ከተማ እና ከተሜነት

ኢትዮጵያ ጥንታዊት ሀገር ነች። ባስቆጠረቻቸው በርካታ ሺህ ዓመታትም ግብርናን ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ አድርጋ ስትጠቀም ኖራለች። ዛሬም ድረስ ግብርናን የሚተካ የኢኮኖሚ ሴክተር አልተገኘም። ይህ መሆኑ ደግሞ ካላት ሕዝብ ውስጥ እስከ 80 በመቶ የሚደርሰው በግብርና የሚተዳደር እና በገጠር የሚኖር ነው። ስለዚህም በሀገራችን ከተሜነት ገና በአዝጋሚ ሂደት ውስጥ እንደሚገኝ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

እንደሀገር ሲታይ የከተሜነት ደረጃችን 22 በመቶ ነው፤ ይህም ሲባል 78 በመቶ የሚሆነው ማህበረሰብ በገጠር ይኖራል ማለት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ስናይ በአሜሪካ ከተሜነት 81 በመቶ፣ አውሮፓ 78 በመቶ፣ ኤዤያ ሀገሮች ደግሞ 76 በመቶ የደረሰ ሲሆን አፍሪካ በአማካኝ 43 በመቶ አካባቢ ነው። ከአፍሪካ ውጥም ከሰሃራ በታች ያሉት 22 በመቶ ላይ ናቸው። ከላይ እንዳነሳነውም የኢትዮጵያ የከተሜነት ደረጃ ገና 22 በመቶ ደረጃ የሚገኝ በመሆኑ አብዛኛው ማህበረሰብ የከተማ አገልግሎት ተጠቃሚ አይደለም።

ከኢኮኖሚ አንፃር ስናይ የዓለም ምርት 80 በመቶ የሚሆነው ከተማ ውስጥ ነው የሚመረተው። እንደሀገር ደግሞ ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ጂዲፒ ደግሞ ከ50 እስከ 60 በመቶ አዲስ አበባ ውስጥ ነው የሚመረተው። ይህም የሚያሳየው ከተማ ማለት የኢኮኖሚ ማዕከል መሆኑን ነው። ስለዚህ ከተሜነትን ሳናረጋግጥ ሀገርን መቀየር እና ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደማንችል በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

ኢትዮጵያ ከሶስት ሺህ ዓመት በፊት የከተማ ልምድ እንደነበራት የተለያዩ አስረጂ ፅሁፎች ያነሳሉ። ለምሳሌ አክሱማይትን እንደምሳሌ መውሰድ እንችላለን። በዚያን ጊዜ የከተሜነት ባህሪ ነበረው። ከተማ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይቆረቆር እንደነበረ ታሪክ ያስረዳል። እንደታሪክ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ አለን፤ ይሁንና ከተማ ተብለው የተቆረቆሩት ታስቦበት አካታች በሆነ፤ ለሁሉም በሚመችና ሁሉንም ማሕቀፍ በሚችል መልኩ የተመሠረቱ ባለመሆናቸው ብዙ ጉድለቶች ይታይባቸዋል። የከተሞቻችንን ታሪክ ስናይ ግማሹ ካምፕ ነበረ፤ በሂደት ወደ ከተማነት የመጣ ነው። በሌላ በኩል ሰው የሚበዛበት ቦታ ትናንሽ ንግዶች የተጀመሩበት፤ ሰው እየጨመረ ሲመጣ በሂደት ወደ ከተማ የመጣ ነው። እነዚህ የአከታተም ሂደቶች ደግሞ ከተሞቻችን ዘመናዊ እና የተሟላ አገልግሎት ለነዋሪዎቻቸው እንዳይሰጡ አድርጓቸው ቆይቷል።

ከተሞቻችን በዕቅድ ያልተመሠረቱ ፤ በፕላን ያልተመሩ በመሆናቸው ለኑሮም ፤ ለሥራም አመቺ አይደሉም። ስለዚህም ከተሞቻችንን እንደገና መገንባት እና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ በማስፈለጉ ወደ ኮሪዶር ልማት መግባት የግድ ብሏል። በአሁኑ ወቅትም 37 በሚደርሱ የሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች የኮሪዶር ልማት እየተከናወነላቸው ይገኛል።

የከተሞች አውራ ተብላ የምትወሰደው አዲስ አበባም ብትሆን በዘፈቀደ የተመሠረተች ከተማ በመሆኗ ስሟና ግብሯ ተራርቆ ቆይቷል። ከተመሠረተች ከ130 ዓመት በላይ የሆናት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች መናኸሪያ፤ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአፍሪካ መዲና እና ተለያዩ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መገኛ ነች። ከ90 በላይ ኤምባሲዎችን በማቀፍም በዓለም ላይ ካሉት ጥቂት የዲፖሎማቲክ ማዕከል ከሆኑት ከተሞች ውስጥ ግንባር ቀደሟ ነች።

