በኦሮሚያ ክልል በመጪው ክረምት አምስት ሺህ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ለመገንባት ታቅዷል

አዲስ አበባ፦ በኦሮሚያ ክልል በመጪው የክረምት ወቅት አምስት ሺህ የቅድመ አንደኛ እና አንድ ሺህ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱ ተገለጸ።

የኦሮሚያ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የዜግነት አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ መሀመድናስር አባጀማል (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በኦሮሚያ ክልል በዜግነት አገልግሎት አምስት ሺህ የቅድመ አንደኛ እና አንድ ሺህ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በዘንድሮው ክረምት ለመገንባት ታቅዷል።

የግንባታው ወጪ በዜግነት አገልግሎት በሚሳተፉ በጎ ፈቃደኞች፣ ባለሀብቶች፣ በጎ አድራጊ ተቋማትና በውጭ ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች እንደሚሸፈን የገለጹት መሀመድናስር (ዶ/ር)፤ ትምህርት ቤቶቹ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሕጻናትን ተቀብለው ማስተማር እንዲችሉ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የግንባታው ዓላማ በክልሉ በገጠራማ የሚገኙ ዜጎች የትምህርት ተደራሽነት ማስፋት መሆኑን አመልክተው፤ ይህም በስነ ምግባር የታነጹ፣ ሀገራቸውን የሚወዱና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት ያስችላል ብለዋል።

በመጪው ክረምት ወቅት ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስና መሰል ድጋፎች እንደሚደረጉም ጠቁመው፤ በክልሉ የዜግነት አገልግሎት ሥራዎች ዓመቱን በሙሉ የሚከናወን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ መሀመድናስር (ዶ/ር) ገለፃ፤ በመጪው ክረምት ወቅት አካባቢን ጥበቃን በተመለከተ አምስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል፣ በትምህርት ዘርፍ ከትምህርት ቤት ግንባታ በተጨማሪ ዘጠኝ ሺህ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ለመስራት እና ሰባት ሺህ ስድስት መቶ የሕጻናት መጫወቻ ለመስራት ታቅዷል።

በማህበራዊ አገልግሎት ስራዎች የአቅመ ደካማ ቤቶችን የመስራት፣ ከተሞችን የማጽዳት እና የተዘጉ የውሃ ፍሳሽ ቱቦዎችን የማጽዳት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸው፤ በዘንድሮው በጀት ዓመት እስከ 10ኛ ወር ድረስ ከ42 አይነት በላይ የዜግነት አገልግሎት ሥራዎች ተሰርተዋል። ይህም በገንዘብ ከ105 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነው ብለዋል።

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የዜግነት የአገልግሎት ስራዎች በአዋች ቁጥር 219 /2011/ሐምሌ ስምንት ከታወጀ በኋላ እስከ አሁን 268 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን በገንዘብ የሚገመት ስራዎች ተሰርተዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You