አዲስ አበባ፡– በሻሸመኔ ከተማ ውብና ሳቢ ማድረግ የሚያስችል የኮሪደር ልማት ሥራ መጀመሩን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አስታወቁ።
የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ አዳነ ተክለጊዮርጊስ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የአዲስ አበባ ከተማን ተሞክሮ በመውሰድ በሻሸመኔ በ65 ሚሊዮን ብር በጀት የኮሪደር ልማት ሥራ ተጀምሯል።
ለኮሪደር ልማቱ ከማህበረሰቡና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ጠቁመው፤ ሁለት ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ የማስፋት እንዲሁም የኮሪደር ልማትና ውበት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ዋናውን የአስፓልት መንገድ በ14ሜትር የማስፋት እና የእግረኛውን መንገድ በግራና በቀኝ በ18 ሜትር እንዲሰፋ መደረጉንም አስረድተዋል።
በአጠቃላይ የመንገድ ስፋቱ 50 ሜትር ያለው ሲሆን፤ መንገድ ዳር የተለያዩ አረንጓዴ ውበቶችና መብራቶች እንደሚዘጋጁ አመላክተዋል።
በመንገድ ማስፋት ስራው 238 የተለያዩ የንግድ ቤቶች በፈቃደኝነት ከዋናው መንገድ ተነስተው ወደ ውስጥ ገባ እንዲሉ ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ አዳነ እንደተናገሩት፤ የኮሪደር ልማት ሥራው ከተጀመረ ሁለት ወር ሆኖታል። አሁን ላይ የንግድ ቤቶችን የማስነሳት ሥራ በስፋት እየተሠራ ይገኛል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የከተማው ነዋሪ የመኖሪያ አካባቢውን እንዲያለማና ጽዱ እንዲያደርግ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመው፤ የንቅናቄና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
አቶ አዳነ እንዳመላከቱት፤ የኮሪደር ልማት ሥራው ከመጀመሩ አስቀድሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አማካኝነት በአዲስ አበባ ከተማ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በመጎብኘት ልምድ ተወስዷል።
በዚህም በአዲስ አበባ እየተሠሩ ያለውን መልካም ተግባር በመውሰድ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ያሉት ከንቲባው፤ የልማት ሥራው ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።
አሁን እየተሠራ ላላው የኮሪደር ልማት 65 ሚሊዮን ብር የተበጀተ ሲሆን፤ በቀጣይም በተለያዩ ክፍለ ከተማዎች የኮሪደር ልማቱ እንዲስፋፋ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል። ለዚህም በመንግሥት በጀት ብቻ ኅብረተሰቡን የማሳተፍ ሥራ ይሠራል ብለዋል።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም