‹‹በዘመነ ዲጂታል›› በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሉ ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎችን (ስታርትአፖችን) ማበረታታት ተገቢ እንደሆነ ይነገራል:: በኢትዮጵያም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን የማበረታታቱ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል:: ለዚህም ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል::
ከማሳያዎቹ መካከልም ከሰሞኑ በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ያለው ‹‹የጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎችን ስታርትአፖች አውደ ርዕይ›› አንዱ ነው:: አውደ ርዕዩ ከመጋቢት 30 ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 28 ድረስ የሚቆይ ሲሆን በአውደ ርዕዩ በርካታ ጀማሪ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው አካላት የሚሳተፉበትና የፈጠራ አቅማቸውን የሚያሳዩበት እንደሚሆን ይታመናል::
የዝግጅት ክፍላችን በአውደ ርዕዩ ተገኝቶ በጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎቹ የቀረቡ የፈጠራ ሃሳቦችን በመቃኘት ያዘጋጀውን ይዞ ቀርቧል:: በአውደ ርዕዩ ሥራቸውን ካቀረቡ ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎች መካከል ዶክተር ፍቃዱ ድሪባ አንዱ ነው።
ዶክተር ፍቃዱ አውቶማቲክ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ መሳሪያ/አውቶማቲክ ኤሌክትሪክ ፓወር ሬጉሌሽን ዲቫይስ /ፈጠራ ባለቤት ነው። የዚህ ፈጠራ ጠቀሜታ እንደ ሀገር ላለው የመብራት ኃይል መቆራረጥ ችግር መፍትሔ የሚያመጣ ነው::
አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ከመብራት ኃይል እያንዳንዱ ተጠቃሚ ጋር እስኪደርስ 35 በመቶ ያህል የኃይል መቀነስ እየተከሰተ መሆኑን መረጃዎች እንደሚያመላክቱ የሚናገረው ዶክተር ፍቃዱ፤ በኢንዱስትሪዎች እንዲሁ የኤሌክትሪክ ኃይል መቀነስ ሆነ ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሶ፤ ይህ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ለችግሮቹ መፍትሔ በማምጣት የኃይል መቀነስንም ሆነ በየጊዜው የሚያጋጥመውን የመብራት ኃይል መቆራረጥ ለማስቀረት ያስችላል ይላል።
የአውቶማቲክ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ መሳሪያው ሦስት ነገሮችን መሥራት የሚያስችል ሲሆን፤ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠር፣ የቮልቴጅ መጠንን መጨመር እና የኃይል ፍጆታ በመቀነስ የሥርዓት አቅምን እንደሚጨምር ያመላክታል።
ይህን የፈጠራ ሥራ የጀመረው 2009 ዓ.ም አካባቢ እንደነበር የሚያነሳው ዶክተር ፍቃዱ፤ ነገር ግን በመሀል አቋርጦ ወደሌላ ሥራዎች ማዘንበሉን ነው የገለጸው:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለጀማሪ የፈጠራ ሥራዎች የተሰጠው ትኩረት ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክንያት እንደሆነም አልሸሸገም::
የፈጠራ ሥራው በአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ተመዝግቦ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ተሰጥቶታል:: በተጨማሪም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት የሶፍት ዌር ፕሮግራም እና ሰፊ የቴክኖሎጂ ሥራ እንዲኖረው ተደርጓል።
ዶክተር ፍቃዱ፤ አሁን ላይ ጃንግል ፓውር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የተሰኘ ድርጅት በመመሥረት ቴክኖሎጂውን ለማምረት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ይናገራል:: ቴክኖሎጂው በስታርትአፕ በሚያገኘው የፋይናንስ ድጋፍ በቅርቡ ወደ ማምረት ሥራ እንደሚገባ ይገልጻል:: ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች የፋይናንስ ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት ጥናት ተደርጎ ቢዝነስ እቅድ ተነድፎለት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ያመላክታል::
‹‹ቴክኖሎጂው ከ20 ዓመት በላይ ካለ ምንም ጥገና ሊያገለግል ይችላል:: ይህ የፈጠራ ውጤት ተግባር ላይ ሲውል ሁሉንም ሰው የሚጠቅም ነው:: ለምሳሌ ቴክኖሎጂውን የሚጠቀመው አንድ ፋብሪካ ቢሆን ፋብሪካው ይህን ቴክኖሎጂ ሲጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታውን ይቀንስለታል። በመሆኑንም ቴክኖሎጂውን ሲጠቀም የቴክኖሎጂውን የገዛበትን ዋጋ አሁን ላይ በኤሌክትሪክ ኃይል ብክነት የሚከፈለውን ቅጣት ከዓመት ባነሰ ጊዜ ሊመልስ ይችላል›› በማለት አስረድቷል::
‹‹ቴክኖሎጂ በሀገራችን የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራ ነው›› የሚለው ዶክተር ፍቃዱ፤ ኢንዱስትሪዎች በአዲሱ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ሲጠቀሙ ቀደም ሲል እየባከነ ያለውን ኃይል መቆጠብ ስለሚችሉ ይህ የሚቆጥቡትን ኃይል ለሌላ ማሽን ማዋል እንደሚችሉ ያስረዳል::
‹‹ለፈጠራ ሥራ የሚያስፈልገው ኤሌክትሪክ ዲቪይስ ከውጭ ሀገር የሚመጣ ሲሆን፤ ፒሲቪ ቦርዱን እዚሁ ዲዛይን አድርጎ ለመሥራት ማሸኑ በመኖሩ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተፈቅዶልኛል›› የሚለው ዶክተር ፍቃዱ፤ ድርጅቱ ሲቋቋም ‹‹ፒሲቪ ቦርዱን›› እና ‹‹ሰርፌስ ቦርድ›› የሚያመርት ማሽን ከውጭ ማስገባት ከተቻለ ሌላውን ሥራ በሙሉ ሀገር ውስጥ እንደሚሠራ ይናገራል::
ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሲደረግና ሥራ ሲጀምር በመጀመሪያ ዙር 500 ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል:: ወደፊት ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ተርፎ ወደ አፍሪካ ሀገራት ኤክስፖርት ለማድረግ እቅድ እንዳለው ያመላክታል:: ይህን ቴክኖሎጂ ሀገር ውስጥ በማሳደግ ለሀገር ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ትውልድ የሚጠቀምበት እንዲሆን በሀገር አቅም ሠርቶ ማሳደግ ይቻላል የሚል ፅኑ አቋም ይዞ እየሠራ እንደሆነ ገልጿል::
‹‹ይህ ፈጠራ በስታርትአፕ ደረጃ መሥራት ከጀመርኩ ሦስት ዓመታት ያህል ሆኖኛል። ነገር ግን በጊዜው የስታርትአፕ ሃሳብ በደንብ ስላልታወቅ የሚደግፈኝ አካል ባለመኖሩ እስካሁን እንድቆይ አስገድዶኛል›› ያለው ዶክተር፤ አሁን ላይ እስካሁን ማነቆ የሆኑ ችግሮች ተቀርፈው ሕጎች እየጸደቁ ሲሆን ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎች ለሀገር ትልቅ ሥራን የሚሰሩበት ሰፊ ምህዳር እየተፈጠረላቸው ስለሆነ ሊጠቀሙበት ይገባል በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል::
ወጣት ሳሙኤል ጌትነት እና ጓደኞቹ ከተረፈ ምርቶች የሚያመረቷቸውን የተለያዩ ምርቶች ይዘው ቀርበዋል። የሳር፣ የወረቀት፣ የእምቦጭ አረም እና የእንሰት የተረፈ ምርት ተጠቅመው ምርቶችን ያመርታሉ::
እነ ሳሙኤል አላስፈላጊ ከሆኑ እና ተቃጥለው የአካባቢ አየር ንብረት የሚበክሉ ተረፈ ምርቶች ተጠቅመው መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ሁለት ዓይነት ምርቶችን አመርተዋል። አንደኛው የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለመያዝ የሚያገለግለ ዘንቢል /ፓኬጂንግ/ ሲሆን፤ ሁለተኛው የኬክ ፕሌት ነው::
