‹‹ከአጭሩ ሕማማት በኋላ ረዥሙ የኢትዮጵያ ትንሣዔ ይመጣል››ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡ከአጭሩ ሕማማት በኋላ ረዥሙ የኢትዮጵያ ትንሣዔ የሚመጣ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ2016 ዓ.ም የትንሣዔ በዓል አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሕማማት አጭርና ከባድ ቢሆንም ሕማማቱን ለማለፍ  የሚያስችል ኃይል አላት፡፡ ከአጭሩ ሕማማት በኋላ ረዥሙ የኢትዮጵያ ትንሣኤ የሚመጣ ይሆናል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ መከራና ሞት፣ ግፍና ሙስናን፣ ሲዖልና መቃብርን አሸንፎ የተነሣበትን የትንሣዔ በዓል በየዓመቱ እናከብራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሰሞነ ሕማማት ፈተናን፣ ስቃይን፣ ክህደትን፣ አሳልፎ መስጠትንና የክፉዎችን ኅብረት በጽናት ያለፉ ትንሳዔውን ለማየት ችለዋል ብለዋል፡፡

በሰሞነ ሕማማት ሐሰት ያሸነፈች፣ እውነት የተሸነፈች መስላ የታየችበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብዙዎች መሥዋዕትነትን ፈርተው የሸሹበት ነው። በጽናት የቆሙ ጥቂቶች ግን ከሕማማቱ አልፈው ትንሣዔውን ለመመልከት ችለዋል።

ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ እያለፈች መሆኑን አመላክተው፤ ወቅቱ ለኢትዮጵያ የሕማማት ሰሞን ይሆን ይሆናል። የኢትዮጵያ ሕማማት አጭርና ከባድ ቢሆንም ሕማማቱን ለማለፍ የሚያስችል ኃይል አላት። ከአጭሩ ሕማማት በኋላ ረዥሙ የኢትዮጵያ ትንሣዔ የሚመጣ ይሆናል ብለዋል።

የከተማው ጩኸት እና የሐሰቱ ወሬ እንኳን በሩቅ የነበሩትን፣ ቅርብ የነበሩትንም እንዳሸነፋቸው ጠቅሰው፤ የሆሳዕና ዕለት ደግፈው የወጡት ከሦስት ቀን በኋላ ለተቃውሞ ወጥተዋል። ድጋፋቸውም ተቃውሟቸውም የጥቅም እንጂ የመርሕ አልነበረም።

በዚህም በሌላ ጊዜ ለሞት የሚፈላለጉ አካላት እውነትን ለመስቀል ሲሉ ግን ተባብረው ቆመዋል ብለዋል።

ከሕማማቱ ይልቅ ትንሣዔው ይበልጣል፤ ይረዝማልም። ሕማማቱ አምስት ቀን ሲሆን ትንሣዔው ግን አስር እጥፍ ይሆናል። የአምስት ቀን ፈተና የሃምሳ ቀን ዋጋ አለው።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የሕማማቱን ሽብርና ዋይታ፣ መከራና እንግልት ለተመለከተ ትንሣዔ የሚመጣ አይመስለውም። ትንሣዔው ግን የታመነና የተረጋገጠ ነው። የበለጠ ማረጋገጥ የሚቻለውም ጸንቶ እንደ ዮሐንስ በመቆም ብቻ ነው።

የተነሣነው ኢትዮጵያ እንደምትፈተን አውቀንም፤ አምነንም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ለዘመናት የኖሩ ስብራቶችንና ብልሽቶችን ልናክም ስንነሣ መንገዱ አልጋ በአልጋ አይሆንም። ከችግሩ ማትረፍ የለመዱ አካላት ዝም አይሉም።

በመሆኑም እኛ ልጆቿ መከራውን ተቀብለንና ቀንበሩን ተሸክመንላት ትንሳዔዋ እውን እንዲሆን ልንተጋ ይገባል።

የሕማማቱ ወቅት አጭር ቢሆንም ከባድ መሆኑን እናውቃለን። የኮሶ መድኃኒት እንዲያሽር ከተፈለገ በአንድ ጊዜ በከባዱ መወሰድ አለበት። የኢትዮጵያም ሕማማት እንደዚሁ ነው ብለዋል።

በፊስካል ፖሊሲ፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ነጻነትን በማስተዳደር፣ በክልል አደረጃጀት፣ በሲቪል ሰርቪስና በጋራ ትርክት ግንባታ የተረከብናቸው ውዝፍ ዕዳዎች ብዙ ናቸው ያሉት ዶክተር ዐቢይ፤ ወገባችንን አስረን፣ እጅጌያችንን ሰብስበን መራራውን የኮሶ መድኃኒት ውጠን፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ተጠንቅቀን ግን ፈጥነን፤ አስበን ግን ዋጋ ከፍለን መጓዝ ይጠበቅብናል።

ኢትዮጵያ ሕማማቱን ለማለፍ የማይተዋት አምላክ፣ የሚወዳት፣ የሚያስብላት ብቻ ሳይሆን የሚሞትላትም አመራር፣ ዓላማ አይቶ ዋጋ የሚከፍል ሕዝብ እንዲሁም አንጡራ ሀብቷ ኃይል እንደሚሆናት አመላክተው፤ የፈጣሪ፣ የአመራሩ፣ የሕዝቡ እና የአንጡራ ሀብቷ አራት ማዕዘናዊ አቅም፣ ሕማማቱን ማሳጠርና ማስቻል ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ የሚመጣውን ፋሲካ ረዥም እንዲሆን ያደርገዋል።

የጥብርያዶስ ሞቅታም ሆነ የፕራይቶሪዮን ግቢ ጩኸት ከመንገዳችን አያቆሙንም ያሉት ዶክተር ዐቢይ፤ የሆሳዕና ድጋፍም ሆነ የዕለተ ዓርብ ተቃውሞ መንገዳችንን አያስቀይሩንም። የኢትዮጵያን እውነት ብቻ ተከትለን እንገሠግሣለን። በዚህም ሕማማቱን አሳጥረን የኢትዮጵያን የትንሣዔ ጊዜ እናረዝመዋለን ብለዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You