ኮርፖሬሽኑ በኦዲት ሪፖርት የተገኙ ጉድለቶችን እንዲያርም ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

አዲስ አበባ፡- የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኦዲት ሪፖርት የተገኙ ጉድለቶችን እንዲያስተካክል አሳስቧል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በበኩሉ በክዋኔ ኦዲስ የተገኙ ጉድለቶችን ለማስተካከል እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የኮርፖሬሽኑን የ2014/15 በጀት ዓመት ክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ በትናንትናው ዕለት ውይይት አካሂዷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) በኮርፖሬሽኑ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት በርካታ ጉድለቶች መገኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ኮርፖሬሽኑ የዘር ስርጭትና የገበያ ተደራሽነትን ሊያሰፋ ሲገባው በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆኖ በመሥራቱ በሚፈለገው መጠን የምርጥ ዘር ምርት ማቅረብ አልቻለም፡፡

በስትራቴጂክ እቅድ መሠረት የተለያየ ዓይነት የጓሮ አትክልት ዘሮችን ለሽያጭ ለማቅረብ ያቀደ ቢሆንም በ2012 ዓ.ም ከዕቅዱ ዜሮ ነጥብ ዜሮ ስምንት እንዲሁም በ2013 እና 2014 ዓ.ም ምንም ማቅረብ ያልቻለ መሆኑም በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የኦዲት ሪፖርቱን መነሻ አድርጎ እንደገለጸው፣ ኮርፖሬሽኑ ለደንበኞች ከሰጣቸው የዱቤ ሽያጭ ወይም የድህረ ክፍያ አገልግሎት በውል መሠረት መሰብሰብ አልቻለም፡፡

በግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ ስር ከሚፈጽ ማቸው ተግባራት መካከል የቴክኒክ ሥልጠና አገልግሎት አንዱ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ አፈጻጸሙ ግን እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

ከ2012 እስከ 2014 በጀት ዓመት ከምርጥ ዘር እና ከአግሮ ኬሚካል ጋር በተያያዘ ከተካሄደው ምርምር በስተቀር በእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት ላይ የተሠራ ሥራ አለመኖሩም ኦዲት ሪፖርቱ አሳይቷል።

በኮርፖሬሽኑ የሚፈጸሙ ግዢዎች የኮርፖሬሽኑን የግዢ መመሪያ የተከተሉ አለመሆናቸው፣ ኮርፖሬሽኑ ለመጋዘን ግንባታ የሚሆን በቂ ይዞታ እያለው ለመጋዘን ኪራይ ወጪ ማውጣቱ፣ የግብርና ማሽነሪዎች አያያዝ ለብልሽት በሚዳረጉበት ሁኔታ መሆኑንና ሌሎችንም ጉድለቶች አስመልክቶ ቋሚ ኮሚቴው ማብራሪያ እንዲሰጠውና በቀጣይም አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡

በኮርፖሬሽኑ የግብርና ግብዓት ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰሎሞን ገብሬ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ዋነኛ ዓላማው የግብርና ግብዓቶችን ለገበሬው ማቅረብ ነው ያሉ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ ሥራዎች ማከናወኑን አንስተዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የካፒታል አቅም ውስንነትና ከውጪ ምንዛሪ መዘግየትና ማነስ ጋር የተያያዙ ችግሮች ኮርፖሬሽኑ በእቅዱ ልከ እንዳይጓዝ ተግዳሮት ሆኖበታል ብለዋል፡፡

የተገኙ ጉድለቶችን የኦዲት ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ በማስተካከል ሂደት ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You