አዲስ ዘመን ድሮ

አስታዋሹን ሲያስታውሱት…የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሠራተኞች ምን ሆኑ…ይህን በተመለከተ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያወጣው መረጃ ያስታውሰናል:: ሀገራችን ኢትዮጵያ በተሳተፈችበት በኮንጎው የጦርነት ዘመቻ ላይ ስለወታደሩና የገጠማቸው ጉዳይ፤ በጊዜው በአዲስ ዘመን ከሰፈሩ ወቅታዊ ዘገባዎችም ሁለቱን እናስታውሳለን:: ከዚህ ወጣ ስንል ደግሞ “የዝንጀሮ ሥጋ ውዝግብ ፈጠረ “ ነገሩ እንዴትስ ይሆን…ማሞ ውድነህም “አበበን አይቼ” ይለናል::

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሠራተኞች በተገኘ የተሻወርቅ ላይ ክስ አቀረቡ

አዲስ አበባ(ኢ.ዜ.አ) የኢትዮጵያ ፕሬስ፤ የጋዜጠኞች ማከፋፈያና ማስታወቂያ ድርጅት አባሎች፤ ክቡር አቶ ተገኘ የተሻወርቅ፤ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ጊዜ በሥራውና በሠራተኞቹ ላይ በደል አድርሰዋል በማለት ለክቡር አቶ አሐዱ ሳቡሬ የማስታወቂያ ሚኒስትር ትናንት አቤቱታ አቀረቡ::

ሠራተኞቹ ትናንት ለማስታወቂያ ሚኒስትሩ ባቀረቡት 29 አንቀጾች በያዘ አቤቱታ ላይ ክቡር አቶ ተገኘ፤ የፕሬስ፤ የጋዜጠኞች ማከፋፈያና ማስታወቂያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ጊዜ አቋማቸው የማይታወቅ ኤዳና ኢትዮ ማርኬቲንግ የሚባሉ የማስታወቂያ መሰብሰቢያ ድርጅቶች አቋቁመው ለመንግሥቱ ሊገባ የሚገባውን ገንዘብ አላግባብ እንዲባክን አስደርገዋል:: እንዲሁም ከድርጅቱ አባሎች መካከል አንዳንድ ዕድገት የማይገባቸውን ሰዎች ያለደረጃቸው ዕድገት ሲሰጡ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ ያላግባብ ከደረጃቸው ዝቅ በማድረግ የሞራል ውድቀት አድርሰውባቸዋል በማለት በዝርዝር አመልክተዋል::

አቶ አሐዱ ሳቡሬ የሠራተኞቹን አቤቱታ ከተቀበሉ በኋላ ጉዳዩን በዝርዝር የሚያጠኑ መሆናቸውን ገልጠውላቸዋል::

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 7 ቀን 1966ዓ.ም)

የኢትዮጵያ ወታደሮች በኦሬይንቲል ፀጥታን አስከበሩ

በኦሬይንቲል ጠቅላይ ግዛት ፓንሰር ቪል ከሚባለው ቀበሌ ውስጥ ሁከት ተነሥቶ 3 የሲቪል ሠራተኞች መሞታቸው ተነገረ:: በዚህ ቀበሌ የሚገኙ ፖሊሶች በሥፍራው ከመድረሳቸው አስቀድሞ የሀገሬው ሰዎች ሆስፒታልንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ለመውረርና ለመዝረፍ አቆብቁበው ይታዩ ነበር::

ነገር ግን በተባበሩት መንግሥታት ስር የሚታዘዙት የኢትዮጵያ ወታደሮች ደርሰው ፀጥታውን ያስከበሩ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ አስታውቋል::

የኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስተር ሉዊስና የኦሬይንቲል መንግሥት ጠቅላይ ገዥ እስታንቪል በሚገኘው ማረፊያ ቦታ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጓል:: ይህም የሆነበት ምክንያት በኮሎኔል ሞቡቱ ላይ ሴራ ሲያደርጉ በመገኘታቸው መሆኑን እራሳቸው ኮሎኔል ሞቡቱ ለጋዜጠኞች ባደርጉት ንግግር ገልጸዋል::

“ካውሪር ደ አፍሪክ” የተባለው የሚስተር ሉሙምባ ተቃዋሚ ጋዜጣ፤ ሚስተር ሉሙምባን ይደግፉት ከነበሩት 30 የኮንጎ ምክር ቤት አባሎች ውስጥ ሃያ ዘጠኙ የሉሙምባን መሪነት አናውቀውም በማለት ፈጽመዋል ሲል አትቷል::( ሬውተር)

(አዲስ ዘመን መስከረም 20 ቀን 1953ዓ.ም)

የዝና ስም

በተቀዳሚ ወደ ኮንጎ የተላከው የጠቅል ሻለቃ ወደዚያ ክፍለ ሀገር ከሔደ ጀምሮ በፈጸመው ሥራ ከፍ ያለ የአድናቆትና እንደገና የዝና ስም በየጊዜው ከልዩ ወኪላችን በደረሰን ዕለታዊ ወሬ ተረጋግጧል::

ጸጥታን በማረጋጋትና ሁከት በተነሣበት አገር እየተዘዋወሩ ከተማዎችንና ሰፈሮችን ለመረከብ ተጠንቅቆ በመሥራት ተግቶ በመጠበቅ ለሀገሪቱ ታላቅ ውለታ ውለውለታል::

የኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚስተር ሉሙምባ የኢትዮጵያን የጦር መኮንኖችና ወታደሮች ታማኝነት በመገንዘብ፤ ወዲያና ወዲህ የሚዘዋወሩት በኢትዮጵያ ኤሮፕላን እንደሆነ የደረሰው ወሬ ጨምሮ አመልክቷል::

ይልቁንም አሁን የሔዱት መኮንኖችና ወታደሮች በዚያ አገር ሲደርሱና አገልግሎታቸውን ሲጀምሩ፤ ኮንጎ በፍጹም ጸጥታ ላይ መገኘቷ አያጠራጥርም::

ይህም ወሬ አይደለም በኢትዮጵያ ጀግኖች የሆነና ተደርጎ የታየ ስለሆነ ነጋሪ አያሻም::

በመጨረሻ እንደተገኘው ወሬ በኮንጎ ውስጥ የነበረው ሁኔታ እንደቀድሞው ፀጥታው ስለተመለሰ፤ የኮንጎ ሕዝብ የተባበሩትን መንግሥታት ድርጅት ወታደሮች በአክብሮት የተቀበላቸውና በደስታ የተመለከታቸው መሆኑን፤ ከሊኦፖል ድ ቪል የወጣው መግለጫ ያመላክታል::

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 10 ቀን 1953ዓ.ም)

የዝንጀሮ ሥጋ ውዝግብ ፈጠረ

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ በዛየር ተጫዋቾችና በግብፅ ወጥ ቤቶች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር:: አለመግባባቱ የተፈጠረው የዛየር ቡድን ለምግብ ከአገሩ ይዞት የመጣውን የዝንጀሮ ሥጋ እንዲዘጋጅለት ጠይቆ ወጥ ቤቶቹ አናበስልም ብለው በመቃወማቸው ነው::

በመጨረሻ የዝንጀሮው ሥጋ በተለየ ክፍል እንዲበስልላቸውና ያመጋገባቸው ቦታ ግን በሆቴል ቤቱ ሳይሆን በመኝታ ክፍላቸው እንዲሆን የቀረበውን ሃሳብ የተስማሙበት በመሆናቸው ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት ሊበርድ የቻለ መሆኑን በሬውተር በኩል ከካይሮ የተላለፈው ዜና አስረድቷል::

ከአዘጋጁ

በሀገራችን በዱር በገደሉ፤ ቀጭን ከወፍራም፤ ነጭ ከጥቁር፤ ቀይ ከቡላ ቀለም መልክ ያላቸው እጅግ ብዙ ጦጣና ዝንጀሮዎች ይገኛሉ:: እነዚህ የዱር እንስሳት በማሳ ውስጥ የተዘራውን ለቅመው፤ ከጓሮ የተተከለውን ነቅለው፤ ያሸተውንም ሸምጠው የሚበሉ በመሆናቸው ድንጋይ በወንጭፍ ወርውሮ ከማባረርና ቆመጥ ይዞ ከመግደል በቀር በመያዝ ለጥቅም ያዋላቸው የለም::

የዝንጀሮ ሥጋ ለስንቅ እስከመዘጋጀት የደረሰ መሆኑን ለማያውቁት የሚያስገርም ዜና ይሆን ይሆናል:: በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የዝንጀሮ ሥጋ ተወዳጅነቱና ተፈላጊነቱ ከወጥ ቤቶች ጋር እስከማጣላት የደረሰ(እጅ የሚያስቆረጥም) ከሆነ አዲስ የሥራ ዓይነት ለመጀመር ዕቅድ ላላቸው፤ ያፋላጊ የማይከፍሉበት የሥራ መስክ ዕድል የሚያገኙበት ሊሆን የሚችል ይመስላል::

( አዲስ ዘመን መጋቢት 4 ቀን 1966ዓ.ም)

አበበን አይቼ

ጎረቤቴ የሆነ ሰው ድሮ የሚመላለሰው በልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎች ነበር:: ከጥቂት ቀናቶች ወዲህ ግን ከቤት ወደ መሥሪያ ቤት ከዚያም ወደፈለገው ቦታ የሚሔደው በሩጫ ሆነ:: ነገሩ ተደናገረኝና አንድ ቀን፤ ምን መጣብኝ ብለህ ትሮጣለህ? አልኩት፤ እርሱም ምንም አልሆንኩም ግን አበበን ካየሁ ወዲህ እኔም እሮጣለሁ ብሎኝ ሸመጠጠ:: (ተፈተለከ)

ማሞ ውድነህ

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You