
-አልፋራጅ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከቀረጥ ነፃ ሱቅ ከፈተ
አዲስ አበባ፡- የቱሪስቶችን የጊዜ ቆይታ የሚያራዝሙ፣ ለአዲስ አበባ ከተማና በመላው ሀገሪቱ ገጽታ ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ማዕከላት እንዲስፋፉ በሚያስችሉ ተግባራት የግሉ ዘርፍ ሊሳተፍ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዣንጥራር ዓባይ ገለጹ። አልፋራጅ ትሬዲንግ ኩባንያ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከቀረጥ ነፃ ሱቅ መክፈቱን ጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዣንጥራር ዓባይ ትናንት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተመረቀው ከቀረጥ ነፃ (duty free) የንግድ ማዕከል እንደገለጹት፤ የግሉ ዘርፍ ለከተማው ለውጥ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ይህ ምዕራፍ የአልፋራጅን ቁርጠኝነት የሚያሳይ፣ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ገፅታ ለማሳደግ እና ተስተናጋጆች የተመቻቸ የገበያ ማዕከል ውስጥ የሚፈልጉትን እንዲገበያዩ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከ92 ዓመታት በላይ የዘለቀና ከድሬዳዋ ከተማ አንስቶ እስከ አዲስ አበባ ከተማ ጉልህ ስፍራ ይዞ የዘለቀው ኩባንያው ውድ የሆኑ እቃዎችን ከቀረጥ ነጻ (duty free) እና በችርቻሮ ንግድ ደረጃ ያለ ድርጅት መሆኑንም አቶ ዣጥራር አመልክተዋል።
ኩባንያው የከፈተው ማዕከል በተለይ ለአዲስ አበባ ከተማ ትልቅ አቅም ይሆናል፣ ለከተማው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉም ጠቁመዋል። ተጓዦች የኢትዮጵያን ውበት ተመልክተው የማይረሳ ቆይታ ኖራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ እየተሠራ ያለው ልማት ከተማውን የቱሪስት መዳረሻ ማዕከል ማድረግ የመጀመሪያ ዓላማ ነው ያሉት አቶ ዣንጥራር፤ አዲስ አበባ በመሸጋገሪያ ከተማነት ብቻ እንድታገለግል ሳይሆን የቱሪስቶች መቆያም እንድትሆን ፍላጎት አለን ብለዋል።
ቱሪስቶች ሲቆዩ ደግሞ የተለያዩ ምርቶችን ገብይተው ለከተማውና ለሀገር የውጭ ምንዛሬን በማስገባትም የላቀ አቅም የሚፈጥር መልኩ መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ እንዲህ አይነት ትግበራ እንዲበዛ እንፈልጋለን ነው ያሉት።
የአልፋራጅ ትሬዲንግ በቦሌ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት ባለው ልምድ በመነሳት በከተማው እንዲስፋፋ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የቱሪስት ጊዜን ማራዘም፣ ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር እና ደረጃውን የጠበቀ ምርት በማቅረብ ግብይት እንዲፈጠር ማድረግ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ የሚያስችል በመሆኑ መንግሥት የሚደግፈው መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የአልፋራጅ ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አይደሩስ ሁሴን መሐመድ፤ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተከፈተው የአልፋራጅ ከቀረጥ ነፃ ሱቅ እያደገች ያለችውን ኢትዮጵያን የሚያመለክት፣ ኢትዮጵያ ወደላቀ ደረጃ ለመሸጋገር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
“ይህ ከችርቻሮ መሸጫ ቦታ በላይ ነው፣ ኢትዮጵያ ደረጃዋን ከፍ እያደረገች ስለመሆኑ የሚያሳይ መገለጫ ነው” ብለዋል። አዲስ አበባን ለማስዋብ እና ለማዘመን በመንግሥት በኮሪዶር ልማትና በሌሎች ልማቶች የይቻላል ስሜት የታየበት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀገሪቱ እየታየ ያለውን ሰፊ ለውጥ የሚያንፀባርቅ መሆኑን አመልክተዋል።
“ከተማችን ዓለም አቀፋዊ መዳረሻ እየሆነች ነው” ያሉት አይደሩስ፤ እንዲህ ያለው እድገት የግል ባለሀብቱን እና ዜጎችን ትብብር እንደሚጠይቅ አጽንኦት ሰጥቷል።
በዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም