አገልግሎቱ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ሰበሰበ

– አንድ ሺህ 200 ሐሰተኛ ሰነዶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አድርጓል

አዲስ አበባ፦ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አንድ ሚሊዮን 237 ሺህ 329 ተገልጋዮችን በማስተናገድ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ። አገልግሎቱ አንድ ሺህ 200 ሰነዶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማድረጉንም ገልጿል።

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ስለሺ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ የቴምብር ቀረጥ እና የአገልግሎት ክፍያ ያስከፍላል። በዚህም በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት አንድ ሚሊዮን 237 ሺህ 329 ተገልጋዮችን በማስተናገድ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ሰብስቧል።

አገልግሎቱ በዘጠኝ ወራት ከ715 ሺህ 500 በላይ ልዩ ልዩ የውል ሰነዶችን ማረጋገጥ ችሏል። በቀን በአማካኝ ስድስት ሺህ 400 ተገልጋዮች ይስተናገዳሉ ያሉት አቶ ሰለሞን፤ በዚህ ሂደት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ግለሰቦች ሐሰተኛ ሰነዶችን ይዘው ወደ አገልግሎቱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

አንድ ሺህ 200 የማንነት ማረጋገጫ መታወቂያና የጋብቻ ማስረጃዎች ሐሰተኛ ሰነዶች በመሆናቸው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተደርገዋል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ከዚህ ውስጥ 996 የማንነት ማረጋገጫ መታወቂያዎች፣ 165 የጋብቻ ማስረጃዎች እና ቀሪው ልዩ ልዩ የውል ሰነዶች ናቸው። በዚህም 28ቱ ለፖሊስ ቀርበው ሦስት ክስ ተመስርቶባቸዋል ብለዋል።

አብዛኛው ሐሰተኛ ሰነድ የአዲስ አበባ የቀድሞውን መታወቂያና ያላገባ ማስረጃ አስመስለው ለመሥራት የተደረጉ መሆናቸውን ከተያዙ ሰነዶች መረዳት ተችሏል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ እነዚህ ማስረጃዎች የቀሩና በቴክኖሎጂ አሠራር የተተኩ በመሆናቸው በቀላሉ ሊያዙ ችለዋል ብለዋል።

አገልግሎቱ ከፍትሕ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ ወንጀሎችን ለመከላከል በቀን ከስድስት ሺህ በላይ ሰነዶች ሕጋዊነታቸው ይረጋገጣል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ በአሁኑ ወቅት ሐሰተኛ ሰነድን በመጠቀም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ከባንኮች እና ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአገልግሎቱ ሰነዶች ለባንኮች፣ ለመሬት አስተዳደር፣ ለመኪና ሽያጭ ውሎች፣ ለፍትሕ አካላት እና ለተለያዩ ተቋማት ማስረጃነት እንደሚያገለግሉ የጠቆሙት አቶ ሰለሞን፤ የአገልግሎቱ ሰነዶች “ባር ኮድ” እንዲኖራቸው በማድረግ በቀላሉ ተመሳስለው እንዳይሠሩና ሰዎች እንዳይጭበረበሩ ተደርጓል ብለዋል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ፤ የአገልግሎቱ አሠራር በዲጂታል እየታገዘ ነው። የሰነድ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ሰነዶች በአግባቡ ሊያዙና ሊፈተሹ ይገባል። ይህም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች የበኩሉን አስተዋፅዖ ያደርጋል። ከዚህ አንፃር የአገልግሎቱ ሐሰተኛ ሰነዶችን የማረጋገጥ አቅም ተጠናክሯል።

በቀጣይም ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ትስስር በመፍጠር ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሠራም ገልጸው፤ በሐሰተኛ ሰነድ ሐሰተኛ ማንነት የሚቀርብበት ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታትም ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በጥምረት እየሠራ ነው ብለዋል።

በ2015 በጀት ዓመት ለአገልግሎት ቀርበው የተያዙና አገልግሎት እንዳይሰጥባቸው የተደረጉ የማንነት ማረጋገጫ መታወቂያ አንድ ሺህ 509፣ የጋብቻ ማስረጃዎች 178 እና ሌሎች ልዩ ልዩ ሰነዶች 36 በድምሩ አንድ ሺህ 723 ሐሰተኛ ሰነዶች መያዛቸውን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ አምና ለአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ ተገልጋዮች አገልግሎት መስጠት መቻሉን የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ሰለሞን ስለሺ አውስተዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You