በመዲናዋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ6 ሺህ 700 በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች ተገንብተዋል

አዲስ አበባ፡– በመዲናዋ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ 6 ሺህ 700 በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች መገንባታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በአዲስ ከተማና አራዳ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች የመኖሪያ ቤቶችን የማስተላለፍና አዲስ ግንባታ የማስጀመር መርሃግብር ትናንት ተካሂዷል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርሃግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ 6 ሺህ 700 በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች ተገንብተዋል። በትንሳዔ በዓል ዋዜማ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች 907 መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች ተላልፈዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በርካታ የመኖሪያ ቤቶች  ተገንብተው ለነዋሪዎች ተላልፈዋል ያሉት ከንቲባዋ፤ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ6 ሺህ 700 በላይ ቤቶች ተገንብተዋል ብለዋል።

በዓመቱ መጨረሻ ከእቅድ በላይ ቤቶችን ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይ ተጨማሪ አካባቢዎችን የመቀየርና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ከተማን ለመቀየር በተሠሩት ሥራዎች ሳይረኩ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

መንግሥት የጀመራቸው ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ እየቀየረ ነው ያሉት ከንቲባዋ ፤ በከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክትን ጀምሮ መጨረስ ባህል እየዳበረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ቤቶቹ ለዘመናዊ አኗኗር አመቺ በሆነ መልክ የተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ቤቶቹ በርካታ ልበቀና ባለሀብቶችን በማስተባበር የተገነቡ ናቸው ብለዋል።

ፈርሰው የተገነቡት ቤቶች ለኑሮ አመቺ ያልነበሩና በአጭር ጊዜ ተመልሰው የተገነቡ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በበጎ አድራጎች ተግባሩ የተሳተፉ ባለሀብቶችንም አመስግነዋል።

የተገነቡ ቤቶችን የማስረከብ መርሃግብሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተገኙበትን ጨምሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተካሂዷል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You