ሁሌም ቢሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ለሰብአዊ መብትና ለፍትህ የቆሙ አጋር ድርጅቶች አስገዳጅ ሁኔታዎች ባሉበት ሁኔታ ለሽግግር ፍትህ አስፈላጊነት በቅድሚያ ድምፅ የሚያሰሙ ናቸው። በተለይ ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ህግን ለማውጣትና ተግባራዊ ለማድረግ ባቀደችበት በዚህ ወቅት የሽግግር ፍትህ ስኬት የሚለካው በዋናነት የሲቪክ ማህበራት፣ መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ፍትህን፣ የህግ የበላይነትን፣ ተጠያቂነትን፣ ሰላም ግንባታንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በጋራ መስራት ከቻሉ ነው።
ይህ ትብብራቸው መረጃ ለማሰባሰብ፣ በጥናትና ምርምር የማስረጃ ዳሰሳ ለማካሄድ፣ ለባህልና ታሪክ ጥናት፣ ማንነትን መሰረት ባደረገ የይገባኛል ጥያቄዎች ላይ ሙያዊ ትንተና ለማድረግ፣ ለተጎጂዎች ስለሚሰጥ ካሳ፣ ገንቢ የማህረሰብ ውይይት ለማካሄድ፣ በሽግግር ፍትህ ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት ወሳኝ ነው።
የሽግግር ፍትህ አተገባበር የተለያዩ ቅርፆች፣ ስልቶችና አሰራሮች አሉት። እውነትን ማፈላለግ፣ ክስ መመስረት፣ ተገቢ የህዝብ ጥያቄዎችን መለየት፣ የህግ ትንተናና አስተያየት መስጠት፣ ተዋጊ ኃይሎችን ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ፣ ለተጎጂዎች የማካካሻ ድጋፍ ሰጪ መዋቅሮችን ማዘጋጀት፣ ከግጭት በኋላ ስሜቶችን መቆጣጠርና በተጎጂዎችና አጥፊዎች መካከል የውይይት መዋቅሮችን ማዘጋጀት ለተጎጂዎች የስነ አእምሮ ድጋፍና ፈውስ መፈለግ፣ እርቅና ከግጭት በኋላ ማገገምን ያጠቃልላል። በሽግግር ፍትህ ሂደቱ ከሚሳተፉ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ውስጥ ታዲያ አንዱ ሚዲያ ነው።
በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የህግና ፖሊሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዘላለም እሸቱ እንደሚያብራሩት፣ የሽግግር ፍትህ ሀገራት ከአምባገነናዊ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ወይም ከግጭት ወደ ሰላም ሲሸጋገሩ ብሎም በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቶች ውስጥ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ካሉ ለማስተካከል የሚሄዱበት መንገድ ነው።
እነዚህን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በመደበኛው የህግ ስርአት ማስተካከል ይቻላል። ነገር ግን በመደበኛው የህግ ስርአት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ማረም በማህበረሰቡ ውስጥ የተፈጠረውን መቋሰልና ማህበረሰባዊ ቀውስ ላይመልሰው ይችላል። ከዚህ አኳያ የሽግግር ፍትህ ዋነኛ ዓላማ ወደኋላ ሄዶ የተፈጠሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ማረምና እልባት መስጠት ነው። ይህም የተፈጠረውን ማህበራዊ ቀውስና መቋሰል በማከም ተመሳሳይ ነገር ደግሞ እንዳይመጣ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርን ያካትታል።
ሌሎች እንዳሉ ሆነው በሽግግር ፍትህ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከሚጠበቁ ተቋማት ውስጥ ሚዲያው ይጠቀሳል። በሽግግር ፍትህ የሚዲያው ሚና ቁልፍ ሆኖ ገሳለ ሂደቱን የማሳለጠም ሆነ የማደናቀፍ አቅም አለው። ይህ ማለት ሚዲያው በበጎ መልኩ ስራውን ከሰራ የሽግግር ፍትህ ሂደት እንዲሳካ አስተዋፅኦ ያደርጋል። በአሉታዊ መንገድ ስራውን ከሰራ ደግሞ የሽግግር ፍትህ ሂደቱ ሊደናቀፍ ይችላል። ስለዚህ ሚዲያው ከአጀንዳ መቅረፅ ጀምሮ እስከ ዜና ማሰራጨት ድረስ በሽግግር ፍትህ ሂደት የሚኖረው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ የሽግግር ፍትህ ለማንኛውም የሰላም ሂደት ቁልፍ መሳሪያ ነው። ይህ የሰላም ሂደት ደግሞ በህዝብ ካልተገዛ ውጤታማ የመሆን እድሉ ዝቅተኛ ይሆናል። ስለዚህ ይህን የሰላም ሂደት ሀሳብ ህዝቡ እንዲገዛው በማድረግ ረገድ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ሚዲያው ነው። በሽግግር ፍትህ ምንነትና ዓላማ ዙሪያ ማህረሰቡ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ረገድም ሚዲያው ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። በሽግግር ፍትህ ዙሪያ የህዝቡ አተያይ ተአማኒነትና ቅቡልነት እንዲኖረው የማድረግ ስራዎችንም ሚዲያው ይሰራል።
ይህ ሚናቸው እንዳለ ሆኖ ሚዲያዎች በሽግግር ፍትህ ሂደት በተጎጂዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል። የተጎጂ መብቶችን ማጉላት ያስፈልጋል። የተደበቁ እውነቶችን፣ የተፈፀሙ ጥቃቶችን በምርመራ ማጋለጥ ይኖርባቸዋል። ለተጎጂዎች ድምፅ ሊሆኑ ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ የተጎጂዎችን ታሪክ በመሸፈንና በማጋራት ለሽግግር ፍትህ ሂደቱ ቀና ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።
ትክክለኛና ሚዛናዊ ዘገባዎችን በመስራት ሚዲያዎች ለሽግግር ፍትህ ሂደት በጎ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህም ዜጎች በሽግግር ፍትህ ሂደቱ ላይ እምነት ኖሯቸው የሚሳተፉበት ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እድል ይፈጥራል። ከሽግግር ፍትህ ጋር በተያያዘ ሚዲያዎች የዘገባ ጉዳዮችን የሚቀርፁበት መንገድ ግን ጥንቃቄ የተሞላው ሊሆን ይገባል። አንዳንድ የተድበሰበሱ ጉዳዮች ካሉ ደግሞ በደንብ መርምረው በማጋለጥ የፍትህ ሽግግር ሂደቱን ማገዝ ይኖርባቸዋል።
የሽግግር ፍትህ ያለ ሚዲያ ድጋፍ አይሰራም። ይህንንም በሽግግር ፍትህ ሂደት የሚሰሩ ሁሉ ማወቅ አለባቸው። ሚዲያው ከመነሻው ጀምሮ በሽግግር ፍትህ ሂደት መሳተፍ አለበት። መሻሻጫ የሚመስሉ ዜናዎችን ማስቀረት ያስፈልጋል። በተለይ የሽግግር ፍተህን ለማሻሻጫነት መጠቀም አይገባም። የቋንቋ ለውጥ ማድረግም ይጠበቅበታል። የሚዲያው ስራ የሽግግር ፍትህ አላማን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም