ግጭቶችን ለመፍታት ለግጭት የሚዳርጉ አመለካከቶችንና አስተሳሰቦችን የመቀየር ሥራ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን ፈትቶ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ማህበረሰቡን ለግጭት የሚዳርጉ አመለካከቶችንና አስተሳሰቦችን የመቀየር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ የሆኑት አቶ ፍሬሰንበት ወልደትንሳኤ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን ፈትቶ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ማህበረሰቡን ለግጭት የሚዳርጉ አመለካከቶችንና አስተሳሰቦችን የመቀየር ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

በሀገሪቱ የተከሰቱና እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች መንስኤዎቻቸው በቅርብ ዓመታት የተፈጠሩ ሳይሆኑ ለበርካታ ዘመን ሲከባለሉ የመጡ ናቸው ያሉት አማካሪው፤ ችግሮችን ከመሰረታቸው ፈትቶ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሰፊውን ማህብረሰብ የማወያየት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የዜጎች የፍላጎት መለያየትና መቃረን በሀገሪቱ እየተከሰቱ ካሉ ግጭቶች ጋር የሚያያዝ ነው ያሉት አማካሪው፤ ግጭቶችን ለመፍታት ለግጭት የሚዳርጉ መሠረታዊ ጉዳዮች የመለየት ሥራ ተሠርቷል፤ የተለያዩ ለግጭት የሚዳርጉ ጉዳዮችም ላይ ማህበረሰቡን የማወያየት ሥራ በሰፊው እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በወሰን፣በውሃና በሃይማኖት ልዩነቶች ላይ የሚታዩ አንዳንድ አለመግባባቶች፣ ጽፈኝነት፣ድህነትና የመሳሰሉት እንዳንግባባ ያደረጉን የግጭት መንስኤዎች ናቸው ያሉት አቶ ፍሬሰንበት፤ የግጭት ችግሮችን ለመፍታት ማህበረሰቡን የሰላም ባለቤት የማድረግ ሥራም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ግንባታና ሀገራዊ መግባባት ሥራ የአንድ ወቅት ሥራ አይደሉም፤ ይልቁንም ለረዥም ጊዜ የሚሠሩ ቋሚ ሥራዎች ናቸው ያሉት አማካሪው፤ ዘላቂ ሰላምን አስፍኖ ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት ለግጭት፣ ለመገዳደልና ለሁከት የሚዳርጉ አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን የመለወጥ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ግጭቶችን ለመፍታት ማህበረሰቡ ራሱ የራሱን ችግሮች አይቶ የሚፈታበት፤ ከአቅሙ በላይ የሆነውን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በማቅረብ እንዲቀረፍለት የማድረግ ተግባር እንዲያከናውን የማወያየት ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

‹‹ ግጭቶች ቢከሰቱም የግጭት መፍቻ በሆኑ ባህላዊ እሴቶቻችንን በማዳበር ልንፈታቸው ይገባል›› ብለዋል፡፡

ባህላዊና ዘመናዊ የግጭት መፍቻ መንገዶችን በማቀናጀትና በማዳበር ዘላቂ ሰላም ለመገንባትና ሀገራዊ መግባባትን በማህበረሰቡ ዘንድ ለማስረፅ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሰላም ጥቂት ሰዎች የሚያመጡት ዋንጫ አይደለም፤ ሁሉንም ማህበረሰብ ይመለከታል፤ የሰላም ባለቤትም ራሱ ሕዝቡ ነው፤ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው አይደለም፤ ከዚህ አኳያ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡

ማህበረሰቡ ሰላሙን ከሚነሱ አላስፈላጊ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ራሱን በማራቅ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርበታል ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You