ምዕመናን በዓሉን በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በመደገፍ እንዲያከብሩ የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ

አዲስ አበባ፡- ሕዝበ ክርስቲያኑ የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሳኤ በዓል ሲያከብር በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችንበመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የትንሳዔ በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ በዓለ ትንሣዔ የእግዚብሔር ፍቅር መገለጫና የተስፋችን ማሳያ ነው፡፡

ይህን በመገንዘብ ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው ልጆች ደኅንነት በአንድነት በመቆም ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለታረዙት፣ ለታመሙትና ለታሰሩትም ሁሉ ካለን ከፍለን በመስጠት በዓለ ትንሣዔውን ማክበር ይገባል፡፡ በእግዚአብሔር አሠራር ኃጢአት ያለ ቤዛነት አይሰረይም፤

በመሆኑም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም ኃጢአተኛ ሆኖ ስለተገኘ ቤዛ ሆኖ የሚያድነው ያስፈልገው ነበርና፤ በእግዚአብሔር ፊት ለሱ የሚመጥን ንጹህ አካል ከፍጡራን ወገን አልተገኘምና እሱ ራሱ ሰው ሆኖ የሰው ቤዛ ለመሆን በሥጋ ተገለጠ፣ በዚህም መሠረት የሰው ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ በመሰቀል ንጹህ ደሙን አፈሰሰ፤ በዚህም ምክንያት የሰው ኃጢአት በሥርየት ተዘጋ ብለዋል።

የጌታችንን ትንሣኤ ስናከብር የኛንም ትንሣኤ በማሰብ ሊሆን ይገባል፡፡ የሱ ትንሣኤ ለእኛ ትንሣኤ በኩር፣ ማሳያና ማረጋገጫም መሆኑን ገልጸው፤ እግዚአብሔርም በየዕለቱ የሚፈልገው የኛን ትንሣዔ ማየት ነው፡፡ ትንሣዔያችንም አምነን ስንጠመቅ ተጀምሮ ከመቃብር ስንነሣ የሚጠናቀቅ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

እግዚአብሔር ክሕደትን፣ ከሕገ ተፈጥሮ ያፈነገጠ ጸያፍ ተግባርን፣ ጥላቻን፣ ጦርነትን፣ መለያየትን፣ ራስን ብቻ መውደድን፣ መጨካከንን፣ ግብረ ኃጢአትን፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር ገንዘብ አለማድረግን፣ ፈጣሪን አለማመንን የተጸየፈ ምእመን ማየት ይፈልጋልና እነዚህንና መሰል መጥፎ ተግባራትን መፈጸም እንደማይገባ አስታውቀዋል፡፡

ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ፣ በፍቅር ፣ በሰላም፣ በይቅርታ ፣ በመከባበር ፣ በአንድነት እንዲሁም በመተሳሰብ ሃይማኖታዊና ግብረ ገባዊነት ጸንተን መኖር ከቻልን ትንሣኤ ማለት እሱ ነው ብለዋል፡፡

በዓለ ትንሣዔ የእግዚብሔር ፍቅር መገለጫና የተስፋችን ማሳያ መሆኑን በመገንዘብ ምእመናን ለተራቡ፣ ለተጠሙ፣ ለታረዙ፣ ለታመሙና ለታሰሩም ሁሉ ካለን አካፍለን በመስጠት ከኛ ጋራ በመንፈስና በሞራል በዓለ ትንሣኤውን እንዲያሳልፉ ልናደርግ ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፤ እነሆ የዓለም ንጉሥ ተነስቷልና እንቀበለው፣ እናክብረው፣ እናምስግነው፣ ሁላችንም በትንሳዔው ብርሃን ለሀገራችንና ለሕዝባችን የሰላም መሣሪያዎች እንሁን፡፡ የችግሮቻችን መውጫ ቁልፍ ሰላም ብቻ በመሆናቸው ሰላምና ፍቅርን ጌታ በትንሳዔው እንዲያድለን በጾሎት እንትጋ ሲሉ አስገንዝበዋል።

ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳዔ ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ ተፈናቃዮችን ወደቀድሞ መኖሪያቸው በመመለስ እና ያዘኑትን በማጽናናት መሆን እንዳለበት ገልጸው፤ ለታመሙት ምህረትን፣ ለደከሙት ብርታትን፣ ለታሰሩት ይቅርታ፣ ላዘኑት መጽናናት፣ በጭንቀትና በመከራ ላይ ለሚገኙ ሰላምና ፍቅሩን እንዲሰጣቸው ምዕመኑ በጸሎት እንትጋ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ እንደገለጹት፤ የትንሳኤ በዓል በሚከበርበት ጊዜ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተጓዘበትን የትህትና መንገድ፣ የመከራና የሥቃይ ጎዳና እንዲሁም ስለመተላለፋችን የከፈለልንን የሕይወት መስዋዕትነት በማሰብ መሆን አለበት፡፡ እንደ ፓስተር ጻድቁ ገለጻ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ፍቅር በጭካኔ ላይ ብርቱ እንደሆነና የክህደት ጎርፍ ፍቅርን ሊጠርግ እንደማይችል አስረድቶናል፡፡ ከዚህም ፍቅር የዘር ግንድ የማይቆጥር፣ የብሔር ድንበር የማያግደው፣ ጥላቻን ማሸነፊያ፣ የበቀል ፍላጎትን ማስወገጃና ሰላምን ማስፈኛ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ምዕመናን በዓሉን ሲያከብሩ አቅም የሌላቸውን ወገኖች በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው፤ በዓሉ የደስታ፣ የፍስሃና የትንሣዔውን እውነት የምናስተውልበት ይሁንልን ሲሉ መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዶክተር ዮናስ ይገዙ ባስተላለፉት የበዓል መልዕክታቸውም፤ የትንሳዔ ወቅት ማንነታችንን የሚያስገነዝበን የሰላም ሰዎች መሆናችንንም የሚያስታውሰን ወቅት በመሆኑ የሰላም ሰዎች ሰላምን ተግተው የሚሹና በባለ አደራነት መንፈስ ሌሎችን ለመታደግ የሚተጉ ናቸው ብለዋል፡፡

ጌታችን ለተሳደቡት፤ ለዘበቱበት፤ ላስጨነቁትና ላዋረዱት የአጸፋ ምላሽ አልሰጠም፤ ይልቅስ በመስቀል ላይ ሆኖ እንኳን የተናገረው የእርቅና የሰላም ቃል የመስቀል ስቃይ እንከኳን ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የማስታረቅ አገልግሎቱን ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ምዕመናን ሰላምን በሰላም መንገድ ብቻ እንሻት፤ መሻት ብቻ ሳይሆን ዋጋ ቢያስከፍልም እንኳን ዋጋ ለመክፈል እንፍቀድ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የክርስቶስን መንገድ በመምረጥ መልካሙን ተግተን በመፈለግ የዘንድሮው የትንሳዔ በዓል ተስፋን እንዲሰንቅልን በጾሎት እንትጋ ብለዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶቹ በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሆን የተመኙ ሲሆን፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ የኢየሱስን የትንሳዔ በዓል ሲያከበር በመረዳዳትና በመተጋገዝ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው፣ ዳግማዊት አበበና ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You