መጽሐፉ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ጥናትና የተለያዩ ሥራዎች ለሚያከናውኑ አካላት እገዛ ያደርጋል

አዲስ አበባ፡“ዘመናዊነት ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል አይታሰብም” የተሰኘው መጽሐፍ ከዓባይ ግድብ ጋር በተያያዘ ጥናትና ተግባራዊ ሥራዎችን ለሚያከናውኑ አካላት እገዛ እንደሚያደርግ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ጽ/ቤት ገለጸ።

አስቀናቸው ገብረየስ (ኢ/ር) “ዘመናዊነት ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል አይታሰብም” በሚል ርዕስ ያሳተሙትን መጽሐፍ 990 ኮፒ በትናንትናው ዕለት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ጽህፈት ቤት አበርክተዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ መጽሐፉ በዓባይ ግድብና የሌሎች ግድቦች አጠቃቀምን ለማዘመን እንዲሁም በዘርፉ ጥናትና ተግባራዊ ሥራዎች ለሚያከናውኑ አካላት ጠቃሚ ሃሳቦችን በማቅረብ እገዛ ያደርጋል።

በዓባይ ግድብ ግንባታ ላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አቅሙ በፈቀደው መልክ በገንዘብ ፣በዕውቀት ፣በጉልበትና በሞራል ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

በእውቀትና በተለያዩ የሥነ ጥበብ ሥራዎች የሚደረጉ ድጋፎች በገንዘብ ለመተመን አዳጋች ቢሆኑም ስለ ግድቡ በማስተዋወቅ በኩል ግን ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አንስተዋል።

ጽህፈት ቤቱ መጽሐፍቱ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ጥናትና ተግባራዊ ስራዎች ለሚያከናውኑ ተቋማት፣ ለተለያዩ ቤተመጽሐፍትና ለዩኒቨርሲቲዎች በስጦታ መልክ የሚበረከት መሆኑን ተናግረዋል።

የመጽሐፉ አዘጋጅ አስቀናቸው ገብረየስ (ኢ/ር) በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ለዓባይ ግድብ የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ ቢያደርጉም ይህ በቂ ነው ብለው ባለማሰባቸው ከሀገራቸው ያገኙትን እውቀትና በውጪ ያካበቱትን ልምድ ተጠቅመው እንደጻፉት ተናግረዋል።

በአሜሪካ ከሚሰሩበት 80 ሺህ ሜጋ ዋት የሚያመርትና የወቅቱን ቴክኖሎጂ ከሚጠቀም ተቋም የቀሰሙትን ልምድ በመጽሐፉ ያሰፈሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ለትውልዱ እውቀት በመስጠት የኤሌክትሪክ ኃይል ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

በመጽሐፉ ላይ ከተነሱ ጉዳዮች ባለፈ ከተቋማት ጋር በመተባበር ዘርፉ ስልጠና መውሰድ ለሚፈልጉ ሰዎች ዕውቀታቸውን ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢንጂነሩ ዳያስፖራው ማህበረሰብ ከውጪ ሀገራት የሚቀስመውን ልምድና እውቀት በሀገሬ ቢሆን ብሎ ከመመኘት ባለፈ ልምዱን ለማካፈል መነሳሳት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You