ምክረ ሃሳቡ በብዙ ፈተናዎች የተሻገርናቸውን ትናንቶች ታሳቢ ያደረገ አይደለም!

በአንድ ሀገር /ማኅበረሰብ ውስጥ የሚደረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ በብዙ ፍላጎት በተሞሉ ቡድኖች፣ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የምክረ አገልግሎት እውን የሚሆን አይደለም። የሥርዓቱን ግንባታ ሆነ የመብቶቹ ጥበቃ ተግባራዊ የሚሆነው ሀገራቱ እና ሕዝቦቻቸው ለጉዳዩ ባላቸው መረዳት እና መረዳቱ ሊፈጥር በሚችለው ቁርጠኝነት ነው። ከዚህ ውጭ ከባለጉዳዩ በላይ ስለ ጉዳዩ ተቆርቋሪ ሆኖ ለመገኘት የሚደረጉ ሙከራዎች ተቀባይነት ሊኖራቸው የሚችሉ አይደሉም።

የዲሞክራሲ እና በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አጀንዳዎች፤ የአንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች እና ሀገራት የፖለቲካ ፍላጎቶች ማስፈጸሚያ ስትራቴጂክ ትርክት ተደርጎ በሚወሰድበት፤ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ምስቅልቅሎች እየተፈጠሩ ባለበት ሁኔታ፤ ትርክቶቹ ትናንት ላይ ከፈጠሩት ጥፋት ተምረን በኃላፊነት መንገድ መንቀሳቀስ ካልተቻለ፣ ችግሩ ዓለምን ለተጨማሪ ምስቅልቅል ከመዳረግ ባለፈ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም፡፡

በራሳቸው ጊዜ ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ ተረድተው የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባትም ሆነ ለሰብዓዊ መብቶች የተሻለ ጥበቃ ለማድረግ ከፍ ባለ መነቃቃት ውስጥ የሚገኙ ሀገራትንና ሕዝቦችን፤ ተመሳሳይ ቋንቋ እየተናገሩ ከጀመሩት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማደናቀፍ የሚደረግ የትኛውም ዓይነት ጥረት/ ሴራ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለመገንባት ለሚሞክረው አዲስ የዓለም ሥርዓት ትልቅ ተግዳሮት ነው።

በተለይም ለዴሞክራሲም ሆነ ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዓለም አቀፍ ፖሊስ ነን ብለው የሚያስቡ መንግሥታት ፤ ከሁሉም በላይ ሀገራት የራሳቸውን ተጨባጭ እውነታ ታሳቢ ባደረገ መንገድ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት፤ ከቋንቋ ባለፈ በተጨባጭ መደገፍ፤ የሕዝቦቻቸው ፍላጎት ማክበር፤ ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ እገዛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ማድረግ ከሞራል ሆነ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ግዴታቸውም ነው።

እነዚህ መንግሥታት በቀደሙት ጊዜያት፤ የሕዝቦች የለውጥ መሻት የፈጠራቸው የለውጥ ንቅናቄዎች በአግባቡ እና ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ መደገፍ ባለመቻላቸው ዛሬ ላይ ከፍ ባለ የሕዝቦች መነቃቃት ተጀምረው ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደህንነት የስጋት ምንጭ፤ ከሁሉም በላይ ለሕዝቦቻቸው የከፋ መከራ እና ስቃይ ምክንያት የሆኑ የለውጥ መሻቶች ጥቂት አይደሉም። ለዚህም ሊቢያን ፣ ሶሪያን ፣ የመንን … ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።

የእነዚህ ሀገራት ሕዝቦች ዛሬም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ የተለያዩ ፍላጎቶች ምክንያት የተመኙትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመገንባት ይልቅ፣ በየትኛውም መንገድ ሊያስቡት ለማይችሉት ያልተገባ መከራ እና ስቃይ ተዳርገዋል። ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ለመቆም በዋነኝነት ያጡትን ሰላም ለማጽናት እንኳን ሁሉም ነገር ከእጃቸው መጥቶ፣ እንደ ሀገር የመኖር ህልውናቸው በሌሎች የጥቅም ፍላጎት እጅ ወድቋል።

