የትውልዱ መንገድ ውጤት – የወጣቶቹ የዘይት ፋብሪካ

የአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት ዘላቂ እድገት እንዲያስመዘግብ የግሉን ዘርፍ ትርጉም ባለው መጠን ሊያሳትፍ ይገባል። ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸው የዓለም መሪ የሆኑት ሀገራት ለግል ዘርፍ ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የሚታወቁ ናቸው። በኢትዮጵያም የግሉ ዘርፍ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው በማለም፣ ዘርፈ ብዙ የፖሊሲና የተግባር ርምጃዎች ተወስደው፣ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በማኅበር ተደራጅተውም ይሁን በግላቸው በመሥራት ውጤት ያስመዘገቡ በርካታ ወጣቶች ለዚህ አብነት ተደርገው ይጠቀሳሉ።

ወጣት ታሪኩ አበራ የ‹‹ቶኩማ ኦዳ ነቤ›› የምግብ ዘይት ማምረቻ ሥራ አስኪያጅ እና መስራች ነው። ማኅበሩን የመሠረቱት 50 ወጣቶች ሲሆኑ፣ 50ዎቹም የተገናኙት ደግሞ በሥራ ቦታቸው ላይ እንደሆነ ይናገራል። ማኅበራቸው የተወለደው በ2010 ዓ.ም መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህንንም ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ ጋር ያገናኘዋል።

ወጣቱ ሲያልም የነበረው፤ ከአቻዎቹ ጋር በመሆን ሀገሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ማድረግን ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በእውቀት ላይ የተመሠረተ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራ በማከናወን ኢኮኖሚው እንዲያድግ መሥራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ይገልፃል።

ወጣቱ፣ መጋቢት 24 መድኃኒት ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥሮ ለመሥራት ዱከም በሚገኘው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ለስልጠና መላኩን ያስታውሳል። ወጣቶቹ ስልጠናውን ጨርሰው ሥራ ከጀመሩ በኋላ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይወያያሉ። የውይይታቸውም ዋና ነጥብ ‹‹አንድ ላይ በመሆን የማኅበረሰባችንን ችግር መፍታት የምንችለው እንዴት ነው? የቤተሰቦቻችንን ኑሮ ማሻሻል የምንችለው በምን መልኩ ነው? በተለይ ደግሞ በመልካም እሴት እና ማንነት ያሳደገን የማኅበረሰብ ክፍል መደገፍ የሚቻለው በየትኛው መስክ ብንሰማራ ነው?›› በሚል ሃሳብ ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር።

‹‹በርግጥ እንደ ሥራ ባህሪያችንና ልምዳችን ቢሆን ሊኖረን የሚገባው የመድኃኒት ፋብሪካ ነው›› የሚለው ወጣቱ፣ የመድኃኒት ፋብሪካ ማቋቋም ግን በጣም ብስለትን፣ በእድሜም በእውቀትም መብሰልን የግድ ይላል። በሥራም የካበተ ልምድ መኖርንም ይፈልጋል›› ሲል ያስረዳል።

ስለዚህ ምርጫቸው ያደረጉት የማኅበረሰቡ ችግር የሆነው የዘይት አቅርቦት ላይ መሥራትን ሆነ። እንደ አጋጣሚም 2012 ዓ.ም የዘይት ጉዳይ አነጋጋሪ ይሆናል፤ እነሱም “ማቋቋም ያለብን የዘይት ፋብሪካ ነው” ብለው ወስነው ወደ ሥራ ለመግባት ተስማሙ።

‹‹ባለሀብቶች የመኪናቸውን ሊብሬና የቤታቸውን ካርታ አስይዘው ኢንቨስት ያደርጋሉ። መንግሥት በቀረጸው የትምህርት ፖሊሲ የተማርን እኛ ደግሞ የትምህርት ማስረጃችንን ተጠቅመን ኢንቨስት እናደርጋለን። እኛ ይህን አካሔድ እንጠቀምበታለን። ይህን አካሔድም የትውልድ መንገድ ብለን እናወራዋለን። በእኛ መንገድ፤ በእኛ ጉዞ ትውልድ ይድናል፤ ሀገርም ትበለጽጋለች። ሀገር በተሻለ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ትችላለች›› ሲል ያስረዳል።