ሳሙኤል እንደሚለው፤ የዘንቢል ምርቶቹ በሀገራችን ለተለያዩ ዓይነት የእቃ መያዣዎች የሚያገለግሉና ፌስታሎችን የሚተኩ ናቸው:: እነዚህ ፓኬጆች ፌስታልን መተካት ብቻ ሳይሆን የአፈርን ለምነት የማይጎዱ ከአካባቢው አየር ንብረት ጋር ተስማሚም ናቸው:: በጣም ጠንካራ እና በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ረጅም ጊዜ የሚቆዩም ናቸው::
አሁን ላይ በሀገራችን ያሉት የፌስታል ምርቶች ከፍተኛ የሆነ የገበያ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ጠቅሶ፤ በወር ከስድስት እስከ ስምንት መቶ ሺ የሚሆን የፌስታል ምርት እንደሚፈለግ ያመላክታል:: በመሆኑም ይህን ፌስታል በዘንቢል ምርት በመተካት ያለውን ሰፊ የሆነ የገበያ ፍላጎት አላማ ያደረገ ሥራ መሥራት እንደቻሉ ነው ወጣት ሳሙኤል የሚናገረው::
ሁለተኛው ምርት የኬክ ፕሌት ሲሆን፤ ይህም ኬክን ለመሥራት አስፈላጊ የሆነ የኬክ ማስቀመጫ ነው:: በኬክ ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ ሰዎች ከሚያነሱት ችግር አንዱ የኬክ ፕሌት በሀገር ውስጥ አለመኖር ነው ያለው ሳሙኤል፤ በሀገር ውስጥ የሚያመርቱትም ቢሆን፤ ይህ የኬክ ፕሌት ለማምረት የሚጠቀሙበት ጥሬ እቃ ከውጭ የሚያስገቡ በመሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ይቸገራሉ:: ይህ የፈጠራ ሥራ ግን በኬክ ዙሪያ ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን የሚቀርፍና ለብዙ ሰዎች የሥራ እድል የሚፈጥር ነው ይላል::
አሁን ላይ ከውጭ የሚመጣው የአንድ የኬክ ፕሌት ዋጋ 120 ብር ሲሆን፤ የእነርሱ ምርት በ45 ብር ለገበያ እየቀረቡ ይገኛል:: ስለዚህ ወደ ኬክ ማምረት ሥራ ለመስማራት ለሚፈልጉ አካላት በቅርበት ሊያገኙት እና ወጪም ሊቀንስላቸው እንደሚችል ይናገራል::
አሁን ላይ ለሰባት ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን፤ በቀጣይም በርካታ የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችላቸው እንደሆነ አመላክቷል:: በቀጣይም አስፈላጊ የሆኑ ማሽኖችን አሟልቶ በሙሉ አቅም ማምረት ሲቻል ጥራት ላይ የሚነሳውን ችግር መፍታት ይቻላል:: ጥራት ያለው ተወዳዳሪ የሆነ ምርቶችን በማምረት ከውጭ የሚገቡት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ብቻ ሳይሆን ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ጭምር የውጭ ምንዛሪ ማምጣት ይቻላል ብሏል::
ይህን የፈጠራ ሃሳብ ለመሥራት ያነሳሳቸው በአካባቢያቸው ላይ የሚያዩት የተጣሉ ቆሻሻዎች እንደሆኑ የሚናገረው ወጣት ሳሙኤል፤ ችግሩን ለመቅረፍ ደግሞ የሚያስችል የመፍትሔ ሃሳብ ለማምጣት ባደረጉት ጥረት የፈጠራ ሃሳቡ መጠንሰሱን ይናገራል:: ወደዚህ ሥራ ከገቡ ዓመት ከሦስት ወራት ገደማ የሆናቸው ሲሆን አሁን ምርቶቻቸውን እያመረቱ ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ:: በተለይ የኬክ ፕሌት በጎንደር እና በባህር ዳር ከተማ በጥሩ ሁኔታ እየተሸጠ መሆኑን ይናገራል::
አሁን ላይ በወር ሶስት ኩንታል (300 ኪሎ) ያህል የኬክ ፕሌት እያመረቱ ሲሆን፤ የገበያ ፍላጎቱ ግን ከዚህም በላይ እንደሆነ ነው ያመላከተው:: አሁን ላይ እየተመረተበት ያለው ማሽን በራሳቸው የተሠራና ማኑዋል ማሽኖች ሲሆን፤ እነዚህ ማሽኖች ዘመናዊ ዲጂታል ማሽን መቀየር ከተቻለ በወር የሚመረተው ምርት መጠን በአንድ ቀን ማምረት እንደሚቻል ያስረዳል::
ሳሙኤል እንደሚለው፤ የዘንቢል ምርቶችን እንዲሁ በባህር ዳር እና ጎንደር ከተማ በተለይም ለልብስ ቤቶች፣ ለአትክልት ቤቶች እያቀረቡ ይገኛሉ:: ዘንቢሎቹ ሦስት ዓይነት መጠን ያላቸው ሲሆን፤ ዋጋቸውም እንደየመጠናቸው የሚለያይና አራት፣ ሰባትና አስር ብር ድረስ ነው:: ዘንቢሎቹ አሁን ላይ ሸማቹን እያማረሩ ወዲያውኑ የሚቀደዱ ፈስታሎችን በመተካት ሸማቱ ረጅም ጊዜ ሊገለገልባቸው የሚችሉ ናቸው::