ለነዚህ ሀገራት ሕዝቦች በዓለም አቀፍ አደባባዮች ስለ ዲሞክራሲ እና ስለ ሰብዓዊ መብቶች የሚደረጉ ዲስኩሮች ትርጓሜ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመረዳት የሚከብድ አይደለም። ከዲስኩሮቹ በስተጀርባ ያሉ ፍላጎቶች እና ፍላጎቶቹን ለማስፈፀም፣ ተስፈኞች ሊከፍሉት የሚገደዱት ያልተገባ ዋጋ የቱን ያህል መራራ እንደሆነም እየኖሩት ስላሉ ለእነሱ የተሰወረ አይደለም።

በኛም ሀገር መላው ሕዝባችን በብዙ ተስፋ ወደ ለውጥ ከመጣ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል። በነዚህ ዓመታት እንደ ሀገር የሄድንበት የለውጥ መንገድ የቱን ያህል ፈታኝ እንደነበር ፣ እንደ ሀገር የነበረንን ዘመናት ያስቆጠረ ህልውና ምን ያህል እንደተፈታተነው የአደባባይ ሚስጥር ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ለለውጡ ጉልበት ይሆኑናል ያልናቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለዴሞክራሲ እና ስለሰብዓዊ መብቶች ከፍ ባለ ድምፅ የሚናገሩ መንግሥታት ሳይቀሩ ለውጡን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት፣ ስለ ተስፋችን እንደ ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል አድርገውናል።

እነዚህ መንግሥታት ስለዴሞክራሲ እና ስለዴሞክራያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ስለሰብዓዊ መብቶች እና ስለመብቶቹ ጥበቃ በሚደረጉ ዲስኩሮች አደባባዮችን ሞልተው፣ የጀመርነውን የሥርዓቱን ግንባታም ሆነ የመብቶቹን ጥበቃ የሚፈታተኑ ፣ የሕዝባችንን ልብ በብዙ የሰበሩ ተግባራት በአደባባይ ሲከናወኑ እንዳላዩ እና እንዳልሰሙ ሆነዋል። ጎራ ለይተው ከድርጊቶቹ ፈጻሚዎችም ጋር አንድ ቋንቋ ሲናገሩ ተስተውለዋል። በለውጡ ላይ ዓለም አቀፍ ጫናዎች እንዲበራከቱ በስፋት ሠርተዋል።

በተለያዩ ጽንፈኛ አስተሳሰብ የተገሩ ኃይሎች ጠብመንጃ አንስተው ሕዝባችንን ለሞት ለእንግልት ሲዳርጉ፣ የለውጥ ተስፋውን በጽልመት ለመሸፈን ሲሞክሩ፣ ባህር ማዶ ተቀምጠው ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሱ፣ የሰውን ልጅ መሠረታዊ የመኖር መብት የሚቃረኑ የጥላቻ እና የጥፋት ትርክቶችን ሲተርኩ እንዳላየና እንዳልሰማ ሆነዋል።

ይህ የአደባባይ ሚስጥር በሆነበት፣ እንደ ሀገር የጀመርነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ሆነ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ንቅናቄ ዋነኛ ሀገራዊ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ፣ ከትናንት የተሻለ ዛሬ ላይ በምንገኝበት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር፣ የተሰጠው ምክረ ሃሳብ ሉዓላዊነትን ታሳቢ ያላደረገ እና በብዙ ፈተናዎች የተሻገርናቸውን ትናንቶች ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም።

ለጀመርነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላለፉት አምስት ዓመታት እንደ ሀገር /ሕዝብ የከፈልናቸውን መጠነ ሰፊ ዋጋ አሳንሶ የሚመለከት፣ የሕዝባችንን የሰላም፣ የዴሞክራሲ እና የልማት መሻት ያላገናዘበ ነው፣ በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ለ120 ዓመታት የቆየውን ግንኙነትም የሚመጥን አይደለም!

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You