ከመልሶ ልማቱም የላቀው የኮሪደር ልማት

አዲስ አበባ እንደ ስሟ አለመሆኗ ሁሌም ይገለጻል። በርግጥም እንደ ስሟ አይደለችም፤ አንዱ ጋ ጥሩ ሲታይ ሌላው ጋ ሲደርስ ጥሩ አይታይባትም። ጥሩ ያልሆነው ደግሞ ይበዛል።

የአዲስ አበባን እንደ ስሟ አለመሆኗን በከተማዋ ተወልደው ያደጉትም፣ ከተማዋን ቆይተው የተቀላቀሉትም፣ በተለያዩ የሥራና የመሳሰሉት ጉዳዮች ወደ ከተማዋ የገቡ የወጡትም፣ በውጭ ሀገሮች ለአያሌ ዓመታት ቆይተው የመጡትም ይረዱታል።

ከተማዋ ነዋሪዎቿን በሚገባ የሚያስተናግዱ መሠረተ ልማቶችና አገልግሎቶች የተጠማች፣ የተራበች ናት። ሰፋፊ ነባር መንደሮቿ ጣሪያዎች፣ ግድግዳዎች፣ መውጫ መግቢያ መንገዶች፣ የመኖሪያ ቤቶችና መንደሮች በእጅጉ የተጎሳቆሉ መሆናቸውን ይመሰክራሉ።

ከእነዚህ መንደሮች አብዛኞቹ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ያልዞረባቸው በመሆናቸው ለጎርፍ መውረጃ የተሠሩ ቱቦዎች፣ ክፍት ሥፍራዎች፣ ወዘተ ሁሉ የቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ ተደርገውባት አያሌ ዓመታትን ቆይታለች። ወንዞች በአቅራቢያቸው የሚያልፉ ጥቂት የማይባሉ መኖሪያ ቤቶች የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽም በተለይ በክረምት ወቅት በሞተር እየተሳበ ጭምር ወደ ወንዞቿ ይለቀቃል።

ይህች ለሀገሪቱ ከተሞች ሁሉ ሞዴል መሆን ያለባት ከተማ የረባ መጸዳጃ ቤቶች ሳይኖሯት ዘመናትን አሳልፋለች። አብዛኞቹ መኖሪያ ቤቶች የእኔ የሚሉት መጸዳጃ ቤቶች የሌላቸው በመሆናቸው ክፍት ቦታዎች የወንዝ ዳርቻዎች ሁሉ የመጸዳጃ ቦታዎች ተደርገው ኖረዋል። ይህን የተገነዘቡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምስጋና ይገባቸውና የጋራ መጸዳጃ ቤት እየተገነቡ በርካታዎችን ባለመጸዳጃ ቤት አድርገዋል። ይህ ባይሆን ከተማዋ ምን ያህል በአሳፋሪ ቁመና ላይ ልትገኝ ትችል እንደነበር መገመት አይከብድም። የውስጥ ለውስጥ መንገዶች አንዴ ኮረኮንች፣ ሌላ ጊዜ ኬር፣ ከዚያ ደግሞ ኮብልስቶን እየለበሱ ከሰለጠኑት የከተማዋ አካባቢዎች ኋላ ኋላ እየተከተሉ ኖረዋል።

ይህን የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር ላለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት በከተማዋ ስለመልሶ ልማት ሲወራባት ቆይቷል፤ ከወሬም አልፎ ብዙም ተሰርቷል። በዚህም በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿ የተሻሻለ ሕይወት መምራት ወደሚቻልባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንዲገቡ ተደርገዋል፤ ሌሎች ባለይዞታዎች ደግሞ መሬትና ካሳ እየተሰጣቸው ወደ ከተማዋ ዳርቻዎች ገብተዋል። በተለቀቁ ቦታዎች ላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ አረንጓዴ ሥፍራዎች ሪልስቴቶች፣ የገበያ ማዕከላት ለምተዋል።

ይሁንና ችግሯ ዘመናትን ተሻግሮ እዚህ የደረሰ ሆነና ቢፈቱት ቢፈቱት አላልቅ ብሎ አሁንም ወደ ግዙፍ መልሶ ልማት ተግባር ገብታለች። እስከ ቅርብ ጊዜ በመልሶ ልማቱ የተከናወነው ተግባር ከተማዋ መልማት ከሚጠበቅባት አኳያ ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል ሆኖ አልተገኘም።

