በመንግስት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ተቋማትን በሁሉም ወረዳዎች ተደራሽ ለማድረግ በተያዘው በጀት ዓመት አስር ተቋማት እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ በመንግስትና በግል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አዳዲስ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን በተያዘው እቅድ መሰረት በተያዘው በጀት ዓመት በመንግስት ኮሌጅ 275 ሺ 671 እና በግል ኮሌጆች ደግሞ 92 ሺ 254 በድምሩ 367 ሺ 925 ሰልጣኞች ከደረጃ አንድ እስከ አምስት በመሰልጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ ስልጠና ካጠናቀቁት ውስጥ 44 ሺ 627 ሰልጣኞችን ከስራ ጋር ለማስተሳሰር እቅድ ተይዞ 47 ሺ 331 ሰልጣኞች ስራ እንዲይዙ ተደርጓል፡፡
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስትቲዩት በ2003 ዓ.ም ላይ በሚኒስተሮች ምክር ቤት በአዋጅ 245/2003 የቴክኒክና ሙያ መምህራንና አመራሮችን ለማሰልጠን የተቋቋመ ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ እንዲመሰረት ዋነኛ ምክንያት የነበረው ተወዳዳሪና ብቃት ያላቸው የቴክኒክና ሙያ መምህራንን የሚያፈራ ተቋም ባለመኖሩ ነው፡፡ በተጨማሪም ብቁ የሆኑ የቴክኒክና ሙያ ኃላፊዎችን ስታንዳርዱን በጠበቀ መልኩ የሚያፈራ ተቋም አልነበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ በአገሪቱ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለሚገኙ መምህራን ስልጠና የሚሰጥ ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በኢንስቲትዩቱ በመጀ መሪያ ዲግሪ አውቶሞቲቭ፣ ኮንስትራክሽን፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙንኬሽን ቴክኖሎጂ እና ማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ መስጠት የጀመረ ሲሆን ከተከፈተ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ሬልዌ እና ሰርቬይ ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ማስተማር ጀምሯል፡፡
በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኢንስትቲዩት አዲስና ነባር መደበኛ አሰልጣኝ፣ አመራርና ኢንዱስትሪ ቴክኒሻን ስልጠና ቅበላው በተቋሙ የተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ሰልጣኞች እየሰለጠኑ ሲሆን በዚህ መሰረት በመደበኛ ዲግሪ 903፣ በሁለተኛ ዲግሪ 421፣ በክረምት መርሃ ግብር ዲግሪ አንድ ሺ አምስት መቶ 69፣ በማስተርስ 101 ሲሆን ጥቅል ቅበላ በሁሉም ማሰልጠኛ ተቋማት ሶስት ሺ ሃምሳ ሶስት ሰልጣኞች ይገኛሉ፡፡ እኛም በኢንስትቲዩቱ የስራ እንቅስቃሴ ዙሪያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኩሪያ ንጋቱ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
የዘንድሮ ትምህርት አሰጣጥ እንደማንኛውም ከፍተኛ ትምህርት በተመደበው ወቅት ተጀምሯል፡፡ በኢንስትቲዩቱ የትምህርት መቆራረጥ አልነበረም፡፡ ሰልጣኞቻችን ከስራ ላይ የሚመጡ በመሆናቸው ወይም ባሉበት ተቋም የቴክኒክ እና ሙያ አሰልጣኞች ናቸው። ለዚህም የትምህርት እንቅስቃሴው በተፈለገው አቅጣጫና መርሃ ግብር መሰረት ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ተቋሙ ከሌሎች የሚለየው ስልጠናው የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ እንደመሆኑ በተግባር የሚደገፍ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በተሳካ ሁኔታ ተሰጥቷል፡፡ በአሁን ወቅት በኢንስትቲዩቱ ዘጠኝ ሺ የሚሆኑ ተማሪዎች ይገኛሉ፡፡ ተማሪዎቹ በዋናው ግቢ የሚሰለጥኑና በየክልሎች በሚገኙ ኮሌጆች ውስጥ በዲግሪ መርሃ ግብር የሚማሩትን አካቶ ነው፡፡ በዲግሪ መርሃ ግብር በትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ በ15 ኮሌጆች ትምህርት ይሰጣል፡፡
ከቴክኖሎጂ ፈጠራ
ኢንስትቲዩቱ ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ ቴክኒክና ሙያ ዘርፉን በማዘመን የኢንዱስትሪ ሽግግር ማምጣት የሚችል የሰው ሃይል ማፍራት ነው፡፡ በቴክኒክና ሙያ መማር ማስተማሩ ዘርፍ ላይ ያሉ አሰልጣኞችን በአገሪቱ ላይ ላሉት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የሰለጠነ ሰው ማፍራት እንደዚሁም ቴክኒክና ሙያ ዘርፉን የሚመሩ አመራር ማፍራት ሌላኛው ተልዕኮ ነው፡፡ የአገሪቱን ኢንዱስትሪ ሽግግር ወይም ቴክኖሎጂ በመቅዳት የኢንዱስትሪ ሽግግር ማምጣት ነው፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ስራ ላይ የተፈለገውን ያክል አልተከናወነም፡፡ በቅርቡ የዘጠነኛ ወር አፈጻጸም በተገመገመበት ወቅትም ኢንዱስትሪን መቅዳትና ማሸጋገር ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ታይቷል፡፡ ይህን ለማስተካከል በይበልጥ እየተሰራ ይገኛል። የመጀመሪያው ትኩረት አሰልጣኞችን የማፍ ራት ወይም ብቁ አመራሮችን ለማፍራት በቴክኒክና ሙያው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ኢንዱስትሪ መቅዳት ላይ ትኩረት አለመሰጠቱ ታይቶ ጠንካራ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
አርሶ አደሩን የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎች የተሸጋገሩ አሉ፡፡ ለምሳሌ ያክል የእርሻ ማሽን በኢንስትቲዩቱ ባሉ አሰልጣኞች እንዲሰራ ተደርጎ በአማራ ክልል በባህርዳር በሚገኘው ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኩል እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ በደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ላይ ደግሞ የመጨረሻ ሙከራው ታይቶ የተሰጡ ግብዓቶች እንዲጨመሩ ተደርጎ የበለጠ አርሶ አደሩን ለመጥቀም ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በክልል በሚገኙ ኮሌጆች በአካባቢያቸው ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡ በአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአካባቢውን ችግር ለመፍታት በአባያና በጫሞ ሀይቅ ላይ የተነሳውን የእምቦጭ አረም የሚያጠፋና ዘመናዊ የአሳ ማጥመጃ ጀልባዎች ተሰርተዋል። በኮምቦልቻና በማይጨው የተሰሩ ስራዎችም አሉ፡፡ በየአካባቢው ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ብዙ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ነገር ግን የወጡት ቴክኖሎጂዎች የህብረተሰቡን ችግር የሚቀርፉ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ያሉት ጅምሮች አጠናክሮ በመቀጠል ቴክኖሎጂዎችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ስራዎች ይቀጥላሉ፡፡
በሰልጣኞች የሚሰሩ የምርምር ስራዎች
በኢንስትቲዩቱ ውስጥ የቴክኖሎጂ ዘር ፎች ላይ ስልጠና እንደመሰጠቱ የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች ብዛት ባይኖራቸውም በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ በማህበራዊ ሳይንሱ በተለይ በትምህርት አመራር ትምህርት ክፍል ውስጥ የምርምር ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ በአራቱ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ እና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ሰርተው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ሰልጣኞቹ መምህራን በመሆናቸው ወደ ፖሊ ቴክኒክና ወደ የቢሮዎቻቸው ሲመለሱ በደረጃ የሚማሩ ሰልጣኞች የተሻሉ ስራዎችን እንዲሰሩ የሚያደርጉና የሚያበረታቱ እንዲሆኑ የበጀት እጥረቶች አሉ፡፡
ለምርምር ስራ ከፍተኛ የሆነ ወጪ ስለሚያስወጣ በቡድን እንዲሰሩ ይደረጋል። አንዳንድ ፕሮጀክቶች ደግሞ በግል እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡ በአገሪቱ ለምርምር ስራ ለተማሪዎች ምን ያክል ገንዘብ መሰጠት አለበት ተብሎ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ገንዘብ ተሰጥቶ ተማሪዎች ስራዎቻቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። በዚህ ላይ አንዳንድ ተማሪዎች የሚያነሷቸው ክፍተቶች አሉ፡፡ የምርምር ስራዎቻቸውን ለማከናወን እቃዎች ጠይቀው በፍጥነት ተገዝቶ ያለመቅረብና እንዲገዙ የተጠየቁት የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች ወይም አንድ ቴክኖሎጂ ለመስራት የሚያስችሉ እቃዎችን ለመግዛት ወደ ገበያው ሲወጣ የሚገኘው እቃ የሚፈለገውን ያክል አይደለም፡፡ ለዚህም ተማሪዎች በፈለጉት ጊዜ እቃዎችን እያገኙ አይደለም፡፡
ተመራቂዎችን ከመከታተል
ኢንስትቲዩቱ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን በተለያዩ ጊዜያት ያከናውናል፡ ፡ በአገሪቱ ባሉት ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ በግልም በመንግስትም ያሉት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን የክትትልና ድጋፍ ስራው በአራቱም አቅጣጫ በዓመት ሁለት ጊዜ ይከናወናል፡፡ በዚህ ክትትል ስራ ሰልጣኞችን፣ አሰልጣኞችንና አመራሮችን በአካል የማግኘት ነገር ይኖራል። በወቅቱ ያሉትን ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ በአጠቃላይ በሚደረጉ የክትትልና ድጋፍ ስራ ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ላይ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ አሰልጣኞችን ለመሰልጠን ወደ ኢንስትቲዩቱ ሲመጡ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች የሚናገሩት በአብዛኛው የትኩረት ማነስ እንዳለ ነው። በተለይ እንደመደበኛው ትምህርት ወይም እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመንግስት የሚሰጠው አይነት ትኩረት አይሰጠውም። ብዙዎች ወደ ግል ስራ ወይም የስራ ፈጠራ መሸጋገሪያ እንደመሆኑ መጠን በግላቸው ስልጠናውን ፈልገው የሚመጡ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ሰልጣኞች ተምረው ከጨረሱ በኋላ ወደ ሌላ ቦታ የመግባት ሁኔታዎች አሉ።መንግስት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶባቸው ወደ ፖሊ ቴክኒክ ገብተው ከማስተማር ይልቅ ወደ ግል ኮሌጆች የመፍለስ ነገሮች በስፋት ይስተዋላሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011
መርድ ክፍሉ