ሀገር እና ሕዝብን ታሳቢ ያደረገ የፖለቲካ ሥብዕና ለጀመርነው የፖለቲካ ህዳሴ አልፋና ኦሜጋ ነው!

የአንድ ሀገር የፖለቲካ ህዳሴ እውን ሊሆን የሚችለው ከሁሉም በላይ የፖለቲካ ልሂቃን ከግላዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶች ወጥተው ሀገር እና ሕዝብን ታሳቢ ያደረገ የፖለቲካ ሥብዕና መፍጠር ሲችሉ፤ ይህንንም በቀጣይ ትውልድ ላይ መሥራት የሚያስችል ተነሳሽነት ሲያዳብሩ ብቻ ነው። ይህ የፖለቲካ ህዳሴ አልፋና ኦሜጋ ነው።

ግለሰባዊ እና ቡድናዊ የፖለቲካ ፍላጎቶች በየትኛውም መንገድ እና ሁኔታ በሀገራዊ የፖለቲካ መድረኮች ላይ ደምቀው ቢታዩ፤ በማኅበረሰብ ውስጥ በአንድም ይሁን በሌላ ተደማጭነት አግኝተው አደባባዮችን ቢሞሉ፤ ውሎ ሲያድር፤ የችግር ፣ የሁከት እና የግርግር ከዚያም አልፎ የከፋ ጥፋት ምንጭ መሆናቸው የማይቀር ነው ።

ለዚህ ደግሞ የሀገራችንን የሰባት አስርት ዓመታት የፖለቲካ ትርክት ማየት በራሱ በቂ እና ተገቢ ነው። በእነዚህ አስርት ዓመታት ውስጥ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶች በተለያዩ ወቅቶች የተፈጠሩ የለውጥ ሀገራዊ መነቃቃቶችን ትርጉም አልባ ወደሆነ የጥፋት ትርክቶች ወስደውታል። በዚህም በየዘመኑ የነበረውን የለውጥ ተስፈኛ ትውልድ የተስፋው ባለቤት እንዳይሆን አድርገውታል።

እነዚህን ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶች የሚገራ በመታጣቱ ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ የሚደራደር፤ ከዛም አልፎ ሀገረ መንግሥቱን / የሀገር ህልውናን ስጋት ውስጥ የሚከት ከጥፋት እና ከሁከት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት፤ ይህንንም በአደባባይ ያለአንዳች ሀፍረት ዋነኛ የፖለቲካ ስትራቴጂ አድርጎ የሚወስድ ልበ ደንዳና የፖለቲከኞች ስብስብ ፈጥሯል።

በቀደመው ዘመን ከፍ ባለ የለውጥ ተስፋ፤ ስለሀገር እና ስለሕዝብ ቀጣይ እጣ ፈንታ በብዙ መነሳሳት እና ቁርጠኝነት የተንቀሳቀሰው ትውልድ ፤ በግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶች ተጨናግፎ፤ ሀገር እንደ ሀገር በከፋ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ገብታለች፤ በዚህም ያልተገቡ ዋጋዎችን ከመክፈል ባለፈ ብዙ ያደሩ የቤት ሥራዎች ተሸክማ እንድትጎብጥ ሆናለች ።

ከብዙ ሕይወት መሥዋዕትነት እና ውድመት በኋላ የተገኙ “የአሸናፊዎች የአሸናፊነት ትርክቶችም”፤ የሕዝብ ድል ባለመሆናቸው ተመልሰው ሀገርን ለሌላ ተጨማሪ ውድቀት ዳርገዋል። ሀገርም ከአንድ ግጭት ወደ ሌላ ግጭት እየተንደረደረች በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድትኖር ተገድዳ ሆናለች። በዚህም ትውልዶች ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱበት ሁኔታዎች ተፈጥረው አልፈዋል።

እንደሀገር ለዘመናት ይዘናቸው የመጣንባቸው የፖለቲካ እሳቤዎች የሕዝብን እውነተኛ መሻት መሠረት ያላደረጉ፤ በግለሰቦች እና ቡድኖች ፍላጎት የተጠለፉ በመሆናቸው፤ ሕዝባችን የፈለገውን እና የየዘመኑ ትውልድ በደረሰበት የመረዳት መጠን የከፈለውን መሥዋዕትነት የሚመጥን ተገማች ፍሬ እንኳን ማፍራት ሳይችል ረጅም ዘመን በተስፈኝነት ለመጓዝ ተገድዷል።

