‹‹ የተረከብናቸውን ድሎች ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር ስሜት ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል››ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚደንት

አዲስ አበባ፡ካለፈው ትውልድ የተረከብናቸውን ድሎች ተገቢ ክብር በመስጠት፣ ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር ስሜት እና አንድነት ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚደንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ገለጹ።

ልጅ ዳንኤል ጆቴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዘንድሮ ለ83ኛ ጊዜ የሚከበረው የድል በዓል የኢትዮጵያ አርበኞች ከአምስት ዓመታት ውጊያ በኋላ የኢጣሊያን ወራሪ ጦር ድል በማድረግ በሀገር ጉዳይ የማይደራደሩ እና መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጁ መሆናቸው መልእክት የተላለፈበት ነው።

በዓሉ የድል እንጂ የነፃነት ቀን አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የቀድሞ ትውልድ መልካም ሥነምግባር የተላበሰ፣ ሃይማኖት ያለው፣ ስለሀገሩ ታሪክ የሚያውቅና የሚመራመር፣ የጎረቤት ሀገሮችን ሁኔታ የሚገነዘብ እና ሊኖር የሚችለውንም ችግር አውቆ ለሀገር ሰላም መስፈንና አንድነት በተጠንቀቅ የሚቆም ሕዝብ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህንን መልካም ተግባር የአሁኑ ትውልድ ከታሪክ በማንበብና በመስማት የቀድሞ አባቶችና አያቶቹ ሲሰሩ የነበሩትን ታሪክ የሚደግም ሊሆን እንደሚገባውም አመልክተዋል።

አሁን ያለው ትውልድ በትምህርትም በስራም ታታሪ መሆኑን ያስመሰከረ ነው።ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉትም በንግድ ንቅናቄ ሰፊ እይታ ያላቸው፣ ደፋር መሆናቸውንም የሚያሳዩ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ብለዋል።

የሌሎች ሀገሮችን ቋንቋ አውቀው ከእነርሱ ጋር በንግድ እና በሌሎች የሁለትዮሽ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው።እድሉን እያገኙ ሲሄዱ ከዚህም በላይ እንደሚሰሩ አምናለሁ።ተምረዋል፣ ታሪኩንም ያውቃሉ በተለያየ መልኩ ሥራ ላይ እያዋሉትም ይገኛሉም ነው ያሉት።

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ አብዛኛው ወጣት ትውልድ በመልካም ስብዕና የተቀረፀ ነው።ሆኖም ግን አንዳንዶች ለመልካም ስብእና ተቃራኒ የሆነ ተግባር የሚፈጽሙ የሉም ማለት አይቻልም።በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት እና በመንግሥት ድጋፍ ተሻሽለው ወደ መጥፎ ስብእና የገቡ ወጣቶች ይለወጣሉ። ትውልዱ ሰውን ከሚጎዳ እና አእምሮን ከሚያበላሹ ነገሮች እየተቆጠበ የሚሄድ ከሆነ የተጣለበትን አደራ በማስቀጠል የታሰበበት እና የታለመበት ቦታ ያደርሳል።

በየዓመቱ ሚያዝያ 27 የሚከበረው የድል በዓል በየጊዜው እየደመቀ መከበሩ በሕይወት ላሉት፣ ለሀገር መስዋዕት እሆናለሁ ብሎ ለተሰለፉት የመከላከያ ሠራዊትና የፀጥታ አካላት በሙሉ የሚያስደስት መሆኑን ጠቁመው፤ ለሀገሩ መስዋእት የሆነ ትውልድ በሕይወት ዘመኑ መስዋዕት የሆነለት በዓል ሲከበርለት መመልከት ይፈልጋል፤ ይሄ ለእዛ ትውልድ ሽልማቱም ምስጋናውም ነው ሲሉም አክለዋል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You