ደግነት እና ልግስና በሕይወቱ የሚያስደስተው ትልቁ ተግባር ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ የሚያልመውን ለማሳካት የሚጓዝበትን መንገድ በጥንቃቄ በመምረጥ ‹‹ዛሬ ላይ የልጅነት ሕልሜ ምንም ሳይሸራረፍ እየኖርኩት እገኛለሁ›› ይላል።
የተወለደበት ወቅት በሀገሪቱ ከሥልጣን ለውጥ ጋር ተያይዞ የደርግ መንግስት ማብቂያ ነበር ። በመሆኑም በአዲስ አበባም ሆነ እንደ ሀገር ውጥረትና አለመረጋጋት የሰፈነበት ወቅት ነበር። ለወላጆቹ ሁለተኛ ልጅ የሆነው ሻሎም በጽንስ ውስጥ እያለ የመንግሥት ለውጥ ተደረገ። የነበረው አለመረጋጋት እና ውጥረት ሲረግብ የመንግሥት በለውጡ ማግስት እሱ ተወለደ። ሻሎም የሚለው ስያሜም ተሰጠው በእብራይስጥ ትርጉሙም የማያቋርጥ የእግዚአብሄር ሰላም የሚል ትርጉም አለው ። ሻሎም ያዕቆብ አርኣያ።
እድገቱ ልዩ የሆነ የአብሮነት ተምሳሌት የሚገልጽበት ልጅነቱን ባሳመረለት የጨርቆስ መሀል ሰፈር ነው። ‹‹በልጅነቴ ድሎት ምን እንደሆነ ስለማላውቅ ችግር ምን እንደሆነ አላውቅም። ነገር ግን የደግነትን ጥግ እያየሁ አድጊያለሁ፡፡›› የልጅነት ጊዜው በተለየ መልኩ የሚመለከተው እንዳልነበረ ይናገራል። ዓለም ከሚኖርባት ትንሽ ቤትና ሰፈር ባለፈ ያላትን ገጽታ ለማየት እድሉን አላገኘም። ‹‹ ብዙ ቤቶች መስኮት አላቸው፤ መስኮቱ ግን ለብርሀን ማስገቢያ ወይንም ለንፋስ አልነበረም እቃ ለመዋዋስ እንጂ፡፡›› የሚለው ሻሎም እስከ ስድስት ዓመት ብቻ የኖረበት ነገር ግን የልጅነት ትውስታው ውስጥ ትልቁን ሥፍራ እንደሚይዝ ይናገራል።
ሻሎም በዚህ የልጅነት እና የመቦረቂያ እድሜው በአንዱ ቀን ጠዋት ከፍተኛ የሰዎች ጩኸት እና ሁካታ ከእንቅልፉ ይቀሰቅሰዋል። በአቅራቢያቸው ያለን የመኖሪያ ቤት ቆርቆሮ ለመንቀል የሚታገሉ ሰዎች ነበሩ። ምን እየተካሄደ እንደሆነ ያልገባው ሕጻን ሻሎም አባቱን ጠየቀው። ጎረቤታቸው የሆነ ሰው በማረፉ ምክንያት አስክሬን ለማውጣት ቤቶቹ እጅግ የተጠጋጉ መሆን በሩ ምቹ ባለመሆኑ በጣርያው በኩል አስክሬኑን ለማውጣት እየሞከሩ መሆኑን ከአባቱ መረዳት ቻለ። ይህ ክስተት በልጅነቱ ውስጥ ትልቅ ጥያቄን ጥሎ አለፈ።
ሌላኛው የልጅነት ትውስታው ቴሌቪዥን በቤታቸው የተገዛበት ወቅት ነበር። በቴሌቪዥኑ መስኮት የሚተላለፈው የውጭ ሀገር ፊልሞች ላይ የሚመለከታቸው የአኗኗር ዘይቤዎች ከእርሱ ጋር ፍጹም ተቃራኒ ሆነበት። ለአባቱም ሰዎቹ በቤተክርስትያን ትምህርት ወቅት የሚሰማቸው በአእምሮው የሚስለው መንግስተ ሰማያት ነው እንዴ የሚል ጥያቄ ነበረው። ከአባቱ ያገኘው ምላሽ ልክ እንደሱ በምድር ላይ የሚኖሩ መሆናቸውን ሲረዳ ይህ አይነት ልዩነት በፍጹም ተገቢ እንዳልሆነ እና መቀየር አለበት የሚል ሀሳብ በልቡ ውስጥ ተቀረጸበት። ብዙም ሳይቆይ ወላጆቹ የመኖሪያ መንደራቸውን ቀይረው ሲሄዱ የተሻለ የሚባል ሕይወትን ማግኘት ችሏል። ያጊዜም ለእርሱ ጥሩ ወቅት ነበር።
ሻሎም በልጅነቱ ያስተናገደው አብሮ የመኖር እና የመረዳዳት ባሕል በልቡ ትልቅ ቦታ ነበረው። በመሆኑም በአንድ ወቅት የገና በዓልን ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር ለማክበር የበዓል ማድመቂዎችን ለማሟላት መማከር ጀመሩ። ለሻሎም ግን በዓሉ ከፌሽታ ይልቅ በአከባቢው ከሚመለከታቸው በመንገድ ላይ የሚያድሩ ሕጻናት እና በእምነት ቦታዎች በር ላይ በመለመን ከሚውሉት ጋር በሕብረት ማሳለፍ ፍላጎቱ ነበር። ሻሎም በጊዜው ከክፍል ጓደኞቹ በእድሜ ትንሹ ቢሆንም በሀሳቡ ተስማምተው ከየቤታቸው ያሰባሰቡትን የምግብ ግብዓቶች ተባብረው በመስራት ነድያንን በማብላት አሳለፉ። ይህ አጋጣሚ ሻሎም በሕይወቱ እጅግ የተደሰተበት ጊዜ ነበር ።
በማግስቱ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ እነዚህ ነድያን ሁልጊዜም እዛው መቆየታቸውም አልተዋጠለትም። የሕይወት ዓላማውም ይህ ሊሆን እንደሚችል አወቀ። ለብዙዎች መድረስ የሚችል የእርዳታ ድርጅት መክፈትን አለመ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ ትምህርት ቤት ሲጀምር ከትምህርቱ ይልቅ ጨዋታውና ጓደኝነቱ ይበልጥ ይስበው ነበር። በዚህም በትምህርቱ ጎበዝ ቢሆንም የነበረው ትኩረት ቀንሶ እንደነበር የአፍላነት እድሜውን ያስታውሳል።
የመሰናዶ ትምህርቱን ጨርሶ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ትምህርት ክፍልን ተቀላቀለ። ይህ የትምህርት ክፍል ሰፊ ጊዜን በይበልጥ ወደ ትምህርቱ ትኩረት ማድረግን የሚጠይቅ ነው። ታዲያ በመጀመሪያው የትምህርት ዓመት ሻሎም ትክክለኛ አቅሙን ለማሳየት ጊዜ ወስዶበት ነበር። ‹‹ አንድ የማልረሳው መምህር ውጤትህ ጥሩ አይደለም ቤተሰቦችን ነጋዴ ከሆኑ እነሱን አግዛቸው። ትምህርት ይቅርብህ ብሎኝ ነበር። ›› በማለት ልቡን የሰበረውን ጊዜ ያስታውሳል።
ሻሎም ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲገባ 17 ዓመቱ ነበር። በዩኒቨርሲቲው ወደሶስተኛ ዓመት ሲሸጋገር 20ኛ ዓመት ልደቱ ላይ ደረሰ። ከዚህ በኋላ የሚያባክነው እድሜ እና ጊዜ መኖር እንደሌለበት ወሰነ። የምንግዜም ሕልሙ ‹‹አይዞን የእርዳታ ድርጅትን›› እውን አድርጎ ብዙዎችን ማገዝ ነው። ታዲያ አንድን ለትርፍ ያልተቋቋመ የእርዳታ ድርጅት ለማስተዳደር የሚያስችለውን ተጨማሪ ትምህርት ለመማር ወሰነ ።
በትምህርቱ ጥሩ ውጤት የለውምና ወላጆቹ ይህንን ሀሳብ ለመደገፍ ጊዜ ወስዶባቸዋል። የማኔጅመንት ትምህርትን በሌላ መርሀግብር፣ በቀን ደግሞ መደበኛ ትምህርቱን መማር ቀጠለ። ከማለፊያ ውጤት ማምጣት ባለፈ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት አብረውት የነበሩትን ተማሪዎችንና መምህራኖቹንም አጀብ አሰኘ። ሻሎም ሀሳብን በደንብ የማስረዳት ክህሎት ያለው በመሆኑ በጊቢው ውስጥ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎችን በሚያስረዳበት ጊዜ መምህርነት ሌላኛው ተሰጥኦው መሆኑን ተረዳ።
የዩኒቨርሲቲ ቆይታውን ሲጨርስ በነበረው ከፍተኛ ውጤት መምህር የመሆን እድልን አግኝቶ በተማረበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር ለመሆን ቻለ። ባገኘው የውጭ የትምህርት እድል መሰረት በውጭ ሀገር ሁለተኛ ዲግሪውን መማር ቻለ። ታዲያ ሻሎም ለ10 ዓመት ያክል ለማስተማር ለራሱ ቃል ገብቶ ነበር። በውጭ ሀገር ቆይታው የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ ወደ 17 የሚጠጉ ዓለምአቀፍ ሰርተፍኬቶች፣ ሁለት ዓለምአቀፍ ዲፕሎማዎች አግኝቷል። በሚማርበት ሀገር ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በመሄድ ግዜውን በአግባቡ ተጠቅሟል። ሲመለስም ቃሉን ባለመርሳት በተለያዩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ኮሌጆች በመዟዟር ለ10 ዓመት በማስተማር ቃሉን አክብሯል።
‹‹ደካማ የትምህርት ስርዓት ኖሯት ያደገች ሀገር፤ ጠንካራ የትምህርት ስርዓት ገንብታ ደግሞ ያላደገች ሀገር በፍጹም የለችም።›› የሚለው ሻሎም ትምህርት መቼም ችላ ሊባል የማይገባ ጉዳይ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻል። እውቀት፣ ክህሎት እና ስብዕና አንድ መምህር ለተማሪዎቹ መስጠት የሚገባው ነው የሚል እምነት አለው። ትምህርትን አብዝቶ በመውደዱም በአሁን ሰዓት ሶስተኛ ዲግሪውን በመማር ላይ ይገኛል።
ሻሎም አስተማሪ በነበረበት ወቅትም ሕልሙ የሆነውን አይዞን ፋውንዴሽን አልረሳውም። የተባበሩት መንግሥታት የልማት እቅዶች የሚያተኩርባቸው የትምህርት ፣ ጤና፤ ንጹህ የውሀ መጠጥ እና የወጣቶችን ማብቃት ፋውንዴሽኑ ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ነጥቦች በማጥናት የአይዞን ፋውንዴሽን የረጅም ዓመት እቅድ አብሮ አዘጋጀ።
‹‹ከማስተማሩ ጎን ለጎን የአይዞን ፋውንዴሽንን ለመመስረት ሀሳብ ነበረኝ፤ ነገር ግን ሕጋዊ ለማድረግ ያለው ሒደት ረጅም በመሆኑ ቀስ በቀስ ሂደቱን ማከናወን ቀጠልኩ።›› የሚለው ሻሎም በዚህ ሒደት ውስጥም እንደ ልጆቹ ለሚያያቸው ተማሪዎቹ ሕልሙን በማጋራት የመጀመሪያ አባላቱን አገኘ። ‹‹አይዞን›› የሚለው ቃል የተመረጠበት ምክንያትም ተስፋን የሚሰጥ ነው ሲል ይገልጸዋል። አይዞን በሲቪል ማኅበረሰብ እውቅናና ሕጋዊነትን አግኝቶ በመመዝገብ ሥራ ከጀመረ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ያህል ጊዜ ሆኖታል።
በአሁን ሰዓትም ከ500 በላይ የሚሆኑ በተለያየ የሙያ ዘርፍ ላይ የሚገኙ በጎፍቃደኛ ባለሙያዎች ይገኙበታል። የበጎ ፍቃደኛ ክፍሉ የጥናትና ምርምር ቡድን፣ የኢንጅነሪንግ ቡድን፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የፈጠራና ኪነጥበብ፣ የስልጠናና ጥናት ቡድን፣ የቴክኖሎጂ ቡድን እንዲሁም የሕግ ጉዳይ ቡድን በውስጡ ይገኛሉ።
ፋውንዴሽኑ ከተመሰረተ በኋላ ከሚያተኩርባቸው ማኅበራዊ ዘርፎች የመጀመሪያው ትምህርት ነው። የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚገኙ ትምህርትቤቶች ያለባቸውን ችግር በማጥናት የትምህርትቤት ቁሳቁሶችን በማሟላት በጥሩ ሁኔታ ላይ የማይገኙ ትምህርትቤቶችን በተሻለ መልኩ ገንብቶ ለሕጻናት ተማሪዎች ምቹ አድርጎ ያስረክባል።
ሌላኛው በአይዞን ፋውንዴሽን ትኩረት የተሰጠው ፕሮጀክት ንጹህ የውሀ መጠጥ አቅርቦትና ንጽህና ነው። ይህም ትምህርትቤቶችን መገንባት ብቻ ሳይሆን ምቹ የመማሪያ ሥፍራዎችን ለሴት ተማሪዎች መፍጠር ላይ ያለመ ነው። በዚህም በእያንዳንዱ ሥራዎች ላይ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በሚያደርገው እንቅስቃሴ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያን አብሮ ያቀርባል። ሌላኛው ፕሮጀክት ወጣቶችን እና ሴቶችን ማብቃት ነው። ትምህርት ቤቶችን በመስራት ሒደት የመጀመሪያው ስፍራ ጉራጌ ዞን ነበር። ትምህርት ቤቱ ሰፊ የመማሪያ ስፍራ ይኑረው እንጂ ተማሪዎች የሚማሩበት ክፍል ግን ለመማር በፍጹም ያልተመቸ ነበር ።
ታዲያ የአይዞን የኢንጂነሪንግ ክፍል ቦታውን በመጠቀም የትምህርት ቤቱ ዲዛይን ምን ሊመስል ይገባል የሚለውን በንድፈ ሀሳብ ካስቀመጠ በኋላ ከመማሪያ ባለፈ የተማሪዎች ቤተ- መጻህፍት ፣ ቤተ-ሙከራ፣ ማረፊያ፣ መጫወቻ የያዘ እንዲሆን በእቅዱ ውስጥ አስቀምጦታል ። ቀጣዩ ትምህርቤቶችን አቅም በፈቀደ መልኩ ለመስራት ወደ አፋር አሉልአባድ የሚባል ቦታ ላይ ተማሪዎች በድንኳን ውስጥ ሆነው የሚማሩበትን ቦታ አገኘ። ‹‹ተማሪዎች ወደ ትምህርትቤቱ ለመምጣት በረሀ አቋርጠው ነው የሚመጡት፤ ከመጡ በኋላ ደግሞ አንደኛ እና ሁለተኛ ክፍል በአንድ ላይ በድንኳኑ ውስጥ ተማሪዎች ጀርባ ተሰጣጥተው ነበር የሚማሩት። ይሄ በጣም አሳዛኝ ነበር ። ›› ይላል፡፡
ይህንን ችግር ከተመለከተ በኋላ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሰባሰብ ትምህርትቤቱን መስራት ላይ ሻሎም አብሮ እንደ ግንበኛ ተሳትፎበታል። ‹‹ ትምህርትቤቱን ስንሰራ ጭቃ ውስጥ ያለች ጊንጥ ነድፋኝ ቦታው በረሀ በመሆኑ የሚደርስልኝ ሰው አጥቼ ነበር። ›› በማለት ያስታውሳል። አይዞን ፋውንዴሽን ትምህርትቤቱን በሚሰራበት ወቅት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እና ባለሙያዎችን ከራሱ አሟልቶ የሚወስድ በመሆኑ በአንድ ክልል ከአንድ በላይ ትምህርትቤት የመስራት እቅድ አለው። ይህም በብዙ ማጓጓዝ ይዘው የሚሄዱትን ግብዓቶች ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ያስችላቸዋል። ቀጣዩ ፕሮጀክት በጦርነት የተጎዱ ሦስት ክልሎች ላይ ማለትም ትግራይ ፣ አማራ እና አፋር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ‹‹ ከጦርነት ወደ ትምህርት ቤት ›› ኢኒሼቲቭ ነው ።
በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርትቤቶች መጠገን እና መልሶ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የሚያስችል ነው። ‹‹ የሰው ልጅ የሚያደርገው ጥናትና ምርምር ከምድር አልፎ ጠፈር ላይ ደርሷል። ነገር ግን ጦርነትን ማስቆም የሚችል የእውቀት ልክ ላይ አልደረሰም ። ›› ሲል የጦርነትን አስከፊነት ይገልጻል ።
በመሆኑም ኢኒሼቲቩ በደቡብ ትግራይ መኾኒ ከተማ የጦር መሳሪያ ያፈራረሳቸውን ትምህርትቤቶች መልሶ በመገንባት ለሕጻናት ሳቢ እንዲሆን አድርጓል። የመማሪያ ደብተሮችን፣ የደንብ ልብስ፣ የመምህራን ጋወን ከማሟላት ባሻገር በጦርlት የተፈጠረውን መጥፎ ጠባሳ ለመመለስ የሚያስችል ስልጠና አብሮ እንዲሰጥ አድርጓል። ሌላኛው ጉዳት የደረሰበት በአፋር ክልል ዳርሳጊታ ትምህርት ቤት በድጋሚ መልሶ በማደስ ለሕጻናት በድጋሚ ምቹ እንዲሆን አድርጓል። ‹‹ በከባድ መሳሪያ የተመቱ ትምህርትቤቶች ውስጥ ሕጻናቱ ያዩትን መድፍ በግድግዳ ላይ ስለው ተመልክተናል። ጦርነቱ በፈጠረው ጠባሳ ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ ነበር። ›› ሻሎም በተጓዘባቸው ቦታዎች የተመለከተው ጉዳይ ነው።
ወጣቶችን እና ሴቶችን ማበረታታት ላይ የሚያተኩረው ዘርፍ (እሷ ትችላለች) ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመርቀው የወጡ ተማሪዎችን የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት በሥራ ዘርፍ ላይ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉበትን እንዲሁም የራሳቸውን ቢዝነስ መጀመር እንዲችሉ የሚያደርግ ስልጠና ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመሆን ይሰጣል ።
ሌላኛው የንጹህ ውሀ መጠጥ ፕሮጀክት ከመሬት ወደ ቤት የሚሰኝ ነው። ይህም በተለያዩ ቦታዎች ላይ የውሀ ጉድጓዶችን በመቆፈር ንጹህ የውሀ መጠጥን ለማድረስ ያለመ ነው። ከተቋቋመ ጥቂት ጊዜ የሆነው አይዞን ፋውንዴሽን ከሻሎም ሀሳብ ወደብዙዎች ደርሶ ራሱን የቻለ የሚመራበት ቦርድ የተቋቋመለት ነው። ተቋሙ ራሱን ከሚያገኛቸው የበጎ ፍቃደኞች የአባላት መዋጮ ባለፈ በኢንጂነሪንግ ቡድኑ ለተለያዩ ተቋማት ፕሮጀክቶችን በመስራት፤ የቴክኖሎጂ ቡድን እንዲሁ ለተቋማት የድህረገጽ ማጎልበት ሥራዎችን በመስራት በእርዳታ መልክ የራሱን ገቢ ለማግኘት ይሰራል ።
ሻሎም በአይዞን ፋውንዴሽን ውስጥ እንደ አንድ ባለሙያ የሚሰራ ነው። በስሩ ተቀጥረው ከሚሰሩ ሰራተኞች ባለፈ ምንም አይነት ገቢን ወይም ክፍያን አይቀበልም። ከፋውንዴሽኑ ውጪ ያለውን ጊዜ ገቢ የሚያገኝበት የራሱ ቢዝነስ፣ እና የሚመራው ተቋም እንዳለ ይገልጻል።
ኢትዮጵያ የምትሰጥ እንጂ እርዳታን የምትቀበል ሀገር ብቻ መሆን የለባትም የሚለው ሻሎም የአይዞን ፋውንዴሽን የወደፊት እቅድ ከኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ጥቁር ዜጎችን ማገዝ የሚችል እንደሆነ ገልጿል። ‹‹ዓለም ላይ ችግር የፈጠሩ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ መፍትሄን ያመጡ ሰዎችም አሉ። እኔ ኖሬ እስካልፍ ድረስ ብቻ የሚቆይ ሕልም እንዲኖረኝ አልፈልግም። እኔ ካለፍኩ በኋላም ብዙዎችን የሚያገለግል መሆን አለበት። ትልቅ ሕልም አልሙ፤ ለማሳካት ደግሞ በትንሹ ጀምሩ ሕልማችሁን የሚመጥን ጥረት ይኑራችሁ። ›› የሚል ምክር በማካፈል ሃሳቡን ቋጭቷል።
ሰሚራ በርሀ