ወጣት ሴቶችን ለማብቃት የወጣት ማርታ ሕልም

ሌሎችን የምትረዳበትን መንገድ መፍጠር የልጅነት ሕልሟ ነው:: ይህ ፍላጎቷ ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ገና በአፍላ እድሜዋ ነበር ከጓደኞቿ ጋር በመሆን መጽሓፍት የማግኘት እድል የሌላቸውን ተማሪዎች ለመርዳት አነስተኛ ቤተ መጻሕፍት ለመክፈት ያስቻላት::

መጻሕፍት ባነበበች፣ ፊልም ባየች ቁጥር ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ስትመለከት ሴቶችን መርዳት የምንግዜም ምኞቷ ነበር:: እናም ይህ ምኞቷ ፍላጎት ብቻ ሆኖ አልቀረም፤ ዛሬ ላይ በውስጧ የበቀለው ሴቶችን የመርዳት ዓላማ አድጎ፤ ወጣት ሴቶች ላይ የሚሰራ በጎ አድራጎት ድርጅት እስከማቋቋም ደርሳለች::

በዛሬው የሴቶች ዓምድ እትማችን የሀገር አቀፍ ወጣት ሴቶች በጎ አድራጎት ድርጅት መስራች እና አስተዳዳሪ የሆነችውን ወጣት ማርታ ማሙዬን ተሞክሮ እናካፍላለን::

ወጣት ማርታ አዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ አካባቢ ተወልዳ ያደገች ሲሆን፤ ሁሉንም የትምህርት ደረጃዎችን ያጠናቀቀችው እዚሁ ከተማ ነው:: የመጀመሪያ ዲግሪዋን በኮምፒውተር ሳይንስ ከተማረች በኋላ፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ለማጠናቀቅ ችላለች::

“በልጅነቴ መጻሕፍትን ሳነብ፣ ፊልሞችን ስመለከት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ነገሮች ያሙኛል:: ከዚህ ጋር ተያይዞ የነበረኝ ቁጭት እያደገ መጥቶ ነው መሰለኝ ሁልጊዜ የማስበው በሴቶች ላይ መስራት ነው:: ሴቶችን የሚያግዝ በብቃት፣ በሥራ ፣ በዓላማ ጠንክረው እንዲወጡ የሚያግዝ ትልቅ ሥራ መስራት እመኝ ነበር “ትላለች::

በልጅነቷ አራት ኪሎ አካባቢ ቤተ መጻሕፍት እንዳ ቋቋመች ትናገራለች ፤ ለዚህ ደግሞ ያነሳሳት፤” ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል እየተማርን ቤተመጻሕፍት ስንሄድ ስለሚሞላብን መጻሕፍ ተከራይተን ነበር የምናነበው:: መጻሕፍ ለመከራየት ከሆነ ቤተሰብ ገንዘብ ለመስጠት ስለማይጨክን ለምነንም ቢሆን ተቀብለን እንከራያለን:: ነገር ግን ተከራይቶ ለማንበብ አቅሙ የማይፈቅድለት ተማሪ አለ:: ” ስትል ትናገራለች::

እናም ማርታ እነዚህ ከፍለው መጻሕፍ መከራይትና ማንበብ የማችሉ ተማሪዎች ነገር ስለሚያሳስባት፤ ሁሌ ሰፊ ቤተመጻሕፍ ቢኖር እያለች ትመኝ የነበረው:: ምኞቷ ወደ እውነታው ተቀየረና ስምንተኛ ክፍል ስትደርስ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም በቃች::

ተከራይተው ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎችን ለመርዳት ቤተመጻሕፍት ማቋቋም እንደምትፈልግ ነገረቻቸው :: በወቅቱ እንዲያነቡ የተፈቀደላቸው ቤተ መጻሕፍ ነበር እና ሌሎች ተማሪ ጓደኞቻቸው ማንበብ እንዲችሉ አስፈላጊ የሆኑ መጻሕፍትን በማሟላት ወደተሟላ ቤተ መጻሕፍትነት ቀየሩት::

“በቤተ መጻሕፍቱ እኛም እናነባለን ሌሎች ተማሪዎችም ገብተው መጠቀም ስለጀመሩ እየሰፋ መጣ:: ቤተመጻሕፍቱ እየሞላ ተከራይተን ወይም ውጪ ድንጋይ ላይ እየተቀመጥን በማንበብ መቸገራችንን በማየት፤ ከትምህርት ቤት ውጭ አንድ የወጣቶች ቤተመጽሓፍት ነበረና እዛ እንድናነብ ተፈቀደልን:: “ትላለች::