‹‹እኛ የአርሶ አደር ልጆች ነን። በተፈጠረልን የሥራ እድል ጥሩ ካፒታል እንዲኖረን እንሻለን። ብር ባገኘን ቁጥር ደግሞ የተሻለ ትምህርት እንማራለን፤ የፋይናንስ ነፃነታችንን እናውጃለን፤ ይበልጥ እንሰራለን፤ እነዚህን ባደረግን ቁጥር በርካታ ሰዎችን መቅጠር እንችላለን።›› ሲል ያብራራል። በአሁኑ ወቅት እውቀት ያላቸው እና አዕምሯቸው የበለጸገ ሰዎችን ማግኘት የሚያስችል መደላድል እየተፈጠረ መሆኑንም ጠቅሶ፣ ‹‹ይህም ሁኔታ የበለጠ ከግባችን ሊያደርሰን እንደሚችል ጥርጥር የለውም›› ይላል።

እንደ ታሪኩ ገለጻ፤ ወጣቶች ሁሌ ተወቃሽ ትውልድ መሆን የለባቸውም። በሚችሉት ሁሉ የሀገራቸውን ችግር ለመፍታት የሚጥሩና የሚተጉ መሆን ይጠበቅባቸዋል። የተማሩትም ችግር ለመፍታት ነው። ስለዚህ ‹‹እንዴት ነው ችግር መፍታት የሚቻለው›› በሚል እነርሱም ማኅበሩን ለመመስረት በቅተዋል።

‹‹የሰው ልጅ ትልቁ ጠላቱ የገንዘብ ማጣት አይደለም። ወይም ደግሞ የገበያ ችግር አይደለም። ለምሳሌ አንድን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ስንነሳ ‹አትችልም፤ ገንዘብም እውቀትም የለህም፤ ይህ እንዴት ይቻልሃል? መንግሥት ደግሞ ለነደፍከው ፕሮጀክት ስኬታማነት አያግዝህም› የሚሉና ሌሎች ብዙ ነገሮች ስለሚነገሩ እንዳንሞክር ያደርጉናል›› ሲል ጠቅሶ፣ ይሁንና ሥራ መጀመር በጣም ብዙ ዝግጅት ማድረግን አይጠይቅም፤ ራስን ማዘጋጀትና ሰዓትን በአግባቡ መጠቀምን ግን ይጠይቃል›› በማለት ይናገራል።

ወጣቶቹ በ2013 ዓ.ም በስድስት ሚሊዮን ብር የማምረቻ ቤት በመንግሥት ተገነባላቸው። በዚህም ስድስት ሚሊዮን ብር ማትረፍ ቻሉ። በ2014 ዓ.ም ደግሞ የ36 ሚሊዮን ብር ማሽን ገባላቸው። በዚህም 36 ሚሊዮን ማትረፍ ቻሉ። በ2016 ዓ.ም ደግሞ አሁንም መንግሥት በ37 ሚሊዮን ብር ሁለት መጋዘን ገነባላቸው። ፕሮጀክታቸው በመንግሥት በኩል ብቻ በአጠቃላይ 45 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደተደረገበት ወጣቱ ይናገራል።

እነርሱ የመድኃኒት ፋብሪካ ሠራተኞች ነበሩ። ትልልቅ ፋብሪካ መትከል ያለበት ባለሀብት ብቻ የሚመስላቸው ቢኖሩም፣ ‘እውቀት ያላቸው ወጣቶችም መሥራት ይችላሉ፤’ የሚል አመለካከት ይኖር ዘንድ መንገዱን መጀመራቸውን ታሪኩ ያስረዳል። የካፒታላቸው ምንጭ ከወር ከሚያገኙት ደመወዛቸው የሚያስቀምጡት ቁጠባ መሆኑን ይገልጻል። “በመነሻ አካባቢ ከወር ደመወዛችን መቆጠብ የጀመርነው 200 ብር ነበር። ሁለተኛ ዙር ላይ የቆጠብነው 220 ብር ሲሆን፣ ሶስተኛው ዙር ላይ ደግሞ 320 ብር ነው። በዚህ ሂደት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የደረስንበት የቁጠባ መጠን 520 ብር ላይ ነው” ሲል ያስረዳል።

ማሽኑን በገዙበት ወቅት ግን እያንዳንዱ አባል በአንድ ጊዜ 20 ሺ ብር መቆጠብ ችሏል። የእነርሱ ቁጠባ እንደተጠበቀ ሆኖ የመንግሥት ድጋፍ ደግሞ ትልቁን ቦታ ይዟል። ይህ ሁሉ ተደማምሮ የዘይት ፋብሪካው እውን ወደመሆኑ ምዕራፍ ላይ ደረሰ።

