ፎረሙ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች በንግድና ኢንቨስትመንት በጋራ እንዲሠሩ ዕድል ይፈጥራል

አዲስ አበባ፡- የንግድ ፎረሙ የኢትዮጵያ እና የኬንያ ዜጎች በንግድና ኢንቨስትመንት በጋራ እንዲሠሩ መንገድ እንደሚከፍት የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የኬንያ አምራቾች ማኅበር በጋራ ያዘጋጁት የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ከትናንት ጀምሮ ለሦስት ቀናት እየተካሄደ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሽንቁጤ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የፎረሙ ዓላማ የሁለቱ ሀገራት ዜጎች በንግድና ኢንቨስትመንት በጋራ የሚሠሩበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው፡፡

በፎረሙ ላይ የኬንያ ኢንቨስተሮች እና በአምራች ዘርፍ የተሠማሩ ባለሀብቶች መገኘታቸውን የገለጹት፤ ፕሬዚዳንቷ፤ ኢትዮጵያ ይበልጥ በአምራች ዘርፍ ለመሠማራት ፍላጎት ያላት በመሆኑ ፎረሙ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያግዛል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኬንያ ፓርላማ አባላት በፎረሙ መገኘታቸውን ጠቁመው፤ ይህም የፓርላማ አባላቱ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ መቀየር የሚገባቸውን ሕጎችና አዋጆች ከንግድ ማኅበረሰቡ ቀርበው በመስማት እንዲሻሻሉ አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸው ዕድልም ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ይህን እንደግብዓት በመውሰድ ምክር ቤቱ በቀጣይ በፓርላማው ለመሳተፍ ጥያቄ እንደሚያቀርብ እና ምክር ቤቱ ዓለም አቀፍ ተቋም እንደመሆኑ በአፍሪካ ኅብረት እና በሌሎች በዓለም ሀገራት በሚካሄዱ ጉዳዮች የኢትዮጵያን የግል ዘርፍ ወክሎ ለመሳተፍ አሳብ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ መሰንበት እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ እና የኬንያ የንግድ ግንኙነት ሲነጻጸር ኬንያ ከ60 በመቶ በላይ ምርቶቿን ወደ ኢትዮጵያ ትልካለች፡፡ ከኢትዮጵያ ምርቶችን ወደ ኬንያ የምትልክ ቢሆንም ከኬንያ ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው፡፡

በቀጣይ ይህ እንደዚህ አይቀጥልም። ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ነፃ የንግድ ቀጣና በመጠቀም ወደ ሌሎች አገራት ምርቶቿ ለመላክ መሥራት ይኖርባታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ ኦሪያና በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ፎረሙ የኢትዮጵያ እና የኬንያ መንግሥት ባደረጉት ስምምነት መሠረት፣ የኬንያ ባለሀብቶች በንግድና ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ያሉ ዕድሎችን እንዲረዱ ያስችላል፡፡

የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት አሁንም በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ ማደግ ይችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት በሁለቱ ሀገራት የሚደረገው የንግድ ሁኔታ ዝቅተኛ እንደሆነ የተገለጸ መሆኑን አውስተው፤ በዚህም የሁለቱን ሀገራት የንግድ እንቅስቃሴ እንዴት ማሳደግ ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ከንግድ ማኅበረሰቡ ጋር እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You