“በቤተመጽሀፉ የትምህርት መጻሕፍትን ጨምሮ የተለያዩ ልቦ ወለዶች እና ታሪካዊ መጻሕፍቶች ነበሩ:: ከዛን ወደ ሰብሳቢው በመሄድ ዝም ብለው የተቀመጡ መጻሕፍት ይሸጡና፤ እኛ ለትምህርታችን የሚያዘጋጀንን ወቅታዊ መጻሕፍት እናምጣ ብለን አማከርነው:: “በማለት ትገልጻለች::

በዚህ ሁኔታ በቤተመጻሕፍቱ የተለያዩ መጽሓፍ እንዲሟላ አደረጉና ሌሎች ተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚጠቅማቸው መጻሕፍት እንዲያገኙ መንገድ ከፋች ለመሆን በቁ:: ቤተ መጻሕፍቱን ለሌሎች ተማሪዎች በሚሆን መልኩ የማደራጀቱ ሀሳብ መጀመሪያ ላይ የማርታ ቢሆንም፤ ከዛ በኋላ ስትሰራ የነበረው ምኒልክ፣ መድኃኒያለም እና ናዝሬት ትምህርት ቤት ከሚማሩ ጓደኞቿ ጋር ነበር:: እነ ማርታ በቤተ መጻሕፍቱ እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ ከሰሩ በኋላ ለተቋሙ አስረክበው:: አሁን ላይ ያ ቤተ መጻሕፍቱ መፍረሱን ትናገራለች::

ማርታ ሌሎችን ለመርዳት ካላት ፍላጎት ባለፈ ኪነጥበባዊ እና ስፖርታዊ ነገሮች በጣም ስለሚስባት በእንደዚህ አይነት መርኃ ግብሮች ላይ ትሳተፍ ነበር:: አፍላ እድሜ ላይ እያለች በሞዴሊንግ እና ኪነጥበባዊ ጉዳዮች ላይ ከመሳተፍ በተጨማሪ ማርሻል አርት ላይ ለአምስት ዓመት ተሳትፋለች::

“ትምህርት እና ኪነ ጥበብ እያልኩ ባድግም፤ ሁሌም የሴቶች ነገር ውስጤን ይነካዋል:: ከራሴ ጋር አነጻጽራለሁ፤ እኔ መሃል ከተማ አራት ኪሎ ተወልጄ ሴቶች ላይ የሚደርሱ አንዳንድ ተጽዕኖዎችን ስመለከት፤ ሌሎች አካባቢዎችስ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚለው ያሳስበኛል:: “ትላለች::

እነዚህ ነገሮች ስታስብ ሴት ወጣቶች ላይ ብዙ ነገር ለመስራት ሀሳብ አደረባት:: በትምህርት እና ስልጠና ግንዛቤዋ እያደገ ሲመጣ የራሷን በጎ አድራጎት ድርጅት ከመክፈቷ በፊት በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ በመሳተፍ የምታገለገል ሲሆን፤ ከእነዚህ ተቋማት ጋር ስትሰራ ፕሮፖዛሎችንም ታዘጋጅ ነበር::

“የአመራርነት እና ሌሎች የተለያዩ አይነት ስልጠናዎች በየግዜው ስወስድ አቅሜን እያዳበርኩ መጣው:: ዲግሪዬን ስማር በኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን እሳተፍ ስለነበር አመራር ሆኜ ተመረጥኩ:: “ስትል ትናገራለች::

በፌዴሬሽኑ አመራር ሆና ስትመረጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሴት ወጣት አመራሮች እና ሙያተኞች የሚል ዘርፍ እንዲቋቋም አደረገች:: በዚህም በየክልሉ በርካታ ወጣቶችን በማግኘት የግንዛቤ ሥራ ለመስራት ቻሉ :: ከዛን እሷ የዘርፉ ሰብሳቢ እንድትሆን ተደረገ::

ማርታ በፌደሬሽኑ ስትመራው የነበረችውን ዘርፍ፤ እንደ መደበኛ ድርጀት ለመክፈት ሀሳብ አደረባት:: ከሶስት ዓመት በፊት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ካጠናቀቀች ከአንድ ወር በኋላ፤ አሁን የምትመራውን ሀገር አቀፍ ወጣት ሴቶች በጎ አድራጎት ድርጀት ለማቋቋም ሂደቱን ጀመረች::

