የትምህርት ተቋማት ዘመንኑን የሚዋጁ፤ ተወዳዳሪና ብቁ ሆነው ከዓለም እኩል የሚራመዱ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ራሳቸውን በዲጅታል ቴክኖሎጂው ማዘመን የግድ ይላቸዋል። ዲጅታል ቴክኖሎጂ በትምህርት ተቋማት ላይ ሙሉ ለሙሉ መተግበር ከተቻለ ብዙ ችግሮች በቀላሉ ይፈታሉ። ለአብነት የሀብት ብክነት ይቀንሳል፤ አሰራሮች ይዘምናሉ፤ ተጨባጭ እውቀት ይመጣል፤ ተወዳዳሪነት ይጨምራል። ‹‹ትምህርት ለሁሉም›› የሚለው መርህ እውን ይሆናል። ከዓለም ጋር በእኩል መንገድ ለመራመድ ያስችላል። ስማርት ትምህርት ቤቶችን በስፋት ለመፍጠርና ለሌሎች አርዓያ የሚሆኑ ተግባራትን ለማከናወንም ሁነኛ እድልን ያመቻቻል።
ይህ ዘመን የግድ ዲጅታል ቴክኖሎጂን የሚጠቀም የትምህርት ማህበረሰብን ይፈልጋል። በዘርፉ የተገነቡ ተቋማትም መኖር የውዴታ ግዴታ እየሆንም መጥቷል። አሁን የትምህርት ማህበረሰቡ በብዙ መልኩ ተለዋዋጭ ሆኗል። ፈጣን የሆነውን ቴክኖሎጂንም መቀላቀል ጀምሯል። በተለይ ወጣቱ ይህንን ዓለም በመቀላቀል ላይ ያለው አቅም በዲጅታል ትምህርቱ ካልታገዘ ብዙ ስብራቶችን ይፈጥራል። ለእርሱ የሚመጥን ትምህርት መስጠት ካልተቻለም እንደ ሀገር የሚታጣው ነገር ይበራከታል። እናም እንደ መንግሥት ይህ ታሳቢ የሆነ ይመስላል። ወጣቱ በተለያየ መልኩ የዲጅታል ትምህርቱን በመጠቀም ጥሩ እድሎችን ለራሱ እየፈጠረ መጥቷል። ይህ ደግሞ በትምህርት አካባቢ ቢደገፍ የበለጠ ውጤታማነቱ ይጨምራል። የተሻሉ እድሎችን ለሀገርም ለተማሪዎችም ማምጣት ይቻላል። ከዚህ አንጻርም እንደ ኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ተጠሪ ዶክተር ካሳሁን ገላና እንዳሉት፤ ዲጅታል ትምህርት ዋነኛ ዓላማው ተማሪዎችን በሚገባቸው መልኩ በተለያየ መንገድ ትምህርቱን እንዲያገኙ ማስቻል ነው። በተለይም ተደራሽነትን አስፍቶ፤ ጥራት ያለው ትምህርት ከመስጠት አኳያ አሰራሮችን ማቅለል ነው። ይህም በኦዲዮ አለያም በቪዲዮና በንባብ ሊሆን በሚችል መልኩ እንዲከታተሉት ማድረግ ላይ በስፋት የሚሰራበት ነው። ቴክኖሎጂው ከትምህርት ቤት አልፎም ትምህርት በተለያዩ ተቋማት ይሰጣልና ትምህርቱ ገደብ ሳይኖረው፤ ወሰን ሳይበጅለት እንዲሰጥ የሚቻልበት እድል ነው። ማለትም አንድ ተማሪ ቤቱ ሆኖ አለያም በሀገር ውስጥ ተቀምጦ ዓለም ላይ ያለውን ትምህርት እንዲከታተልበት አማራጭ ይሰጠዋል።
የትምህርት ዲጅታላዜሽን አስፈላጊነት ከተማሪዎችም ይሻገራል። መምህራንንም በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። አንዱ ዝግጁና አቅም ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ከተለመደ አሰራር እንዲወጡ፤ የውጪውን የመማር ማስተማር ሁኔታን እንዲረዱና ለተማሪዎች በሚመጥን መልኩ ትምህርቱን እንዲሰጡ ማስቻሉ ነው። በተጨማሪም አዳዲስ አሰራሮችን እንዲያውቁና ከዘመኑ እኩል እንዲራመዱም የሚያደርጋቸው ነው።
የትምህርት ዲጅታላይዜሽን ሌላኛው አስፈላጊነት ዜጎች ፈጣሪም ፈጣንም እንዲሆኑ እድል መስጠቱ ነው። መሠረታዊ የሀብት መፍጠርያ ስልቶችን በማመቻቸት፤ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ችሎታዎች ከፍ እንዲሉ ያደርጋል። የተማረውን ኃይል ከፍ በማድረግ የኢንዱስትሪውና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎችን በኢኮኖሚው ላይ ያላቸው ድርሻ እንዲጨምሩም እድል ይሰጣል። መካከለኛና ከፍተኛ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ከመፍጠር አኳያም የማይተካ ሚና አለው። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተበታተነ ሁኔታ በገጠር በመኖሩ ሊከሰት የሚችለውን የትምህርት ተደራሽነት፤ ጥራትና ተወዳዳሪነትን የመሳሰሉ ችግሮች ከመፍታት አንጻርም ሚናው ቀላል እንደማይባልም ይናገራሉ።