ገና ብዙ መልማት ይጠበቅባታል። ነባር መንደሮቿ ብቻም ሳይሆኑ ለሙ የተባሉት የከተማዋ አካባቢዎችም ተጨማሪ ልማት የሚፈልጉ ናቸው። የልማት ተነሽዎች የገቡባቸው ሰፈሮችን የተመለከቱ አንድ የከተማ ልማት ባለሙያ የተካሄደው መልሶ ልማት በቀጣይም መልሶ ልማት የማይካሄድበት ስለመሆኑ እንደሚጠራጠሩ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ደረጃውን የጠበቀ ልማት አልተካሄደም ነው አስተያየታቸው። የማያመላልስ ልማት እናካሄድ ነው ሃሳባቸው። ይህን ሃሳብ እኔም እጋራዋለሁ።

አሁን እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን የደከሙ መንደሮች ብቻ የሚመለከት አይደለም። የለሙ የምናላቸው እነቦሌም በልማቱ ታቅፈዋል። ከዚህ መረዳት የሚቻለው መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መልሶ ልማት በኮሪደር ልማቱ እየተካሄደ መሆኑን ነው።

የኮሪደር ልማቱ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ስለመሆኑ አያያዙ ያመለክታል። ነባሮቹን መንደሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማንሳት የተለቀቀው ቦታም እንደ እስከ አሁኑ መልሶ ልማት ዳዋ ሳይለብስ ወዲያውኑ ወደ መልሶ ልማቱ ተገብቷል። ለልማቱ ደንቃራ ይሆናሉ ያላቸውን ሕንፃዎች አንስቷል፤ ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ ከተማ በመኖሪያ ቤት፣ በመሥሪያ ቦታ እጥረት የምትሰቃይ ሆናም ነው። ልማቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ለልማቱ ደንቃራ የሚሆነውን እያስወገዱ ልማቱ አቅፎ የሚያሻሻላቸውን ሕንፃዎች እየቀፉ መሥራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት ነው፤ አራት ኪሎን ለእዚህ ማሳያ ትሆናለች።

በኮሪደር ልማቱ አንዳንድ አካባቢዎች መንገዶች በአዲስ መልክ እየተቀየሱና እየተገነቡ ናቸው፤ በሌሎቹ ደግሞ የእግረኛ መንገዶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው። ጎን ለጎንም እንደ ኤሌክትሪክ፣ ውሃ፣ ፍሳሽ ማስወገጃ፣ ቴሌኮም ወዘተ ያሉት መስመሮች እየተገነቡ ናቸው። በግሉ ዘርፍ የሚለሙ ቦታዎች ተለይተው ጨረታ ወጥቶባቸዋል። በኮሪደር ልማቱ የሚገኙ የግልም ሆኑ የመንግሥትና የሌሎች ድርጅቶች ሕንፃዎች በልማቱ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ማሟላት ያለባቸውን እንዲያሟሉ እየተደረጉ ናቸው። ሕንፃዎቹ መሠረታዊ የእድሳት ሥራ ውስጥ ገብተዋል።

እኛም በኮሪደር ልማቱ አዲስ አስተሳሰብ እየተመለከትን ነው። በከተማዋ ለመልሶ ልማት በርካታ ቦታዎች ከዓመታት በፊት ጽደተው ብዙም የረባ ነገር ሳይሰራባቸው ዓመታት መቆየታቸው ይታወቃል። ያን ዓይነቱን የመልሶ ልማት መንገድ የኮሪደር ልማቱ ሽሮታል። በእዚህ የኮሪደር ልማት በፒያሳ፣ እሪ በከንቱ፣ አራት ኪሎ ድረስ እየተካሄደ ካለው ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ መንገዶች ግንባታ፣ የሕንፃዎች እድሳት፣ አያስፈልጉም የተባሉ መኖሪያ ቤቶችና ሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጥባቸው በርካታ ሕንፃዎች እንዲፍረሱ የተደረገበትና ሌሎች የልማት ሥራዎች እየተካሄዱ ካለበት ሁኔታ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው።

ከተማዋ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብቻ አይደለችም። የዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት መቀመጫ ናት፤ በእዚህ ደረጃ ላይ የምትገኝ ከተማ ዲፕሎማቶቿን፣ በተለያዩ አህጉራዊ ጉዳዮች የሚመጡ የሀገሮች መሪዎችንና ከፍተኛ ባለስልጣናትን እንዲሁም የግዙፍ ተቋማት መሪዎችንና ቅርንጫፎቻቸውን ምቾት የምትጠብቅ፣ ገብተው በመጡበት ፍጥነት ጥለዋት የማይወጧት ውለው የሚያደሩባት የሚሰነብቱባት ከተማ መሆን ይኖርባታል። አሁን እየተካሄደ ያለው ልማት ይህን የሚመጥን ነው።