“እራሱን የቻለ ድርጀት ለማድረግ ስለፈለኩ አማከርኳቸው እና ተመዝግበን፤ በቦርድ እንዲመራ በማድረግ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ተመሰረት:: ለቀጣይም ትልቅ ዓላማ ነው ያለን::” ስትል ታስረዳለች::

“ድርጅቱን የመጀመር ድፍረቱ የመጣው ሴቶች ላይ የሚያጋጥመውን ችግር ባየው ቁጥር ደፋር እንድሆን አደረገኝ:: እዚህ ቦታ ላይ ተቀምጬ ምን አለ ትንሽ ነገር ማድረግ ብችል የሚለው ሀሳብ ደግሞ ውስጤን ይገፋዋል:: አብረውኝ ያሉ ሰዎች ሀሳቤን ሲቀበሉ ሲደግፉኝ እና አንዳንድ እድሎች ሳገኝ እየተጠቀምኩ፤ ድርጅቱን ወደ መሬት አወረድኩ::” ትላለች::

ማርታ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ተምሬያለሁ፣ ልምድ አለኝ በማለት ተማሪ እያለች ትሰራቸው የነበሩ ሥራዎችን መበተን ከበዳት:: ስለዚህ እንደ ሀገር አሁን የምትሰራውን ሥራ እየሰራች፤ በቀጣይ ደግሞ ሌላ አቅም ለማዳበር ወስና ወደ ሥራው ገባች:: ይህም ውስጣዊ እርካታ እንደሰጣት ትናገራለች::

የድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ብትሆንም፤ የደረሰባቸውን ነገር ለማማከር ስለምትቀላቸው የተለያዩ ወጣት ሴቶች ወደ ማርታ በመምጣት በግልጽ ችግራቸውን ይገልጹላታል :: መፍትሄ መስጠቱ በድርጅቱ አቅም የሚቻል ከሆነ እንዲረዱ የሚደረግ ሲሆን፤ ከእዛ ከፍ ያለ ከሆነ ደግሞ አቅም ካላቸው አካላት ጋር በአፋጣኝ እንዲደርስ ይደረጋል::

“ድርጅቱ በቦርድ የሚመራ እና የራሱ የገንዘብ ስርዓት ያለው ሲሆን፤ ከአንድ አንድ ለጋሾች ከሚገኙ ድጋፎች ባለፈ፤ ፈንድ የማግኘት ነገር በጣም ትንቅነቅ ነው:: በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወዳድረን ድርጅታችን ሲያልፍ የምናገኛትን ፈንድ ያለንን ልምድ እና ግንኝነቶች በመጠቀም በትንሽ ብር በዙ ነገር እንሰራለን::” ትላለች::

ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ የምትገልጸው ማርታ፤ “ትልቁ ዓላማው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና መብት ላይ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ሴት ወጣቶችን ማብቃት ነው:: ልክ እንደ ዓላማው አሁን ድርጅቱ እየሰራ ያለው መሰረታዊ በሆነ መልኩ የሴት ወጣቶችን ሕይወት መቀየር ነው:: “ስትል ትገልጻለች::

ለአብነትም ከሁለት ዓመት በፊት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ከዩኒቨርሲቲ ውጭ ከሰባት የመንግስት አካላት ጋር በመፈራረም፤ በአደንዛዥ እጽና በሌሎች ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ በሚያደርሱ ችግሮች ዙሪያ ለስምንት ወራት በመስራት ከ ስድስት ሺህ 500 በላይ ሰዎች ጋር መድረሳቸውን ታስረዳለች::

“ስልጠናው የተሰጠው በአካባቢው ለሁሉም ማኅበረሰብ ነበር፤ ምክንያቱም ወጣቱ የሚኖረው በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለሆነ ከሱስና ከሌሎች እኩይ ተግባራት ጋር ተያይዞ ግንዛቤው ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ያስፈልገዋል:: ለዚህም የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መንገዶችን አድርገናል::” ስትል ትገልጻለች::

ሌላው በአራዳ ክፍለ ከተማ 15 ድርጅቶች በኮቪድ ምክንያት የተበላሸባቸውን ከአክሽን ኤይድ ጋር በመተባበር ድጋፍ እንዲደረግላቸው አድርገዋል:: ድርጅቱ እነዚህን ድጋፎች ሲያደርጉ በትናንሽ ገንዘብ ለመፈጸም ጥረት ያደርጋል::