ክፍያዎች በእያንዳንዱ ሱቅና ቤት ውስጥ በዲጅታል ሆኗል። አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴው በቴክኖሎጂ እየሆነ መጥቷል። በቀጣይ ደግሞ ማንኛውም ሰው ጥሬ ገንዘብን መጠቀም ሊያቆም ይችላል። ይህ ደግሞ በእውቀት ካልተመራ ከፍተኛ ኪሳራን ያደርሳል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ መሰረቱ ዲጅታል ትምህርቱን ማስፋትና ወጣቱም ሆነ ሌሎቹ ዜጎቻችን የዲጅታል ዓለሙን በዲጅታል ትምህርት እንዲቀላቀሉ ማድረግ ነው። ለዚህም እንደ ሀገር ሙሉ ለሙሉ ትምህርት ቤቶች ዲጅታል ትምህርቱን ተግባራዊ እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው ይላሉ። ከእነዚህ መካከልም ዋና ዋናዎቹ የኤሌክትሪክ ኃይልና ኔቶርክ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ዶክተር ካሳሁን፤ ዲጅታል ቴክኖሎጂው እውን መሆን በጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች ላይ የመጡ ለውጦች እንደ ማሳያነት ይጠቀሳሉ ብለዋል፤ የኔትዎርክ አገልግሎት በሌለባቸው አካባቢዎች ጭምር ነገሮች እየተቀየሩ ነው። ምክንያቱም በዘርፉ በርካታ ተግባራት በመከናወናቸው ተማሪዎች ኔትዎርክ በአለበት ቦታ የጫኑትን ኔትዎርክ በሌለበት ቦታ ላይ እንዲያነቡት እድል ሰጥቷቸዋል። በቪዲዮና መሰል መንገዶች የተቀረጹ ትምህርቶችም በተለያየ የማስተማሪያ ዘዴ እንዲሰጡ ሆኗል። ይህ ደግሞ የብዙዎችን ተማሪዎች ውጤት አሻሽሏል። መምህራንም የማስተማር ስነዘዴያቸውን እንዲቀየሩ እንዳደረጋቸው አንስተዋል።
ነገሩ ፈታኝ ቢሆንም እንደ ኦሮሚያ ክልል ይህ ተግባር በስፋት እየተከናወነ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ካሳሁን፤ የትምህርት ሥርዓቱ ከተቀየረ ጀምሮ የዲጅታል ትምህርቱ የመማር ማስተማር ስራው እንዳይቋረጥ እያገዘና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። ለዚህም ማሳያው 317 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች የዲጅታል ይዘት ተደራሽነት ያላቸው ሲሆን፤ በክልሉ ካሉት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንድ ሦስተኛው የዲጅታል ትምህርት ተግባራዊ ተደርጎባቸዋል። ይህ ገና ብዙ መስራትን የሚጠይቅ እንደሆነም ዶክተር ካሳሁን ተናግረዋል።
በአንዱ ባይሆን በሌላ መልኩ ትምህርት ቤቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል የግድ እንደሆነ ክልሉ ያምናል የሚሉት ኃላፊው፤ አሁን ላይ በክልል ደረጃ ከ5 ሚሊዮን የኮደር ኢንሼቲቭ ጋር ተያይዞ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን እንዲሁም የአስተዳደር ሠራተኞች ዲጅታል ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙበት ለማስቻል ከ320 በላይ ወረዳ ስላሉ በእያንዳንዱ ወረዳ ዲጅታል ፓርክ እንዲቋቋም እየተሰራ ይገኛል። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ፈጣሪም ፈጣንም እንደሚያደርጋቸው ይታመናልም ብለዋል።
የፓርኩ መቋቋም አላማ ከ20 በላይ ኮምፒውተር ያለው ክፍል በመፍጠር እያንዳንዱ ወረዳ አንድ ማዕከል ኖሮት ልጆች ፣ ወጣቶች መጥተው የዲጅታል ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ፤ እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው። ይህ ሁኔታ ዲጂታል ትምህርቱን በክልል ደረጃ ከማስፋት ባሻገር የትምህርት ይዘትን በፓወር ፖይንቶች፣ ኢንተርኔትን በመጠቀም በዚያው ላይ በማንበብ አልያም በመጫን የመጠቀም ሥርዓትን ያሰፋል። ተማሪዎች ተጨማሪ ትምህርቶችንና ማጣቀሻዎችን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ከመዝናናት ባለፈ ትምህርት ነክ ጉዳዮች እንዲከናወኑባቸው በመሆናቸው ሰፊ የትምህርት አማራጮችን እንዲያገኙም መደላደልን ይፈጥርላቸዋልም ሲሉ አብራርተዋል።