በቅርቡ እንደሀገር የተፈጠረውን የሕዝብ የለውጥ መሻት በተለመደ መሥዋዕትነት ማዋለድ ቢቻልም፤ ለውጥ ሊፈጥረው በሚችለው ስሜታዊነት እና የተቃርኖ ትርክቶች ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው ባሰቡና ከፍ ባለ የልብ ድንዳኔ በተንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ቡድኖች ያልተገባ መንገጫገጭ ውስጥ እንዲገባ ሆኗል ።

ፖለቲካን ከብሔራዊ ጥቅም ለይቶ ያለማየት ችግር በፈጠረው ግራ መጋባት እና ግርግር ሕዝባችን ለከፋ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች ተጋልጧል፤ ፈተናዎቹ የመላው ሕዝባችንን ጓዳ ከማንኳኳት አልፎ ሀገረ መንግሥቱን ስጋት ውስጥ የጨመረበት ሁኔታ ተከስቶ ነበር። ከዚህም ባለፈ ሕዝባችን የለውጥ ተስፋውን ተጨባጭ በሚያደርግ የለውጥ ሥራዎች ውስጥ በሙላት እንዳይሰለፍ አድርጎታል።

እነዚህ ካልጠራ የፖለቲካ ሥብዕና የሚመነጭ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶች ዛሬም ቢሆን የሕዝባችንን የለውጥ መሻት እየተገዳደሩ ናቸው። ከተዛቡ እና ሀሰተኛ ትርክቶች ፤ ከጽንፈኛ እና አክራሪነት አስተሳሰብ ፤ በሀገር እና በሕዝብ ላይ ከሚሟረቱ ሟርቶች እና ርግማኖች በስተጀርባ ያሉ ፍላጎቶች የዚህ እውነታ ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው ።

እንደሀገር የሕዝባችንን ዘመን ተሻጋሪ የቁጭት መሻት (ሰላም እና ልማትን) እውን ለማድረግ ከሁሉም በፊት ፖለቲከኞች፤ የሕዝባችንን መሻት የሚመጥን የፖለቲካ ሥብዕና መፍጠር ይኖርባቸዋል። በግለሰብ ይሁን በቡድን የተገዙላቸው የፖለቲካ እሳቤዎች የሕዝባችንን ፍላጎቶች መሠረት አድርገው የሚነሱ እና ለዚሁ የተገዙ ሊሆኑ ይገባል።

ሕዝባችን አሁን ላይ አብዝቶ የሚፈልገው ከፈተናዎች የሚያሻግር ፖለቲካ እንጂ በፈተናዎቹ የሚቆም ፖለቲከኛ አይደለም። የሚፈልገው በብሄራዊ ጥቅሞች የሚደራደር ፤ በሀገረ መንግሥቱ የሚቆምር ሳይሆን ፤ ሀገረ መንግሥቱን የሚያጸና፤ ብሔራዊ ጥቅሞቹን ዘመኑን በሚመጥን እሳቤ ተጨባጭ የሚያደርግ ፖለቲካኛ ነው ።

በተዛቡ እና ሀሰተኛ በሆኑ ትርክቶች፤ በጽንፈኛና አክራሪነት አስተሳሰቦች፤ በሀገር እና በሕዝብ ላይ በሚሟረቱ ሟርቶች እና ርግማኖች ራሱን ገንዞ ፤ በሕዝብ መከራ እና ስቃይ ለማትረፍ ሌት ተቀን የሚዳክር ፤ ይህንንም የፖለቲካ አልፋ እና ኦሜጋ አድርጎ የሚያስብ የፖለቲካ ኃይል ለሀገርም ለሕዝብም የሚፈይደው ነገር የለም።

እንደሀገር አሁን ላይ ራሱን የፖለቲካ ልሂቅ አድርጎ የሚወስድ፤ የዚህ ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት እጋራለሁ የሚል የትኛውም ግለሰብ ከሁሉም በላይ ከግላዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶች ሊወጣ ፤ ሀገር እና ሕዝብን ታሳቢ ያደረገ የፖለቲካ ሥብዕና ሊፈጥር ይገባል፤ ለዚህ የሚሆን እርቅም ከራሱ ጋር መፍጠር ይኖርበታል። ይህ ለጀመርነው የፖለቲካ ህዳሴ አልፋና ኦሜጋ ነው!

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You