በመዲናዋ በአካባቢ ብክለት በዓመት አንድ ሺ 600 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ

አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ በአካባቢ ብክለት የተነሳ በዓመት አንድ ሺ 600 ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በአካባቢ ብክለት ምንነትና ሁለንተናዊ መከላከያ ስልቶች ላይ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ለማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፣ ለአትሌቶችና ለታዋቂ ግለሰቦች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ትናንት አካሂዷል።

በወቅቱ የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ በዓለም ጤና ድርጅት ከተቀመጠው መስፈርት(ስታንዳርድ) በስድስት እጥፍ ያደገ ብክለት አለ። ይህ ብክለት የተፈጥሮ ሀብቶችን ጭምሮ በመጉዳት የትውልዱ ጤና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል።

በከተማዋ አብዛኛው ኢንዱስትሪዎችም ሆኑ ተቋማት ፍሳሾቻቸውን ወደ ወንዝ እንደሚለቁ አመላክተው፤ ይህም የውሃ ብክለትና የአፈር ብክለት እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

በመዲናዋ በአየር፣በውሃ፣በአፈርና በፕላስቲክ ብክለት ምክንያት በዓመት አንድ ሺህ 600 ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ጠቅሰዋል።

የአካባቢ ብክለቱን ለመከላከል ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚቆይ ንቅናቄ በከተማ አቀፍ ደረጃ የተጀመረ ሲሆን፤ በዚህም ከሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሰዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታቅዷል ብለዋል።

በባለስልጣኑ የአካባቢ ብክለት ጥበቃ ሕግ ተከባሪነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ጉዴታ በበኩላቸው ባቀረቡት ጥናት እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ በየዓመቱ በተለያዩ የአካካቢ ብክለቶች አማካኝነት አንድ ሺ 600 ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ።

60 በመቶ የሀገሪቷ ኢንዱስትሪዎች በአዲስ አበባና አካባቢዋ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ከኢንዱስትሪዎቹ የሚለቀቁ ፍሳሾች አትክልቶችን በመበከል ከፍተኛ የጤና ጉዳት እያስከተሉ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በገዳይነታቸው ከሚታወቁ 10 በሽታዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ምክንያታቸው የአካባቢ ብክለት ነው ያሉት አቶ ለሜሳ፤ ማህበረሰቡም ይህንን ችግር በአግባቡ በመገንዘብ የአካባቢውንና የራሱን ጤና ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።

በከተማ አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘው ንቅናቄም የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ያለመ መሆኑን ገልጸው፤ ባለስልጣኑ በየወሩ በእያንዳንዱ የብክለት ዓይነቶች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንደሚያከናወን አመላክተዋል።

በዚህም በሚያዝያ ወር የፕላስቲክ ብክለት ላይ ግንዛቤ መፈጠሩና በግንቦት ወር ደግሞ የአየር ብክለት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You