የትችት አባዜ

በግራ በቀኝ የሚርመሰመሱት የግንባታ ማሽኖችን እየሸሹ ከሚራመዱት እግረኞች መካከል ዘውዴ መታፈሪያ አንዱ ነው። አንደኛው ዶዘር ሲያልፍ ሌላኛው ይተካል። ሰዎች በሚሠራው መንገድ በቀኝ ዳር አንዳንዶች ደግሞ በግራ ዳር ሌሎች ደግሞ በመሃል ይራመዳሉ። ዘውዴ በሚሠራው መንገድ መሃል ለመሃል እየተራመደ ለራሱ ያጉተመትማል። ምን እንደሚል አይሰማም። የሚራመደው ለብቻውን ነው። ነገር ግን ለብቻውን ያወራል። ምክንያቱ ግልፅ አይደለም።

እየተራመደ የእጅ ስልኩ ጠራ፤ አነሳና ከገብረየስ ገብረማሪያም ጋር ማውራቱን ቀጠለ። ‹‹እየመጣሁ ነው።›› ብሎ ሳይጨርስ አንድ ተሽከርካሪ በመንገዱ መሃል ለመሃል በፍጥነት መጥቶ አቧራውን አቡንኖበት አልፎት ሄደ። ዘውዴ በአፍ እና በአፍንጫው የአቧራው ብናኝ ገባበት። ቅባት ያልተቀባው ፀጉሩ በአቧራ ተሸፈነ። ድሮም ጀማምሮት ነበር፤ አቧራው ሲቦንበት እና እየበረረ የመጣው ተሽከርካሪ ለጥቂት ሊገጨው እንደነበር እያስታወሰ ጭራሽ ተነጫነጨ።

‹‹…በመሃል የከተማ ጎዳና አቧራ አልብሰውኝ ጭራሽ ሊደፉኝ ነው?›› ሲል፤ ገብረየስ ከወዲያ ሆኖ ‹‹ ምንድን ነው?›› ብሎ ጥያቄ አቀረበ። ‹‹ከተማው አይጥ የገማመጠው ቦንቦሊኖ መስሎልሃል። አቧራውን አለፍኩ ስትል ጭቃው አያሳልፍህም፤ ለማንኛውም ስመጣ እናወራለን። በእግር መሄድ ግዴታ ስለሆነብኝ ለብቻዬ እየተራመድኩ ነው። ታክሲ የማገኝበት ቦታ ልደርስ የቀረኝ ትንሽ ነው። አሁን እደርሳለሁ።›› ብሎ ስልኩን ዘጋው።

ግራ ቀኙን ፈረሳውን እና ግንባታውን እየተመለከተ እግሩ እንዳመጣለት ሲራመድ ጭቃ ረገጠ። ‹‹…ኤጭ! ሰው መሃል ከተማውን እንዲህ ጭቃ በጭቃ ይደረጋል?…›› ብሎ በማጉተምተም ሳይሆን የሚሰማ ድምፅ በማውጣት ምሬቱን ተናገረ። ብዙም ሳይርቅ በድጋሚ የእጅ ስልኩ ጠራ ደዋዩ ተሰማ መንግሥቴ ነበር። ከደዋዩ ‹‹…ደርሳችኋል ?›› የሚል ጥያቄ ቀረበ። ‹‹እኔ ገና ነኝ።›› ገብረየስ ግን ደርሷል።›› የሚል ምላሽ ሰጠ። የት እንደሆነ ሲጠይቀው በመከፋት ከአዲስ አበባ እምብርት ብዙም ሳይርቅ በእግሩ እየተራመደ እንደሆነ ሲገልጽ፤ ተሰማ ግር አለው። ‹‹ አመሻሽ ላይ ምን ልትሠራ ከሠፈር እራቅክ?›› ብሎ ሲጠይቀው፤ ‹‹ እየተቦካ ያለው ሊጥ ኩፍ ማለቱን ላረጋግጥ፤ ልጎበኝ።›› ብሎ ምላሽ ሰጠው። ተሰማ ሳቀ፤ ዘውዴ የተሰማን ሳቅ ላለመስማት ተንቀሳቃሽ ስልኩን ከጆሮ አራቀው።

‹‹ አንተማ ምን አለብህ በደንብ ሳቅ!›› ሲለው ተሰማ በድጋሚ ሳቀ። ዘውዴ ግንባሩን ቋጥሮ ‹‹አሁን ይህን ያህል የሚያስቅ ምን ተናግሬ ነው?›› ሲል ጠየቀ። ‹‹… አንዳንዴ ሳስበው የተፈጠርከው ለሰዎች ተርፈህ ኑሮን ለማጣጣም ሳይሆን ለማማረር ብቻ ይመስለኛል። ጉብኝትህ ለመደሰት እና ለማድነቅ ካልሆነ ለምን ከአካባቢህ ራቅክ?… አሁን ደግሞ ሊጥ ምናምን እያልክ ታጣጥላለህ። ለማጣጣል የተፈጠረ ሰው..›› ብሎ ተሰማ በድጋሚ ረዥም ሳቅ ሳቀ።

ዘውዴ ተቆጣ፤ ‹‹እንዴ…ምን ለማለት ፈልገህ ነው? እኔ ላደንቅ ሳይሆን የመጣሁት ፈረሳውን ላይ ነው። አንተም በእኔ ቦታ ላይ ብትሆን ከኔ በላይ አማራሪ ትሆን ነበር።›› አለው። ግልጽ እኮ ነው፤ ‹‹ አንተ ከመተቸት እና ከማማረር ውጭ የምታውቀው ነገር የለም እያልኩህ ነው። እኔማ እየተሠራ ያለውን አይቼ አደንቃለሁ። ገብረየስም በተመሳሳይ መልኩ የሚደነቀውን ያደንቃል፤ ክፍተት ካለም ይናገራል። አንተ ግን በቅድሚያ ራስህ ያለብህን ችግር ሳታይ የሌላ ሰውን ለዛውም የሚሠራ ሰውን ጉድፍ ተራራ አሳክለህ ትተቻለህ። ሰው በመሥራቱ እንደተጎዳህ እያሰብክ ትብሰከሰካለህ። አልፈህ ተርፈህ ትበሳጫለህ። አሁን ፈረሳው ቢኖርም ካሳ አለ። ፈረሳው ለውበት እንጂ ለማጥፋት አይደለም። ነገር ግን አንተን የሚታይህ ፈረሳው ብቻ ነው። የነገው ውበት አይታይህም። ሰዎች እየደከሙ እየሠሩ ያለው ሥራ ፍፁም አይታይህም።…›› ሲል ተሰማ ምላሽ ሰጠው።

ዘውዴ እንደገና በስጨት ብሎ፤ ‹‹ጭራሽ አትናገር እያልከኝ እኮ ነው። ያየሁትን እና የታዘብኩትን እንዳልናገር ለምን ታሳቅቀኛለህ፤…›› እያለ ሲቀጥል፤ ተሰማ በበኩሉ ‹‹ አትናገር አላልኩም። ነገር ግን ስትናገር መናገር ባለብህ ጉዳይ ላይ ብቻ ይሁን እያልኩህ ነው። ሁሉንም ነገር ማጣጣል፤ ሁሉንም ነገር መተቸት እና መቃወም አንተንም ትዝብት ላይ ይጥልሃል። አልፎ አልፎም ቢሆን ሚዛናዊ ለመሆን ሞክር፤ መልካሙን ነገር መልካም ነው በል›› አለው።

ዘውዱ በበኩሉ፤ ‹‹ እንደኔ እምነት ከሆነ ደግሞ መጥፎ ነገርን ካዩ ያስተዋሉትን እና የታዘቡትን መናገር፤ መጥፎ ተግባር አይመስለኝም።›› ብሎ ከመናደድ ይልቅ ፈገግ አለ። ሁልጊዜም በጣም ሲናደድ ደም ስሮቹ ተወጣጥረው ተገታትረው ሲጨርሱ ወደ ቦታቸው ይገባሉ። ተንፈስ ብለው ይጠፋሉ። የዛን ጊዜ ዘውዴ ፈገግ ይላል። ‹‹ ወደው አይስቁ አለ ሰውየው ለካ ወደህ አልሳቅክም። አሁን መናደዴን ትቼ መሳቅ ጀምሬያለሁ።›› ብሎ ዘውዴ ከመሃል ወጥቶ ወደ መንገዱ ቀኝ መራመዱን ቀጠለ።

ወደ ቀኝ ሽሽቱን የቀጠለው በተከታታይ አፈር የጫኑ ትልልቅ መኪኖች እያለፉ በመሆኑ ነው። አልፈው እንደጨረሱ ድምጹን ከፍ አድርጎ፤ ‹‹ አፈር የጫኑ መኪኖች ሊቀብሩኝ ሲሉ አመለጥኳቸው።›› አለ። ተሰማ ሲስቅ በዘውዴ የእጅ ስልክ የሚሰማውን ድምፅ በቅርበት ከግራ እና ከቀኝ እየተራመዱ ያሉ መንገደኞች ድረስ ይሰማል። ዘውዴ የእርሱም ሆነ የተሰማ ንግግርን መንገደኛ ሊሰማ እንደሚችል ሲያውቅ ተሳቀቀ። በተለይ እርሱ ሲናገር የነበረውን አስታወሰና ከአካባቢው ቶሎ መራቅ ፈለገ።

‹‹መንገዱ እንኳን ለእንደአንተ ዓይነቱ ባለመኪና ለእኔ ለእግረኛውም ምጥ ሆኖብኛል። መጥተህ ብታየው ደስ ይለኝ ነበር።..›› እያለ ሲናገር፤ በመሠራት ላይ ያለውን መንገድ ጨርሶ ታክሲ ተራ ደርሶ ነበር። ጫማውን አየት ሲያደርግ ሶሉ በጭቃ ከላይ ቆዳው በአቧራ እጅግ ቆሽሿል። ‹‹ትንሽ ቆይቼ እደርሳለሁ። አንተ ለገብረየስ ድረስለት።›› ብሎ ጫማውን ማስጠረግ ፈለገ። ግራ ቀኝ ሲመለከት ከሩቅ ጫማ ጠራጊውን አየው እና ጠራው። ጫማ ጠራጊው እግር ማስቀመጫ ሳጥኑን በቀኝ በኩል ብብቱ ውስጥ ከቶ በግራ እጁ ነጭ ሁለት ሊትር የምትይዝ ባልዲ ቢጤ አንጠልጥሎ ሮጦ መጣለት። ዳር ይዘው ዘውዴ ቆሞ ጫማ ጠራጊው ተንበርክኮ የዘውዴ ጫማ መፅዳት ጀመረ። ዘውዴ ‹‹መቀመጫህ የት ነው መቼም አፍርሰውብህ ነው አይደል?›› ብሎ ጠየቀው። ልጁ ፈገግ ብሎ ወደ ላይ ጥርሱን አንጋጦ፤ ‹‹አይ እኔ አልፈረሰብኝም። ሥራ የጀመርኩት ሰሞኑን ነው፤ ቋሚ ቦታ ገና እየፈለግኩ ነበር ።›› በማለት ምላሽ ሰጠው።

‹‹አዬ አሁንማ በቃ ምንም ማድረግ አትችልም። እንኳን አንተ ቀድመውህ ወደ ሥራ የገቡትም አቅቷቸዋል።›› ሲለው፤ ልጁ ፈገግ ብሎ ጫማ መጥረጉን ቀጠለ። ዘውዴ ግራ ገባው፤ ‹‹..ምነው ሳቅክ?…›› አለው። ‹‹ልጁ አይ ለጊዜው ብዙ ችግር አላጋጠመኝም እንደውም ከገመትኩት በላይ እየሰራሁ ነው።›› አለው። ዘውዴ፤ ‹‹ ነገሩማ መንገድ እንሰራለን ብለው መንገዱን ማጨማለቃቸው የሰውን ጫማ እያቆሸሸው ለአንተ ገበያው ደርቶልሃል። … እንደውም ለአንተማ ዓለም ነው።›› ሲለው ጫማ ጠራጊው ፈገግ ብሎ፤ ‹‹ለእኔ ብቻ አይደለም፤ ጓደኞቼም የተለያዩ ዕድሎችን እያገኙ ነው። ከፍራሽ ሥር የወዳደቀ ዕቃ እያገኙ እየሸጡ ሳያስቡት እየሠሩ ነው። እኔም ይኸው ያለ እረፍት እየጠረግኩ ገንዘብ እያገኘሁ ነው? ጥሩ ነገር ጥሩ ነው።…›› አለ።

ዘውዴ በጫማ ጠራጊው ተበሳጨ። እግሩን መንጭቆ ለመሔድ ፈለገና መልሶ ተወው። ‹‹…ጥሩ ነገር የምትለው ምንድን ነው?›› ሲል ጠየቀው። ልጁ የዘውዴ ብስጭት አልገባውም። ፈገግታውን ሳይቀንስ ‹‹…አላዩትም እንዴ ጋሼ? እንዴ አበባ እና ወንበር የተተከለበት ቦታ እንዴት እንደሚያምር?…›› ሲል ዘውዴ ልጁ ጥሩ ነው ብሎ የተናገረው ነገር ስላላየው እና የሚሠራውም ስልገባው ፀጥ አለ።

ልጁ ምላሽ ሲያጣ አላቆመም፤‹‹…በእግሮት ሲመጡ የሚያምረውን አካባቢ አላዩትም? ነገሩ ‹ልብ ካላየ ዓይን አያይም› ትል ነበር እናቴ፤ እርስዎም ሌላ ሃሳብ ውስጥ ሆነው አላዩትም ማለት ነው።›› ብሎ የጫማ መጥረጊያ ሳጥኑን በብሩሹ መታ መታ አደረገው። ዘውዴ ግራ እግሩን አውርዶ ቀኝ እግሩን ሰቀለ። ‹‹ …አዎ! የሚሠራውንም ሆነ የተሠራውን ልቤ አላየውም።›› ብሎ ንግግሩን አቁሞ ጫማውን አስጠርጎ ሲጨርስ ታክሲ ይዞ ወደ እነ ተሰማ ሄደ። ልጁ እንደርሱ በምሬት አለመናገሩ ከንክኖታል። እዛ አካባቢ ያለ በሙሉ የመንገድ ሥራውን ይተቻል፤ ያጣጥላል፤ አልፎ ተርፎ ብስጭቱን ይገልፃል ብሎ ቢገምትም፤ ከሚተቸው ይልቅ ዝም የሚለው አዘነበለበት። አንዳንዶች ጭራሽ አድናቆታቸውን ሲገልፁ ሲሰማ ራሱን ከመጠራጠር ይልቅ የእነርሱን ጤነኝነት በጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገባ።

ዘውዴ እነገብረየስ አጠገብ ሲደርስ አላዩትም፤ ገብረየስ ‹‹የሠራ ሰው ምን ጊዜም መተቸቱ አይቀርም። ዋናው ነገር መሥራቱ ነው። መሥራት ከተጀመረ ክፍተትም ቢኖር እየተስተካከለ ይሄዳል።›› ሲል፤ ተሰማ በበኩሉ ዘውዴ መምጣቱን በማየቱ ‹‹…ወቀሳ ከሰሳ እና ጣት መጠቆምን እንደመደበኛ ሥራ ከመቁጠር ይልቅ ለመሥራት መሞከር ይሻላል።›› አለ። ዘውዴ በሁለቱ መሃል ባለው ወንበር ላይ እየተቀመጠ ‹‹ ማን ያሠራን?›› የሚል ጥያቄ አቀረበ። ‹‹ሰርቼ ከመመስገን ይልቅ በተገላቢጦሽ ከመተቸት አምልጬ አላውቅም።›› አለው። ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹እንዳንተ ትችትን ፈርቶ ያልሠራ ወደኋላ ይቀራል። ትችትን ፈርቶ ከመሥራት ወደኋላ ያላለ ደግሞ ሥራው ሲገለጥ መመስገኑ አይቀርም። ዋናው ጉዳይ በጥራት ሕዝብን በሚጠቅም መልኩ በደንብ አስቦ እና አቅዶ ዘመን ተሻጋሪ ሥራ መሥራት ነው። ምስጋናን መጠበቅ ያስቸግራል። ችግሩ አንተ እና አንተን መሰሎች ለመተቸት እንጂ ለመሥራት እና ለማድነቅ አልተፈጠራችሁም።›› አለው።

ዘውዴ ‹‹…መች እድሉ ተሰጥቶኝ አልሠራም አልኩ?›› ብሎ ጠየቀ። ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ዕድሉም ቢሠጥህ ዓይንህ ለማየት አልተዘጋጀም። እጆችህ ስህተት ለመጠቆም እንጂ ለሥራ አያበረቱም። ዓይንህ የሚከፈተው የሚሠሩ ሰዎችን ክፍተት ባይኖር እንኳ ክፍተት ፈልፍሎ በማየት ለመተቸት እና ለማማረር ብቻ ነው። ዓይንህ በመጋረዱ እንድትጎርሰው የቀረበልህን ምግብ እንኳ ለማየት አልታደልክም። በማማረር እና በማጥላላት ለውጥ ማምጣት አትችልም። ሥራ ይሰጠኝ ብለህ ማንንም መጠበቅ የለብህም። ትልቁ መፍትሔ ወደ ራስህ ተመለስ። ሃሳብህን ሰብስብ የምትሠራውን ለይና ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራን ፈፅም። አቅምህን በማማረር አትጨርሰው።…›› አለው።

