የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ- በወሳኝ ምዕራፍ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2016 ዓ.ም የውድድር ዘመን በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ ስታድየሞች እየተካሄደ ለመጠናቀቅ ሰባት የጨዋታ ሳምንታት ብቻ ይቀሩታል። ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአስገራሚ ክስተቶች እና በአስልጣኞች ስንብት ታጅቦ የ23ተኛ ሳምንት የጨዋታ መርሀ ግብሩን አጠናቆ የ24ተኛ ሳምንት ላይ ይገኛል።

ቀጣይ የሚካሄዱት ሰባት ጨዋታዎች የሊጉን ዋንጫ የሚያነሳ እና ወደ ታችኛው የሊግ እርከን የሚወርደውን ክለብ የሚለዩ በመሆናቸው ተጠባቂ ፉክክሮች ይስተናገዱበታል ተብሎ ይጠበቃል።

መስከረም 20/2016 ዓ.ም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መካሄድ የጀመረው የዘንድሮ የሊጉ ውድድር በድሬዳዋ የተወሰኑ ሳምንታት ጨዋታዎችን በማድረግ ቀጣይ ማረፊያውን በሀዋሳ አድርጎ ፍጻሜን በአዲስ አበባ ስታድየም ያደርጋል። ከመጫወቻ ሜዳ ደረጃ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ቅሬታ በተወሰነ መልኩ የተሻሻለ ቢመስልም ከክለቦች የደመወዝ ክፍያ፣ ከአሰልጣኞች ስንብት፣ ከክለቦች ውጤት ማሽቆልቆል እና ከዲሲፕሊን ግድፈቶች ጋር ተያይዞ አሁንም ሊጉ ከወቀሳዎች አልራቀም።

በብዙ ፈተናዎችና ተስፋን በሚፈነጥቁ ጉዳዮች መታጀቡን የቀጠለው የፕሪሚየር ሊጉ ፉክክር የአንጋፋና ውጤታማ ክለቦች እንደወትሮ በአስደናቂ የአሸናፊነት መስመራቸው ላይ አለመገኘት፣ አዲስ ዋንጫ ተፎካካሪ ክለቦችን የፈጠረ ይመስላል። በዚህም መሰረት ፕሪሚየር ሊጉን በማሸነፍ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ እንዲሁም በፕሪሚየር ሊጉ በመቆየት በቀጣይ የውድድር ዓመት በከፍተኛ የሀገሪቱ ሊጉ እርከን ለመፎካከር የሚደረገው የክለቦች ፍልሚያ የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ ስቧል።

ዋንጫውን ለማንሳት አራት የሊጉ ክለቦች ተፎካካሪ ሲሆኑ ስምንት ክለቦች ከሊጉ ላለመውረድ እየተፎካከሩ ይገኛሉ። የሊጉ ክስተት የሆነው አዲስ አዳጊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ መቻል፣ ባህርዳር ከተማ እና የተከታታይ ሁለት ዓመታት ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዘንድሮ ዋንጫ የሚደረገውን ፉክክር በቀዳሚነት እየመሩ የሚገኙ ክለቦች ናቸው። በእነዚህ ክለቦች መካከል ያለው ተቀራራቢ የነጥብ ልዩነት እና በቀጣይ ሰባት ጨዋታዎች በሚያስመዘግቡት ውጤት የሊጉ ቻምፒዮን የመሆን እድልን ይዘዋል።

በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው አዲስ አዳጊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጀመሪያው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዓመት አስገራሚ የሚባል ብቃትን በማስመልከት ለሊጉ ክብር የሚደረገውን ፉክክር በቀዳሚነት እየመራ ይገኛል። ክለቡ ለፉክክሩ እራሱን ለማጠናከር በክረምቱ በርካታ ጠንካራ ተጫዋቾችን ማስፈረሙ ጠቅሞታል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማን የመሳሰሉት ያለፉት ዓመታት ጠንካራ ተፎካካሪዎች ደካማ የውድድር ዘመን ማሳለፋቸው ንግድ ባንክ ባደገበት ዓመት ዋንጫ አልሞ እንዲጫወት መንገድ ከፍቶለታል። ካደረጋቸው 23 ጨዋታዎች 14 አሸንፎ፣ 5 አቻ ወጥቶ እና አራት ሽንፈት በማስመዝገብ በ47 ነጥቦችና 19 ጎሎች ይዞ በመሪነት ስፍራው ተቀምጧል። በመጨረሻ ዓመት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ያልገጠመው ሲሆን ሁለቱን አቻ በመውጣት ሶስቱን ጨዋታዎች ድል አድርጓል።

የንግድ ባንክ ተፎካካሪና ዘንድሮ ሊጉን ለማሸነፍ ከምንጊዜውም በላይ ጠንካራ በመሆን መቅረብ የቻለው መቻል በሶስት ነጥቦች ዝቅ ብሎ በሁለተኛነት ይከተላል። አንጋፋውን እና የመሃል ሜዳ ጥበበኛ የሆነውን ሽመልስ በቀለን የቡድኑ አካል በማድረግና ሌሎች ጥሩ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች በማካተት ለፉክክሩ እራሱን በማዘጋጀት ለዋንጫው እየተፎካከረ ይገኛል። በሃያ ሶስቱ ጨዋታዎች 13 ድል፣ 5 አቻ እና አምስት ጊዜ ሽንፈትን በማስተናገድ ዘጠኝ ጎሎችንና 44 ነጥቦችን ይዞ በሁለተኝነት ለዋንጫ የሚደረገው ፍጥጫ እየደመቀ ነው።

ባህርዳር ከተማና የአምናው ባለድል ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩላቸው የዋንጫ ፉክክሩን የአራት ክለቦች እንዲሆን በማድረግ ከላይ ካሉት ሁለት ክለቦች እኩል የማሸነፍ እድል አላቸው። ፈረሰኞቹ ዘንድሮ በሜዳና ከሜዳ ውጪ ባሉ ችግሮች ደካማ የሚባል የውድድር ዘመን እያሳለፉ ቢሆኑም ዋንጫውን ለሶስተኛ ተከታታይ ዓመት ለማንሳት እስከ መጨረሻው ይፋለማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ባህርዳር በበኩሉ ባለፉት ቅርብ ዓመታት ጥሩ የሊጉ ተፎካካሪ ክለብ መሆኑን በማንሳት ዘንድሮም ዋንጫውን ለማንሳት የተሻለ ተስፋ ሰንቋል። በ11 ድል፣ 5 ሽንፈትና በ7 የአቻ ውጤቶች 40 ነጥቦችን ይዞ 3ኛ ደረጃውን ተቆናጧል። ፈረሰኞቹ በ14 ጎሎች እና በ39 ነጥቦች አራተኛ ደረጃን ቢይዙም የዋንጫ ተስፋቸው አልተሟጠጠም።

የሃያ አራተኛ ሳምንት መርሀ ግብር ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ቀጥሎ የሚካሄዱ ሲሆን፤ ክለቦቹ ለቻምፒዮንነትና ላለመውርድ የሚፋለሙ ይሆናል። በሊጉ ለመቆየት በሚደረገው ትንቅንቅ ሀምበሪቾ ዱራሜ፣ ሻሸመኔ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ይፋለማሉ። በሂሳባዊ ስሌት ሀምበሪቾ ዱራሜ ቀዳሚው ወራጅ ክለብ ይመስላል። የሌሎች ክለቦች የመውረድ ስጋት ቢኖርባቸውም፣ ከቀሩት ጨዋታዎችና ሊመዘገቡ ከሚችሉት ውጤቶች ላይ ሊመሰረት ይችላል።

ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማ ከአንድ ዓመት ከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መመለሳቸው ይታወሳል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You