በቢሾፍቱ የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ቢሾፍቱ:- ድጋፍና እንክብካቤ ለአካል ጉዳተኞች በተሰኘው ማህበር በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ድጋፍና እንክብካቤ ለአካል ጉዳተኞች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ አስፋው በተለይም ለኢፕድ እንደገለጹት፤የአይነ ስውራን ትምህርት ቤቱ በኦሮሚያ ክልል መንግሥትና በቢሾፍቱ ከተማ መዘጋጃ ቤት ፍቃድ በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ለማህበሩ በተሰጠው አንድሺህ 800 ካሬ ሜት ቦታ ላይ ያረፈ ነው።

ትምህርት ቤቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የስምንት ወር ጊዜ የፈጀ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ለግንባታውም በአጠቃላይ 10 ሚሊዮን ብር ወጪ መሆኑ ተጠቁሟል። የግንባታው ወጪም በኔዘርላድ ድርጅቶችና ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንደተሸፈነ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ማእከሉ በአንድ ጊዜ እድሜያቸው ከ6 እስከ 13 የሚሆኑ 30 አይነስውራን ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም እንዳለውም ገልጸው፤ ከቅድመ መደበኛ እስከ አራተኛ ክፍል ደረጃ እንደሚያስተምርም ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባት ቀደም ሲል በቢሾፍቱ ዙሪያ ካሉ አካባቢዎችና ከተለያዩ ክልሎች ለሚመጡ የአይነስውራን ሕፃናት በተበጣጠሰና በኪራይ ይሰጥ የነበረውን የትምህርት አገልግሎት በአንድ ማዕከል ለመስጠት እንደሚያስችለው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

ማህበሩ ላለፉት አስራ አንድ ዓመታት አካል ጉዳተኞች ከተቀረው ኅብረተሰብ ጋር በትምህርት፣ በጤና ፣የሥራ ስምሪትና ሌሎች መስኮች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታዎችን ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ገልጸዋል ።

በእነዚህ ዓመታትም ማህበሩ በዘረጋው የትምህርት አገልግሎት መርሀ ግብር በመቶዎች ለሚቆጠሩ አይነስውራንና የእይታ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሕፃናትንና ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን አብራርተዋል ።

አሁን በቢሾፍቱ ከተማ የከፈተው የአይነስውራን ትምህርት ቤትም ማህበሩ የዘረጋውን የትምህርት መርሀ ግብር ለማስፋትና ተጓዳኝ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችለው መሆኑን ጠቁመዋል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You