አሁን ላይ የተለያዩ ስልጠናዎች እያገኙ መሆናቸውን የሚናገረው ሳሙኤል፤ እነዚህ ምርቶች በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ከትንሽ ነገር ላይ ተነስተው መሥራት ከቻሉ ዲጂታል ማሽኖች ቢያገኙ ደግሞ ጥራቱን ለመጨመር እና የበለጠ ምርቶቻቸው በማሻሻል ጥራት ያላቸው ተወዳዳሪ ምርቶችን ማምረት እንደሚችሉ ይገልጻል::
ይህ የፈጠራ ሥራ በማሳደግ ምርቶቻቸው ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ጠቅሶ፤ በቀጣይም የሀገር ውስጥ ፍጆታን ማሟላት ከተቻለ ወደ ውጭም ኤክስፖርት የማድረግ እቅድ እንዳላቸው አመላክቷል::
ሌላኛው ፈጠራ ሥራ የአፍሮ ሪድ የሞባይል የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ነው:: የአፍሮ ሪድ የሞባይል መተግበሪያ የማስታወቂያና የማርኬቲንግ ባለሙያ ወጣት ናርዶስ ዓለማየሁ እንደምትለው፤ ይህ መተግበሪያ በእ.ኤ.አ 2020 በአራት ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ እንደሆነ ትናገራለች:: የዚህ መተግበሪያ ጠቀሜታ ንባብ ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍም ያለመ ነው::
አሁን ላይ ባለው የወረቀት ዋጋ ንረት የተነሳ ደራሲያን ሥራቸውን ለማሳተም የማይችሉበት እና አንባቢውም እንዲሁ የታተመውን መጽሐፍ እንኳን በተተመነለት ዋጋ ለመግዛት የማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል:: የምትለው ናርዶስ፤ የሁለቱን ችግር ባገናዘበ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርግ መተግበሪያ ለማዘጋጀት በማለም ወደዚህ ሥራ እንደገቡ ትናገራለች::
ናርዶስ እንደምትለው፤ መተግበሪያው መጻሕፍት በዲጂታል ለማንበብ ምቹ በሆነ መልኩ ተዘጋጅተው ይቀርባሉ:: በተጨማሪም ከሥራ ጋር ለማይመቻቸው፣ ማየት ለተሳናቸው እና ማዳመጥ ለሚቀናቸው ሰዎችም እንዲሁ የሚፈልጋቸውን መጻሕፍቶች በኦዲዮ ቅጂ ይቀርባል:: በኮፒ ራይት አንጻር መጽሐፉን በኮፒ እንዳይወሰድ የሚያደርግ አሠራር የተዘረጋለት ሲሆን፤ መጽሐፉን የገዛው ሰው በየትኛው መንገድ ለሌላ ሰው ማጋራት እንዳይችል ተደርጓል::
ከዚህ በተጨማሪ መተግበሪያው ደራሲው ምን ያህል መጽሐፍ እንደተሸጠለት ለማወቅ የሚያስችለው አሠራር ያለው በመሆኑ ደራሲ የተሸጠለትን መጽሐፍ አስቀድሞ ማወቅ እንዲችል ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ናርዶስ ትገልጻለች::
መጻሕፍት ወደ መተግበሪያው የሚገቡትም በደራሲው ፈቃደኛነት ላይ ተመስርቶ ነው የምትለው ናርዶስ፤ አሁን ላይ ከ200 በላይ ነባር እና አዳዲስ ደራሲዎች በህብረት በመሥራት ከ500 በላይ መጻሕፍትን ተደራሽ ማድረግ ችለዋል ነው ያለችው::
‹‹የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች በማስተዋወቅ የንባብ ባህል ለማዳበር እየሠራን በመሆኑ እስካሁን ከ11ሺ በላይ ሰዎች መጻሕፍት መግዛት የቻሉበት ሁኔታ አለ›› የምትለው ናርዶስ፤ ህብረተሰቡን ወደ ዲጂታል በማምጣት መጻሕፍትን በዲጂታል ሲስተም ገዝተው እንዲጠቀሙ ለማድረግ የማስታወቂያ ሥራዎችን እየሠሩ መሆኑን አመላክታለች::
‹‹አንድ ደራሲ መጽሐፉ ወደ መተግበሪያ እንዲገባ ለማድረግ የሚያወጣው ምን ዓይነት ወጪ የለም:: መጽሐፉ መተግበሪያው ላይ ከተጫነና ከተሸጠ በኋላ ግን የደራሲው ድርሻ 50 በመቶ ያህል ሲሆን የተቀረው 50 በመቶ የድርጅቱ ድርሻ ይሆናል›› ትላለች::
አሁን ላይ ደራሲው ሆነ አንባቢዎች መጻሕፍትን በዲጅታል በዚህ መንገድ ማግኘት በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸው አስተያየት እየሰጣቸው መሆኑን ጠቅሳ፤ በቀጣይ ተደራሽነታቸውን በማስፋት የንባብ ባሕልን ለማዳበር እንደሚሠሩ አመላክታለች::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም