ኢትዮጵያ በቱሪዝም (ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ) ሀብቷ ብቻ ከራሷም አልፋ አፍሪካን መትረፍ የሚያስችል አቅም እንዳላት በጥናትና ምርምር ሥራዎች ማቅረቢያ መድረኮችና በመገናኛ ብዙኃን ያልተነገረበት ወቅት ባይኖርም ውጤታማነቱ ግን በተግባር አልታየም።
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የቱሪዝሙ ኢንዱስትሪ ውጤታማ ያለመሆን ምክንያቶች የቴክኖሎጂእውቀትማነስ፣ የሰውኃይል አጠቃቀም፣ የቅንጅታዊ አሰራርና አመራር አለመኖር፣ መሰረተ ልማት አለመሟላት ወዘተ . . . መሆናቸው ይጠቀሳል።
የኢትዮጵያ የሆቴል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ባለፈው ሳምንት 50ኛ ዓመቱን በተለያዩ ፕሮግራሞች ሲያከብር ትኩረት ከሰጣቸው ርእሰ ጉዳዮች አንዱ ይኸው በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው የደነደነ ተግዳሮት ነው።
ከተለያዩ ምንጮች መገንዘብ እንደተቻለው ዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማጣት፣ ለቴክኖሎጂ እንግዳ በመሆን የተገልጋዮችን ጊዜና ጉልበት የሚያባክን፣ላልተፈለገ ወጪና እንግልት የሚዳርግ፣ የሚጠበቅበትን ያገር ኢኮኖሚ የመደገፍ ሚናውን መወጣት ያልቻለ፣ቀልጣፋ አገልግሎትን በመስጠት የደንበኞችን እርካታ ከፍ ማድረግ፣ የቆይታ ጊዜያቸውንና ቁጥራቸውን መጨመር የተሳነው፣ እይታው በራስ ጥቅም ዙሪያ የታጠረ፣ ካረጀና ካፈጀ የዘመድ አዝማድ አሰራር ያልወጣ መሆኑ ነው። ከዚሁ ዘርፍ ጋር በተያያዘ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የሥራ ኃላፊዎችም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያረጋግጡልን ይህንኑ ነው።
የኢትዮጵያ የሆቴል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት እንደገለፁት፣ በአገራችን ያሉትና በኮከብ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች በዘርፉ የሰለጠኑ የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎችን የመቅጠርና የማሰራት ፍላጎት አይታይባቸውም።
ኢንስቲትዩቱ ከአራት ወር እስከ አራት አመት በዲግሪ ደረጃ በሚወሰዱ ፕሮግራሞችና በ15 የትምህርት መስኮች በበቂ መምህራን የሰለጠኑ ወጣቶችን አስመርቆ ለሥራ ዝግጁ ቢያደርግም በዘርፉ የተሰማሩ ባለ ሀብቶች እነዚህን በሙያው በቂ እውቀት ያላቸውን ወጣቶች በመቅጠር በሰለጠነ ባለሙያ የታገዘ አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ የቅርብ ዘመድን እየቀጠሩ የማሰራት ፍላጎት በማሳየታቸው ዘርፉን የሚጎዳ ተግባር እየተፈፀመ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ በአገሪቱ ከሚገኙ ባለኮከብ ደረጃ ካላቸው ሆቴሎች ውስጥ በሥራ ላይ ከተሰማሩት ሰራተኞች መካከል በዘርፉ የሰለጠኑት 23 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።
አንዳንዶችእንደሚናገሩት ይህንን መሰሉ ከዝምድና ጋር የተያያዘ አሰራር ለኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ብዙም የሚያሳስብ ባለመሆኑ ዲግሪ ባይኖርም “ልምድ” በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ነው።
ዳይሬክተሯ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። እንደ እርሳቸው አገላለፅ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ በሙያው ለሰለጠኑ ባለሙያዎች የሥራ እድልን ባለመፍጠር፣ የተገልጋይ እርካታን ባለማስገኘትና ቱሪስቶችንባለመሳብ ያገር ኢኮኖሚን በማቀጨጭ፤ እንዲሁም በዘርፉ ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎትቀልጣፋካለማድረግምባለፈ ባለሆቴሎቹንና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን በመጉዳት ከተወዳዳሪነት ውጪ ያደርጋቸዋል። በተለይ በቁጥጥርና ክትትል ጊዜ አንዱ መለኪያ በሰለጠነ የሰው ኃይል መመራትና ማሰራትን፤ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ወዘተ…የሚመለከት በመሆኑ በባለሙያ ያልታገዘው አሰራራቸው ከደረ ጃቸው ያወርዳቸዋል።
የኢትዮጵያ ሆቴል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በራሱ ምሁራን ባስጠናው ጥናት እንደተመለከተውና ዳይሬክተሯ እንደገለፁልን በሆቴልና ቱሪዝሙ ዘርፍ ባለሙያዎችን ማሰራት ለምሩቅ ባለሙያዎቹ የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ቱሪስቶችን በአገልግሎት ለማርካት፣ የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም፣ ቁጥራቸውን ለማሳደግ፣ ያገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍና ለአገሪቱ ዓመታዊ ገቢ ዕድገት አስተዋፅኦ ከማድረግ ባሻገር ለአገር ገፅታ ግንባታ የሚኖረው ጠቀሜታ ጉልህ ነው። ከእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች አኳያ ሙሉ ለሙሉ በዘርፉ የሰለጠኑና በቂ እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎችን መጠቀሙ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ሙያዊ ግዴታና የአሰሪዎች ኃላፊነት ነው።
በአገሪቱ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ተማሪዎችን ያስመርቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሠለጠኑ የመስኩ ባለሙያዎች በሚፈለገው መጠን በቂ ነው ባይባልም የኢትዮጵያ የሆቴል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከአራት ወር እስከ አራት ዓመት በሚደርሱ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞች በብቁ መምህራን አሰልጥኖና አስመርቆ ለሥራ ዝግጁ እንደሚያደርግ፤ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች እነዚህን እውቀት ያላቸውን ወጣቶች በመቅጠር ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሯ አሳስበዋል።
በፈረንሳይኛ፣በእንግሊዝኛናቻይንኛን በመሳሰሉ ቋንቋዎች በቂ እውቀት ያላቸውን እነዚህን ወጣት ባለሙያዎች ከማፍራታችን አኳያ በሆቴልና ቱሪዝሙ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወጣቶቹን ሊቀጥሩና ሊያሰሯቸው እንደሚገባ፤ በተለይ ከአገር ገፅታ ግንባታ አኳያ ይህ በቀላሉ ሊታለፍ የማይገባው ጉዳይ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ይጠቁማሉ።
ዋና ዳይሬክተሯ እንደሚሉት በተደረጉ ሰፊ ጥረቶች በዘርፉ በተሰማሩ አንዳንድ ባለሀብቶች ዘንድ በባለሙያዎች የመጠቀሙ ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል።በተለይም የተቋማቱ ባለቤቶች የውጪ ዜጎች የሆኑ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ከውጪ አገራት አምጥተው የሚያሰሩና ተቋሙንም ለተማሪዎች ተግባራዊ ስልጠና እንዲሰጥበት በማድረግ በኩል እያገዙት ይገኛሉ።
ከሆቴል ልማቱ ዘርፍ ወጥተን ተያያዥ ወደ ሆነው አስጎብኚ ድርጅቶችም ስንመጣ የምናገኘው ተመሳሳይ ሁኔታና ሂደትን ነው።በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ዋና ዳይሬክተሯ ተቋማቸው የመስክ አስጎኚዎችን “ቱር ጋይድ” ባለሙያዎችን በበቂ ደረጃ አሰልጥኖ ያስመርቃል። በተመሰከረላቸው መምህራን አማካኝነትም ሰልጣኝ ተማሪዎች በአራቱም አቅጣጫ የማስጎብኘት ሥራ “ቱር ጋይድ” እንዴት እንደሚሰራ ተዘዋውረው ተግባራዊ ልምምድ ያደርጋሉ። ለሾፌሮችም የቋንቋ ትምህርት ይሰጣል።
እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ አስጎብኚዎቹ በቂ የቋንቋ ክህሎትና እውቀትን ይዘው ይመረቃሉ። ይሁን እንጂ የሚመለከታቸው የቱር ጋይድ ተቋማት እነዚህን ባለሙያዎች ቀጥረው ሲጠቀሙባቸውና ዘርፉን ሲያዘምኑ፣ ኢንዱስትሪውን ሲያስፋፉ፣ ቀልጣፋ አገልግሎት ሲሰጡ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የቱሪስቶች (ጎብኚዎች)ን ቁጥር ሲጨምሩ አይታዩም። አሰራራቸው ዘመድን ማእከል ያደረገ ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ያዕቆብ መላኩ ያላቸው አስተያየት የተለየ ነው። “አንድ ሰው ሥራውን እስከሰራና አሟልቶ እስከተገኘ ድረስ ዜጋ ነውና ዘመድን እዛ ቦታ ላይ ማስቀመጥ ምን ችግር አለው?” ይላሉ። እንደ ማህበሩ ፕሬዚዳንት ገለፃ አገሪቷ ምንም አይነት ዩኒቨርሲቲና ባለሙያዎች ሳይኖሯት ሥራውን እዚህ ያደረሱት በልምድ ብቻ ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው።
አቶ ያዕቆብ መላኩ ከዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር የሚለዩበት እንዳለ ሁሉ የሚስማሙበት ሀሳብም አለ። እርሳቸው የተማረ የሰው ኃይል መጠቀም የሚለውን በመርህ ደረጃ ያምናሉ። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ከተለያዩ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ምሩቃን አቅም ላይ ጥያቄ አላቸው። ከካሪኩለሙ ይዘት ጀምሮ ችግር አለበት ይላሉ።
ባለፈው ዓመት በዚሁ ወር በጌትፋም ሆቴል ተዘጋጅቶ በነበረውና “የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሆስፒታሊቲ ዳሰሳ ተግዳሮቶችና ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች” በሚል ርእስ በቀረበው ጥናት ላይ እንደተብራራው የአገሪቱ የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ዘርፍ ነው። በተለይም “በሙያው በቂ ዕውቀት ሳይኖራቸው ዘርፉን የሚቀላቀሉ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ቅርሶችና ታሪካቸው በቂ ዕውቀት ሳይኖራቸው በድፍረት እናስጎበኛለን የሚሉ ጥቂት አይደሉም፡፡ እንዲህ ያሉ አስጎብኚዎች ታሪክን ሲያዛቡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሙያዊ ሥነ ምግባርን በመተላለፍ አገርን ትዝብት ላይ ይጥላሉ፡፡” የሚለው በከፍተኛ ደረጃ ሲያወያይ የነበረ መሆኑ አይዘነጋም።
በአጠቃላይ በዘርፉ የስነ-ምግባር ችግርና የእውቀት ክፍተት መኖር፤ ሆን ብሎ የማጥፋት ሁኔታዎች፣ የባለ ድርሻ አካላት ግንዛቤ አነስተኛ መሆን፣ በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢ ያለው ህብረተሰብ ግንዛቤ ማነስ፣ ከባንክ ጀምሮ የመሰረተ ልማት አለመሟላትና የመሳሰሉት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው መስፋፋትም ሆነ ለቱሪስቱ ቁጥር ማነስና የቆይታ ጊዜ ማጠር ምክንያቶች ናቸው በሚለው አቶ ያቆብና ሚኒስትሯ ይስማማሉ። እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ ዘርፉን ማሳደግ እንደሚቻልም እንደዛው። በተለይ የባለድርሻ አካላት መቀናጀት ለችግሮቹ ሁሉ መፍትሄ ነው ባይ ናቸው። (ከዚህ ጋር በተያያዘ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ዳይሬክቶሬት ሥራ ኃላፊዎችን ለማግኘትና በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን በስልክም በአካልም ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
ፕሬዚዳንት አቶ ያቆብ መላኩ እንደሚሉት ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ ሊንቀሳቀሱ የሚገባቸው አካላት አሉ። ከባለሱቅ ጀምሮ መንግሥታዊ የሆኑና ያልሆኑ የግል የድርጅት፤ ባጠቃላይ 15 ያህል አካላት ያሉ ሲሆን፤ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው የዘርፉን ስኬታማነት የሚወስነው።
ሚኒስትሯ እንደሚሉት የሆቴል ባለሙያዎች ማህበር፣ የሆቴል ሥራ አስኪያጆች ማህበር፣ ማሰልጠኛ ማእከላት፣ የአስጎብኚዎች ማህበራት፣ የቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበራትና ሌሎችም እንደ ሀገር አስበው ለአንድ ግብና ለአንድ አላማ ሲባል ተቀናጅተው መስራት ቢችሉ ዘርፉን በሚገባ ማልማት ይቻላል።
የአክሱምዩኒቨርሲቲሰሞኑንባካሄደው ውይይትናበደረሰበት ውሳኔያስተላለፈው መልእክት ይህንኑ ነው። «አክሱምና አካባቢው ከ60 በላይ የቱሪስት መስህቦች እያሉ በሚገባ ባለመሰራቱ ምክንያት ጎብኚዎች አክሱም ደርሰው ከሁለት ቀን ቆይታ በኋላ ይመለሳሉ። በመሆኑም ተቀናጅቶ በመስራት የቆይታ ጊዜያቸውን ወደ አምስት ቀን ለማሳደግና ቁጥራቸውን ለመጨመር ሁሉም ባለድርሻ አካላት መስራት አለባቸው» ሲልም አቋም ላይ ደርሷል።
50ኛ የምስረታ ኢዩቤልዩ በዓሉን ከሰኔ 1 እስከ 3 / 2011 ዓ..ም ድረስ በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ያከበረው የኢትዮጵያ የሆቴል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከፕሮግራሞቹ አንዱ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚለማበትና የሚያድግበት ሁኔታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መምከር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011
ግርማ መንግሥቴ