በትንሽ ገንዘብ በርካታ ሥራዎችን እንዴት እንደሚያከናውኑ የምትናገረው ማርታ፤ “የመጀመሪያው በማኅበረሰቡ የሚሰሩ ሥራዎችን የራሱ አድርጎ እንዲወስድ ማድረግ ሲሆን፤ ሌላው በሰው ኃይል ረገድ እንደ አስፈላጊነቱ ሰው ይቀጠራል:: እንዲሁም ብቃቱ ያላቸውን በጎ አድራጊዎች በመጠቀም ሥራዎች እንዲሰሩ ይደረጋል::፡” ትላለች:: በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ 175 ወጣቶችን በመለየት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን የወጣቶቹን አቅም በሚያሳድጉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ::

“ድርጅቱ ወጣት ሴቶችን ዓላማ አድርጎ የተመሰረተ ቢሆንም፤ ወጣት ሴቶችን የሚደግፉ ሥራዎች በሚሰሩበት ወቅት፤ ወጣት ወንዶችንም ማካተት አስፈላጊ ስለሚሆን እነሱንም ተደራሽ እናደርጋለን:: ነገር ግን ሴቶች ያላገኙት እድል አለ ብለን ስለምናስብ የምንሰራውን ሥራ ሁሉ በሴቶች ላይ እናጎላለን:: “ስትል ታስረዳለች::

“ከሴቶች ጥቃት ጋር ተያይዞ ሥራዎችን ስንሰራ የአጋር ድርጅቶችን ጥናት ለመመልከት እንሞክራለን:: በዚህም በስፋት የሴቶች ጥቃት በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል ብቻ እንዳለ ነው የሚታሰበው:: ነገር ግን ከተማ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሴቶች ጥቃት ነው ያለው::” ትላለች:: “ከተማ አካባቢ አውቃለሁ በሚል ቀለል ተደርገው የሚታዩ መንገዶች በራሱ ለጥቃት ሰለባ እያደረጉ ነው:: የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን በእራሱ በቀላሉ ለጥቃት እንድንጋለጥ ያደርጋል:: ስልጣኔ እየመሰሉ ወጣቱን ይዘው የሚጠፉ በርካታ ችግሮች አሉ ፤ ይሄ በራሱ ጥቃቱን ያሰፋዋል:: “ስትል ታስረዳለች::

“ከሕግ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶችም ጥቃትን እንዲሰፋ ያደርጋሉ:: በኢትዮጵያ ጥቃትን በተመለከተ የተለያዩ ሕጎች አሉ። እነዚህ ሕጎች በአግባቡ ተፈጻሚ ቢሆኑ መልካም ነው:: ለምሳሌ እንደ ሀገር ጥቃት ያደረሰው አካል እያለ፤ ተጎጂው አካል ነው የሚሸማቀቀው:: ሌሎች ሀገራት ላይ ግን ጥቃት ፈጻሚው ከማኅበራዊ ሕይወቱ ሳይቀር ሊገለል ይችላል :: በጥቃት አድራሾች ላይ የሚሰጠው ብያኔ ከጥቃቱ አንጻር አናሳ ሆኖ የሚታይበት ሁኔታ አለ። ይሄ ደግሞ ጥቃቱ እንዲሰፋ አድርጎታል “ትላለች::

አሁንም ቢሆን ሥራችንን ጀመርን እንጂ አልጨረስንም የምትለው ወጣት ማርታ፤ ብዙ ሊሰራባቸው የሚገቡ፣ ትኩረትን የሚሹ ችግሮች አሉ:: በእነዚህ ረገድ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎች በመስራት ውጤታማ እና ተሳታፊ ወጣቶችን የማብቃት እቅድ እንዳለ ትናገራለች::

ሴቶች ሁሌም አንገታቸውን ደፍተው እንዳይኖሩ ራሳቸውን በትምህርት ማሳደግ አለባቸው:: በግል ጥረት የሚመጣ እውቀት ክፍተትን ስለሚሞላ በሁሉም አቅጣጫ ሙሉ ለመሆን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በእውቀት ላይ የታገዘ የኢኮኖሚ አቅምን መገንባት ደግሞ ወሳኝ መሆኑን ትመክራለች።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You