ዲጅታል ትምህርት ተማሪዎች የትምህርታቸውን ይዘት ደጋግመው እንዲያነቡ ያስችላቸዋል። ይዘቶቹ መጽሐፍ ላይ ከሚነበቡት በብዙ መልኩ ስለሚለዩ በቀላሉ እንዲረዱት ያደርጋቸዋል። በዲጅታሉ የትምህርት አሰጣጥ ፓራግራፍ፤ ስዕላዊ መግለጫዎች አለያም ቪዲዮና ግልጽ የሆኑ ማብራሪያዎች ስለሚገኙበት መረጃውን በአግባቡ እንዲረዱትና ወደፊትም ከአዕምሯቸው በቀላሉ እንዳይጠፋ ያግዛቸዋል። የማስታወስ ሁኔታዎችንም ይጨምርላቸዋል። ከውጪው ዓለም ጋርም በቀላሉ እንዲገናኙ ይረዳቸዋል። በተለይም የውጪ ሀገር ትምህርቶች በምን አይነት መንገድ እንደሚሰጡ አይተው በዚያ አግባብ እንዲያጠኑ እድል የሚፈጥርላቸው ነው።
የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋቱም በኩል የማይተካ ሚና አለው። ይዘቶችን፤ የማስተማር ዘዴዎችን በቀላሉ ሀገር ውስጥም ሆነ የተለየ ተቋም ላይ ለመተግበርም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ይህ ደግሞ በክልሉ በተፈጠሩ ሁሉም የትምህርት ሁኔታዎች ላይ እየታየ ስለመሆኑም አብራርተው፤ ፓርኮቹ ወደ ሥራ ሲገቡ ደግሞ የበለጠ አቅም እንደሚፈጠርም አስረድተዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የዲጅታል መሰረተ ልማት ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ነው። ከዚህ አንጻርም አቅም በፈቀደ የሚሰራበት ነው። በመሆኑም ኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮም ትምህርትን ዲጅታል ከማድረግ አኳያ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ይህም በሁለት አይነት መልኩ የሚታይ ነው። እነዚህም ሶፍትዌሮችን በማበልጸግና ስማርት ትምህርት ቤቶችን መፍጠር የሚሉት ናቸው። በተጨማሪነት ከመማር ማስተማሩ ጋር በተያያዘም የኮምፒውተር ቤተ ሙከራዎችን ደረጃ የማሳደግ ሥራም ትኩረት ተሰጥቶት ከሚሰራው ተግባር ውስጥ አንዱ ተደርጎ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
የኢንተርኔት መሰረተ ልማትን በተመለከተ እንደ ክልል በስፋት እየተሰራም ነው። ለዚህም በአብነት የሚጠቀሰው የኢ-ለርኒግ ትምህርቶችን የማስፋፋት ሥራ ነው። እነዚህ በተለይ በልዩ ትምህርት ቤቶችና በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ እየተደረጉ ሲሆን፤ ከዚያ ባሻገር በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ላይ የዲጅታል ትምህርቱን ለመተግበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች በየጊዜው የሚጨምሩ ቢሆኑም አሁን ላይ ባለው መረጃ እንደ ኦሮሚያ ክልል ከ46 በላይ ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ዙር 41ዱ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሞከረ እንደሆነ አመላክተዋል።
ሁሉም ላይ በዲጅታል ትምህርት (ስማርት ክላስ) ለማስጀመር ያልተቻለበት ምክንያት ትምህርት ቤቶቹ ከሌሎች ጋር ተደርበው የሚሰራባቸው በመሆናቸው ነው። ራሳቸውን ችለው እስኪወጡና ለእነርሱ የሚገባ መሰረተ ልማት እስኪገኝ ድረስ በአሉበት እንዲቀጥሉ የሚደረግ ይሆናል ያሉት ዶክተር ካሳሁን፤ ስማርት ክላስ ተማሪዎች ምንም አይነት ኖት ሳይዙ በቀጥታ እንዲማሩ የሚያስችላቸው ነው። ስካን በማድረግ ወስደውም ቤታቸው የሚያነቡበትን እድል ያመቻችላቸዋል። በተጨማሪም የሚሰጡት ትምህርቶች በተመረጡ መምህራን ስለሆነ ሁሉም በእኩል ደረጃ ትምህርቱን እንዲከታተሉ ይሆኑበታል።
