ከግንቦት አንድ ጀምሮ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን አገልግሎት ዲጂታላይዝድ ይደረጋል

አዲስ አበባ፡- ከግንቦት አንድ ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን አገልግሎት ዲጂታላይዝድ እንደሚደረግ የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በፌዴራል መንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት የድኅረ ትራፊክ አደጋና መድን አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጫላ ፈይሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ተቋሙ አገልግሎቱን ቀልጣፋ እና የመረጃ አያያዙን በማዘመን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡

አገልግሎቱ በተለይም ሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን እና የአስቸኳይ ሕክምና ተዘዋዋሪ ፈንድ አገልግሎትን ለማዘመን ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን አዲስ ሶፍትዌር አልምቷል ብለዋል፡፡

አቶ ጫላ፤ ተቋሙ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም የሙከራ ትግበራው በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተማ መደረጉን ገልጸው፤ እስካሁን በሥርዓቱ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

በሙከራ ትግበራው ያጋጠመ ችግር ባለመኖሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዷል ያሉት አቶ ጫላ በግንቦት ወር መጀመሪያም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ የሚያጋጥሙ ችግሮች ካሉም ማሻሻያዎች እየተደረጉ የሚቀጥሉ ይሆናል ብለዋል፡፡

ይህ የአሠራር ሥርዓት አራት ዋና ዋና ችግሮችን እንደሚቀርፍ የተናገሩት አቶ ጫላ፤ የመጀመሪያው የሦስተኛ ወገን ተለጣፊ በፌዴራል ደረጃ ታትሞ ተደራሽ ለማድረግ ረጅም ጊዜ የሚወስድና በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚወጣበት ነበር። አሁን ግን ሥርዓቱ አንድ ሰው ባለበት ሆኖ ክፍያ በመፈጸም አገልግሎት ማግኘት የሚያስችለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ተቋሙ በቀላሉ የተለጣፊዎቹን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ሁለተኛው ለካሳ ክፍያ ከተገልጋዮች የሚሰበሰበውን አረቦን ክፍያ ከዚህ ቀደም ረጅም ሂደት የነበረው ሲሆን ሥርዓቱ ክፍያውን በቀላሉ በቀጥታ ወደ ተቋሙ እንዲገባ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሌላው ሥርዓቱ የነፃ አስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት ክፍያ እና አደጋ ሲደርስ በፍጥነት እና በአግባቡ መረጃ መሰብሰብ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

ሥርዓቱ ከወጪ፣ ከጊዜ እንዲሁም ከመረጃ አያያዝ አንጻር የሚያመጣው ጥልቅ ለውጥ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል አቶ ጫላ፡፡

በተጨማሪ ተቋሙ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን ብሔራዊ የመንገድ ትራፊክ አደጋ መረጃ ሥርዓት (national road accident data manage­ment ) የተሰኘ ሶፍትዌር አልምቶ ሙከራ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ጫላ፤ ይህ ሥርዓት ከዚህ ቀደም ተቋሙ ከመረጃ አያያዝ ጋር ተያይዞ ከዓለም ጤና ድርጅት ሲቀርብበት የነበረውን ቅሬታ የሚያስተካክልና በተቋሙ የሚሠሩ ሁሉንም መረጃዎች በአግባቡ የሚመዘግብ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You