ማሽኖቹ በቆጠቡት ብር ብቻ ተገዛ ማለት እንደማይቻል ወጣት ታሪኩ ይናገራል። በማኅበራቸው ውስጥ በሶስት ዓመታት ውስጥ የቆጠቡት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ብቻ ነው። በተለይ አንዳንድ አዋጆች የወጣቶችን ብልጽግና እና የወጣቶችን ራስን የመቻል ጉዞ የሚጠፈንጉ ናቸው። የእነርሱ ጉዞ ግን ያንን አሳሪ ሂደት ያለፈና እንዲሻሻል የሚያደርግም ነው።

ታሪኩ እንደሚለው፣ የሀገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት እና ሕግ ለወጣቶች ምቹ ነው ማለት አይቻልም። እውነታው የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፤ ችግሩን ሁሉም ያውቀዋል። አንድ ወጣት ሥራ ፈጥሮ ፋይናንስ በሚፈልግበት ጊዜ ዋስትና/ማስያዣ (Collateral) ይጠየቃል። ዋስትና ከመጠየቁ በፊት ግን ያ ሰው በእጁ የያዘው ምንድን ነው ተብሎ መጠየቅ ነበረበት ሲል ያብራራል።

እነርሱ የተጠየቁት አንድ ነገር ነው። ከቀድሞው የዱከም ከተማ ከንቲባ አቶ ተሾመ ግርማ ጋር በጉዳዩ ላይ መወያየታቸውን ወጣቱ ያስታውሳል። በውይይቱም በወቅቱ የነበረው የማሽኑ ዋጋ 22 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር መሆኑ ተሰላ። ውል ማሰሪያ ደግሞ አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ያስፈልግ ነበር። ወጣቶቹ ይህን ሲሰሙ ግራ ተጋቡ፤ ምክንያቱ ደግሞ እነርሱ ያላቸው ብር ውስን መሆን ነው። ከቀድሞ ከንቲባው ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ 453 ሺ ብር በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም (የአሁኑ ሲንቄ ባንክ) ላይ ቆጠቡ። የቁጠባ ማኅበሩ ደግሞ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ብድር ፈቀደላቸው። ያገኙትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ወስደው ልማት ባንክ ቁጠባቸው ላይ አስቀመጡ። በ22 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር መዋዋል ቻሉ። ማሽኑ ተገዝቶ ሲመጣ 36 ሚሊዮን ብር ገባ።

ወጣት ታሪኩ እንደሚለው፤ መንግሥት ማለት መሪ ነው። መንግሥት ሕዝብን የሚያስተዳድርና የሕዝብን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ አዋጆችን ያወጣል። እነዚያን አዋጆች መጠቀም ያለበት ደግሞ ሕዝብ፣ በተለይ ወጣቱ ነው። ስለዚህ የፈለጉትን መጠየቅ ይችላሉ። ልክ ልጅ ወላጆቹን የተቸገረውን ለመጠየቅ እንደማይፈራ ሁሉ ወጣቶችም መንግሥትን የፈለጉትን ለመጠየቅ የሚፈሩበት ምክንያት የለም።

‹‹ምክንያቱም የምንሰራው ወንጀል ወይም ሕገ ወጥ ሥራ አይደለም። የምናራምደው ሥርዓት አልበኝነትንም አይደለም። እኛም የምንጥረው የሀገርን ኢኮኖሚ የተሻለ ለማድረግና ሀገራችንን በምስራቅ አፍሪካ ልዕለ ኃያል እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪና ችግር ፈቺ ሀገር ለማድረግ ነው። በዓለም አቀፍ መድረክም ተሰሚ ሀገር ለማድረግ ነው።” ሲል ያብራራል። ስለዚህ መንግሥት እኛን የማይረዳበት፤ እኛን የሚመስሉ ትውልዶችንም የማያግዝበት ምንም ምክንያት አይኖረውም›› ይላል። እነርሱ የተወሰነ ክፍያ ከፍለው ልማት ባንክ ማሽኑን ያቀረበበትን መንገድም ከዚህ አኳያ ነው የተመለከተው።

ፕሮጀክታቸው ትልቅ ነው፤ ከ200 ሚሊዮን እስከ 300 ሚሊዮን ካፒታል ያለው ባለሀብት የሚሰራው ፕሮጀክት ነው። ወጣቶቹ ተደራጅተው ወደሥራ ከገቡ በኋላ መንግሥት ያላሰለሰ እና የሚያበረታታ እንዲሁም ከምንም ነገር ጋር ሊያወዳድሩት የሚይችሉት ዓይነት ድጋፍ አድርጎላቸዋል። መንግሥት ቀን በቀን ፕሮጀክታቸው የደረሰበትን ደረጃ ይከታተላል።

‹‹እኛ ያለን ብር ሳይሆን እውቀት ነው። በእውቀታችን የተሻለ ነገር እንደርጋለን ብለን አቅደን ስንነሳ መንግሥት እምነት አሳደረብን። መንግሥት አሁንም ቢሆን በእኛ ላይ እምነቱን የተሻለ ማድረግ አለበት። እኛ የአዋጆችና ማስፈጸሚያ ነን። መንግሥት በአሁኑ ወቅት በእኛ ላይ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት አድርጎብናል። እንዲሁም ማሽን በምንገዛበት ሰዓት ዋስ ሆኖናል። መንግሥት በብዙ ነገር ከጎናችን ነው። በእኛ ውስጥ አንድም ባለሀብት የለም። እኛ የያዝነው መንገድ የትውልድ መንገድ ነው በሚል ሥራችንን ተያይዘነዋል›› በማለት ይናገራል።

እነ ወጣት ታሪኩ ፕሮጀክታቸውም መንግሥት ዘንድ ቀርቦ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታና አሳማኝ የሆነ ፕሮጀክት መሆኑን በትክክል ማሳወቅ ይፈልጋሉ። ምክንያቱም የፕሮጀክታቸው ዓላማው ሁሉን አቀፍ የሆነ ፍላጎት የሚያስጠብቅ እንጂ የግል ፍላጎትን የሚያስጠብቅ መሆን እንደሌለበት ያምናሉ። ይህንንም በማድረግ አርዓያ መሆን ይሻሉ።

መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሔ ርምጃዎች መካከል ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የሚገኘው የእነታሪኩ ፕሮጀክትም፣ በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› እንቅስቃሴ ተጠቃሚ መሆኑን ታሪኩ ይናገራል።

ሀገራችን የማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩን የላቀ ደረጃ ላይ ካላደረሰችና ሁልጊዜ ከውጭ ሀገር ምርት የምታስገባ ከሆነ የትም መድረስ አንችልም። ስለዚህ በማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩ በተለይ በዘይት በኩል ያለውን ችግር ፕሮጀክታቸው መቅረፍና የገበያውን ውጥረትም መቀነስ ይችላል። በጥራት በኩል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ይቻላል በማለትም ያስረዳል።

እንደ ታሪኩ አባባል፤ እነርሱ የሚያመርቱት የኑግ፣ የሱፍ፣ የለውዝ ዘይት ነው። ፋብሪካው ማምረት ሲጀምርም 120 ቋሚ እና ተመላላሽ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል። ከዚህ በተጨማሪም ፋብሪካው ሌሎች የሠራ መስኮችንም ይፈጥራል። በአሁኑ ወቅት ፋብሪካውን የመገጣጠሙ ሥራ 90 በመቶ ደርሷል፤ ቀሪው አስር በመቶው ቢበዛ የአንድ ወር ሥራ ስለሆነም በዚህ የሰኔ ወር ዘይት ማምረት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የዱከም ክፍለ ከተማ የሥራ እድልና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ አሰፋ እንደሚሉት፣ ከተማ አስተዳደሩ እየተገባደደ ባለው 2016 በጀት ዓመት ለ50ሺ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅዷል። ከዚህ ውስጥ የዱከም ክፍለ ከተማ 30 በመቶውን ይይዛል። በክፍለ ከተማው ሰፊ የሥራ እድል አለ፤ በርካታ ኢንተርፕራይዞችም ተደራጅተው ወደሥራ ገብተዋል።

ከእነዚህ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ አንዱ የዘይት ፋብሪካ መሆኑንም አቶ ታደሰ ያመለክታሉ። መንግሥት ለወጣቶቹ ትኩረት በመስጠት በርካታ ድጋፍ አድርጎላቸዋል ሲሉም ጠቅሰው፣ ወጣቶቹ ብድር በመውሰድ ማሽን በመግዛት ወደሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል። ‹‹ነገ ደግሞ እነርሱ የሥራ እድል ይፈጥራሉ፤ ግብር ይከፍላሉ፤ ለወጣቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ያደርጋሉ›› ብለዋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You