ተቀርጾ የሚቀመጥ በመሆኑም ሌሎች ቦታዎች ጭምር በማጓጓዝ ተማሪዎች ትምህርቱን እንዲያገኙት የሚችሉበት ነው። የትኛውም ቦታ ላይ ሆነው የሚያስተምሩ መምህራንን በቀጥታ እንዲከታተሉም ይረዳቸዋል። ስለሆነም እንደ ኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ አሁን ላይ በአንድ ትምህርት ቤት ሁለት ሁለት ወደ 82 ክፍሎች እንዲታቀፉ ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል። ሥራው የሚከናወነው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር መሆኑን አስታውቀው፤ በዘንድሮው ዓመት የመሳሪያና መሰል የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ተከላ እየተከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል።
እንደ ኦሮሚያ ክልል የስማርት ክላስ ምስረታን በተመለከተ ደረጃ በደረጃ እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፤ ለስራው እውን መሆን መብራት ያላቸው፣ ኢንተርኔት ያላቸው፣ መሰረተ ልማታቸው በሚል ትምህርት ቤቶች መለየታቸውን አንስተዋል። ስማርት ክፍሎች ቢቀሩም መደበኛ ክፍሎችን በማዘጋጀት የተወሰኑ ኮምፒውተሮችን በማስገባት ዲጅታሉን ትምህርት የሚጀምሩበት ሁኔታም እየተመቻቸ እንደሆነም አመላክተዋል። የተማሪዎችን ክህሎት ከፍ ከማድረጉ ባሻገር የፈጠራ እንቅስቃሴያቸውን በእውቀት እንዲመሩት፤ አዳዲስ ነገሮችን እንዲያዩ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም የሳይበር ክበቦችን በማቋቋም የእርስ በእርስ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ፤ በጋራ የዲጅታል አቅማቸውን እንዲያሳድጉም ፤ ተማሪዎች ለቀጣዩ ዓለም ውድድር ብቁ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራም እየተከናወነ ነው። ይህ እንዲሆንም የተለያዩ ስልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉም ብለዋል።
በዚህ ዘመን ዲጅታል ትምህርት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት በሁሉም ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል ነው። በተለይም ከኢኮኖሚ አንጻር ያሉበትን ችግር ለመፍታት ወሳኝ ነገር ተደርጎ ይወሰዳል። በተማረው ትምህርት ለራሱ የስራ እድልም የገቢ ሁኔታንም የሚፈጥርበት ነው። በተማረው ትምህርት የቀጣይ እጣ ፋንታውንም የሚያስተካክልበት ነው። ከዚያም ባሻገር ዲጅታል ቴክኖሎጂውን ሲያውቁ ይጠቀማሉም ይጠበቃሉም ባይ ናቸው።
ዲጅታል ቴክኖሎጂ አሁን ላይ አንጠቀመውም የሚባል ነገር አይደለም። ለማንኛውም እንቅስቃሴ መሰረታዊ ነገር ነው። ስለሆነም በመጀመሪያ የሰው ኃይሉን በአግባቡ መጠቀም ላይ መስራት ያስፈልጋል። አደረጃጀትን በመፍጠርም አቅም ያላቸውን ሰዎች ወደፊት በማምጣት ትምህርቱን ማጠናከር ይገባል። እውቀቱና ክህሎቱ እንዲዳብርም ወጣቶችንና በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን ከማነቃቃትና ከመደገፍ አንጻር በትኩረት ሊሰራ ይገባል። ከባቢውን በመፍጠርም እድሉ እንዳለ ማሳየት ያስፈልጋል። ለአብነት የቤተሙከራ ደረጃዎችን በማሻሻል፤ የዲጅታል ፓርኮችን በማስፋፋት፤ ወጣቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ በስፋት መስራት አስፈላጊ ነው ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም