴሩ፤ የሰሜን ኮሪያን ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና የፋይናንስ ማጭበርበርን በተመለከተ “መረጃ ለሚያቀብሉ” ሰዎች የ5 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ ለመክፈል ተዘጋጅቷል። ክሪስቲና በቁጥጥር ሥር የዋለችው ባለፈው ሐሙስ አሪዞና ውስጥ ሲሆን፤ የሚወክላት ጠበቃ ስለመቅጠሯ እስካሁን ግልፅ መረጃ የለም ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You