‹‹አይ!… መክረህ ሞተሃል። መነሻ ገንዘብ የሰጠህ ይመስል፤ ለማዘዝም ትፈልጋለህ። ሚሊየነር የነበረ ሰው እየከሰረ እኔ የምሠራው ምን ይዤ በምን መነሻ ነው?›› አለ። ገብረየስ ፈገግ አለ። ‹‹መነሻህንማ መያዝ ያለብህ ራስህ ነህ። ደርሰህ ተሰማ ጋር የመነሻ ገንዘብ ለማግኘት መሞከር ትክክል አይደለም። ሥራም፤ ገንዘብም፤ ሃሳብም ከሰው አትጠብቅ።

እውነት ነው ሰው የሠራውን እያየህ ከምታጣጥል አንተ የተሻልክ መሆንህን ሠርተህ አሳይ።›› ሲለው፤ ዘውዴ ለገብረየስ ‹‹…እንዴ! አንተም አልገባህም እንዴ?›› ብሎ ጠየቀው። ገብረየስ በበኩሉ፤

‹‹ያልገባኝ ምኑ ነው?›› ሲል ጥያቄውን በጥያቄ መለሰው። ‹‹በእኔ በኩል ሕዝብ የሚያመሰግነውን ሥራ ለመሥራት ዕድሉ አለኝ ብዬ አላስብም።….›› ብሎ ሲናገር፤ ተሰማ ፈገግ ብሎ፤‹‹ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም። አንተ ራስህ አምነህ የማትሠራውን ሥራ ሰው ሠርተሃል ብሎ ሊያሞግስህ አይችልም። በቅድሚያ ለመሥራት አስብ ከሰው ምስጋናን አትጠብቅ። በራስህ ጉዳይ ላይ ተጠመድ፤ ደጋግሜ የምነግርህ ለማማረር እና ለማጥላላት ስትል አትድከም። በየትኛውም መስክ ለሰዎች ለመሥራት ዕድሉ አለህ። ሁሉንም ነገር በመጥፎ መልኩ አትመልከት።›› አለው።

ዘውዴ በረዥሙ ተነፈሰና የሚጠጣውን አዞ፤ በሃሳብ ጭልጥ ብሎ ፈዘዘ። አጠገቡ ያሉትን ተሰማ እና ገብረየስን ረሳቸው። እነርሱም እርሱን ትተው የራሳቸውን ጨዋታ ጀመሩ። ዘውዴ ግን መናገሩን አቁሞ ማሰቡን ቀጠለ። ስለራሱ መመራመር ፈለገና ፤ ሰዎች እርሱን እንዴት እንደሚያስቡት በተጨባጭ እንዲያስረዱት ለማወቅ ፈለገ።

ከጓደኞቹ ለመጀመር አሰበና ገብረየስን ‹‹የእኔ መለያ ምንድን ነው?›› ሲል ምላሽ ጠየቀ። ገብረየስ ‹‹ማር የማይጠማት እንደተባለችው ዓይነት ነህ። ምንም ትልቅ ነገር ለአንተም ሆነ ለሌሎች ቢሠራ የአንተ ሚና ትችት መሰንዘር ብቻ እንደሆነ አድርገህ ታስበዋለህ። ከዚህ አንፃር እኔ የማይህ እንደ አንድ ተቺ ሰው ነው።›› ሲል ምላሽ ሰጠው። ዘውዴ፤ ‹‹ ተሰማም ቅድም እንዲህ ብሎኝ ነበር። በርግጥ እኔ ከመሥራት ይልቅ የማውቀው ትችት እና ማማረር ብቻ ነው?´ ብሎ ራሱን ጠየቀ የራሱን ምላሽ ለመስማት አልፈለገም። ይሄ በሽታ እንደተጠናወተው ለማወቅ እና ከበሽታው በቀላሉ ለመገላገል አልፈለገም። ለጊዜው ብተወው ይሻለኛል ብሎ መጠጣቱን ቀጠለ።

ምሕረት ሞገስ

 

Recommended For You