የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለትንሳዔ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፡- የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለትንሳዔ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለትንሳዔ በዓል ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ የትንሳዔ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ በመስቀል ላይ እስከሞት ድረስ ራሱን አሳልፎ በመስጠት ወደር የለሽ ፅኑ ፍቅር ያሳየበት እና እንዲሁም ለበደሉት ሳይቀር ይቅርታና ምህረትን የሰጠበት፣ ሞትንም ድል ያደረገበት መታሰቢያ በዓል ነው።

እኛም እርስ በርሳችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሁሉንም ሰው በመውደድ፣ በይቅርታ፣ በምህረትና በመረዳዳት እንድንኖር ፈጣሪ ይርዳን። በዚህ በኩል ለተዳከሙ እሴቶቻችንም ትንሳዔ ይሁን ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በትንሳዔ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ስለብዙዎች ቤዛ ሆኖ ሞትንም ድል አድርጎ በመነሳቱ ለሠው ልጆች ፍቅርን፣ እርስ በርስ መዋደድን፣ ሠላምና ለነፃነት ራስን መስዋዕት መሆንን ቤዛና አብነት ሆኖ አሳይቶናል።

በዓሉ ሲከበር በታላቁ መጽሐፍ እንደታዘዘው ሁሉም ሰው ልቦናውን ለምህረት፣ ለይቅርታና ለእርቅ በማዘጋጀት በልዩ ልዩ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማገዝ እጆቻችንን ለድጋፍ በመዘርጋት ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የትንሣኤ በዓል ባስተላለፉት መልዕክት ላይ እንደገለጹት፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተቀደሰ ሕይወት ምልክትና በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠን ውድ ስጦታ ተደርጎ እንደሚታመን ገልጸዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የሔደበትን መንገድ፣ ያሳየንን ፍቅር እና ሰላም፣ ዝቅ ብሎ ያገለገለበትን ትህትና፣ በፍቅር እና በትዕግሥት መቻቻልን እንዲሁም ሁሉንም ሰው ማክበርን የመሳሰሉ ምሳሌዎቹን መከተል ከሁላችንም ይጠበቃል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው ያለፉት የፆምና የፀሎት ጊዜያት በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ መንፈሳዊ ሕይወትን በማደስ ፈሪሃ እግዚአብሔርን የተላበሰ ስብዕና እንዲሁም ሞራላዊ እሴትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና የተጫወቱ ናቸው ብለዋል።

በፆሙ ጊዜያት የጎለበቱት መልካም ተግባራት የአብሮነትን ድልድይ የሚያጠናክሩና መልካምነትን የሚያላብሱ፣ በመሆናቸው የዘወትር የተግባር መርሆዎች ሆነው እንዲቀጥሉ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የትንሳዔን በዓል ስናከብር የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህላችንን በማጠናከር መሆን እንዳለበት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ገልጸዋል። ከንቲባ ከድር ለትንሳዔ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የትንሳዔ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን ፅኑ ፍቅር በመስቀል ላይ ያሳየበት እንዲሁም ይቅርታና ምህረትን ለሰው ልጆች የሰጠበት የጥልና የመለያየት ግድግዳን አፍርሶ የሰውን ልጅ የታደገበት ነው፡፡

የትንሳዔ በዓል መታዘዝን፣ ይቅርታንና ምህረትን እንዲሁም አንዱ ለሌላው መተሳሰብ እንዳለበት የሚያስተምረን ሲሆን መረዳዳትንና መጠያየቅን ከተለመደው ባህል ባለፈ በፍጹም መንፈሳዊነት በጎዳና የወደቁትን በማሰብ፣ በሕግ ጥላ ስር ያሉትን በመጠየቅ፣ታመው የተኙትን በማጽናናት በማካፈል በአብሮነት ማክበር ይገባል ብለዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው የትንሳዔ በዓል በክርስትና እምነት ጥልቅ ትርጉም ያለው፤ ክርስቶስ የአዳምን ዘር ከበደል ቀንበር ነፃ ያወጣበት፤ ለሰው ልጆች ምሕረትና ድኅነት፤ ሰላምና ፍቅር የተገኘበት ነው፡፡

ትንሣዔ የጽናት፤ የተስፋና የድል በዓል በመሆኑ በዓሉ ሲከበርም በየወቅቱ የሚገጥሙ ጊዜያዊና ተለዋዋጭ ፈተናዎች በፅናት በማለፍ ለቀጣይ ድል መብቃት እንደሚቻል በማሰብ ሊሆን ይገባል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው የትንሳዔ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆች ሃጢአትና በደል በመሻር በቀራንዮ መስቀል ነብሱን እስከ መስጠት ለሰው ልጆች መስዋዕት የሆነበት በመሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ሆኖ በተግባር ባሳየን ትህትናና ፍቅር መሠረት ከግላዊ ጥቅምና ፍላጎት በመላቀቅ እርስ በእርስ በመተጋገዝና በመተሳሰብ ሕዝባዊ ጥቅምን ማስቀደም እንዲሁም ለችግሮችና ለፈተናዎች ሳንበገር የሀገሪቱን የብልፅግና ትንሳዔ ማፋጠን ያስፈልጋል ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው የትንሣዔ በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የሠውን ልጅ ለማዳን መከራ ተቀብሎ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ሞቶ መነሣቱን በመዘከር የሚያከብሩት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ኃይማኖታዊ አስተምህሮውን በመከተል በሀገራችን ያለው የመከባበር፣ የአብሮነትና የመረዳዳት መልካም እሴት የበለጠ እንዲጎለብት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ህዝበ ክርስቲያኑ በአብይ ጾም ወቅት ሲያደርጓቸው የነበሩትን የመደጋገፍና የመተዛዘን ተግባራት ከጾም ፍቺም በኋላ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You