የኮሪደር ልማቱ ከእስከ አሁኑ መልሶ ልማት በእጅጉ ይለያል። በከተማዋ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችልና ከተማዋን ከስሟ ጋር የሚያገናኝ ብቻ አይደለም፤ አህገራዊና ዓለም አቀፋዊ መልክ እንዲኖራት የሚያስችል።

የልማቱም ፍጥነት በልዩ ሊታይ ይገባዋል። 24 ሰዓትና ሰባት ቀናት በሚካሄደው ልማት በሁለት ወር የተከናወነው ተግባር አፈጻጸም ከፍተኛ መሆን አንድ ፕሮጀክት መጨረስ ምጥ ሆኖባት በቆየች ሀገርና ከተማ መታየት መቻሉ በራሱ በልዩ ሁኔታ ሊታይና ተሞክሮ ተወስዶበት ሊሰራ ይገባል። እንዴት ተደርጎ ቢሰራ በፕሮጀክቶች ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል እንደ ግዙፍ ፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ሁሉ በዚህም ፕሮጀክት ማየት ተችሏል። ትልቅ ነገር ነው።

ከተማዋ የለሙ የተለያዩ አካባቢዎች እንዳሏት ቢታወቅም፣ የዘመኑ አቻ ከተሞች ያሉበት ደረጃ ላይ ትገኛለች ተብሎ አይወሰድም። ልማቱ ወጣ ገባ የሚልና ሰፊ አካባቢን ያልሸፈነ እንደመሆኑ አንዴ ጥሩ መንደር ሌላ ጊዜ የከረፋ የሚታይባት ሆና ኖራለች። ይህችን ከተማ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ አምነው ወደ ርምጃ የገቡት የፌዴራል መንግሥቱንና ከተማዋን የሚያስተዳደሩ አካላትን ማመስገን ይገባል።

ማመስገን ጥሩ ነገር ነው፤ አሁን እየተከናወነ ያለው ተግባር በማመስገን ብቻ የሚቆም ግን መሆን የለበትም። ከዚህም ተሻጋሪ መሆን ይኖርበታል፤ የልማቱ ተባባሪ የሆኑ አካላትንም ያስገኘ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። እዚህ ላይ ለልማቱ ሲባል ከአካባቢው የተነሱቱ የከተማዋ ነዋሪዎች ኮንደሚኒየምም አገኙ የቀበሌ ቤት፣ ካሳም ተቀበሉ ቦታ ወሰዱ ለቀው ከሄዱበት አካባቢ ተፈላጊነት አኳያ ሲታይ መንግሥት እያካሄደ ላለው የኮሪደር ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋልና በእጅጉ የሚመሰገኑ ከመሆናቸው በተጨማሪ የልማቱ ባለድርሻዎች ሊባሉም ይገባቸዋል።

ከዚህ ንግድ በእጅጉ ከደራበት አካባቢ የተነሱ ነጋዴዎች ንግዳቸው ተስተጓጉሎባቸዋል፤ በእዚህ ኮሪደር ለሥራም ይሁን ለተለያዩ ተግባሮች የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ተዟዙረው ሊሄዱ ተገደዋል፤ ይህም ለወጪ፣ ለድካም እየዳረጋቸው ይገኛል። ሁሉም ወገኖች ይህን ሁሉ ችለው ልማቱ እንዲቀላጠፍ እድል ሰጥተዋልና ሊመሰገኑ የሚገባቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ የልማቱ ባለቤትም ናቸውና ሊኮሩም ይገባቸዋል። ልማቱ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የእነዚህ ሁሉ ወገኖችም ጭምር ነው።

ልማቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል። ይህን ታላቅ ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲጠናቀቅ የሁሉም ወገኖች ተባባሪነት ያስፈልጋል። ሥራው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እየተፈጸመ ነው። በሁለት ወር ውስጥ የሚያስገርም አፈጻጸም ታይቷል። ይህ አያያዝ ፕሮጀክቱን የሚመሩ አካላት በተደጋጋሚ እንዳረጋገጡት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይጠናቀቃል። አያያዙም ይህንኑ ያረጋግጣል።

 

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

እስመ ለዓለም

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You