ሆኖም ይህቺ ከተማ በእርጅና ብዛት ጎብጣ መነሳት ከተሳናት ዓመታት ተቆጥረዋል። ከተሠሩ ዘመናትን የተሻገሩት ደሳሳ ጎጆዎቿ በተአምር ከመቆማቸው በስተቀር ቤት የሚለውን መስፈርት በምንም አይነት መልኩ የሚያሟሉ አይደሉም። ግድግዳዎቻቸው ፈራርሶ፤ ጣራዎቻቸው ወይቦ አዲስ አበባን ከዕድሜዋ በላይ አስረጅተዋታል።

ቤቶቹ ሰዎች ይኖሩባቸዋል እንጂ ከንፋስም ሆነ ከጸሃይ እንዲሁም ከዝናብ ማንንም አያስጥሉም። በበጋም ሆነ በክረምት በእነዚህ ቤቶች ውስጥ መኖር ስቃይ ነው። በተለይም በመሃል የከተማዋ ክፍል የሚገኙት ቤቶች ከተማዋ ስትቆረቆር ጀምሮ የነበሩ በመሆናቸው የሚያፈርሳቸው አካል ባይኖር እንኳን በራሳቸው መፍረሳቸው አይቀሬ ነበር።

ይህንኑ በመረዳትም ከተማዋን ምሉዕ ባልሆነ መልኩ የከተሜነት ባህሪ ለማስያዝ ሙከራዎች ቢኖሩም ብዙም የሰመሩ አልነበሩም። ፍልውሃ አካባቢ የተቆረቆረችው አዲስ አበባ በተለያየ ጊዜ ማስተር ፕላን እየወጣለት ስትጠጋገን ዓመታትን አሳልፋለች። በየጊዜው ከተማዋን ይመጥናል የተባለ ማስተር ፕላን ሲወጣና ወደ ተግባር ሲገባ ተመልክተናል።

ይሁን እንጂ አዲስ አበባን ለማዘመን በሚል የተለያዩ ማስተር ፕላኖች ወጥተው አተገባበራቸውም ጉራማይሌ ሆነው በመጡበት ተሸኝተዋል። ማስተር ፕላን የመሬት አጠቃቀምን እና ልማትን፣ የህንፃ አሠራርንና መዋቅርን እና የገበያ ቦታዎችንና ከፍተኛ መንገዶችንና ንዑስ መንገዶች አረንጓዴ ሥፍራዎችን ክፍት ቦታዎችንና የህንፃ ዓይነቶች በዝርዝር ይይዛል። በተጨማሪም ማስተር ፕላን ዓላማዎች ግቦች ያሉት የአንድ ከተማ ቁልፍ የዲዛይን ሰነድ ሲሆን ሌሎች ዝርዝር የፕላን መረጃዎችን የያዙ ከተሞች ከፕላኑ ውጭ አፈንግጠው ምንም ዓይነት ነገሮች እንዳይሠሩ የሚገድብ እስከ አስር ዓመት የአፈፃፀም ጣራ ያለው ዝርዝር ፕላን መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ሆኖም በየወቅቱ በነበሩት ማስተር ፕላኖች ለነዋሪው ክብር የማይሰጡና ይባሱንም ነዋሪውን ከአካባቢው አፈናቅለው የተም የሚበትኑ ነበሩ። መሃልኛው የአዲስ አበባ ክፍል ችምችም ብለው በተሠሩ ቤቶች የታጨቀ፤ ከዘመኑ ጋር ያልዘመነ፤ ከ130 ዓመታት በፊት በነበረው የቀጠለ እና በአሁኑ ወቅት ያለውን የአኗኗር ሁኔታ የማይመጥን ነው። አብዛኞቹ ቤቶች አንድ መጸዳጃ ቤትን ለሰላሳ ፤ለአርባ የሚጠቀሙ ብዙዎችም መጸዳጃ ቤት የሌላቸውና በየጥጋጥጉ ለመጠቀም የተገደዱ ዜጎች ያሉባቸው አካባቢዎች ናቸው።

እነዚህ አካባቢዎች የአዲስ አበባን የኋሊት ጉዞ የሚያሳዩና የከተማዋ የድህነት መገለጫዎችም ናቸው። ጎዳና ተዳዳሪነት፤ ሴተኛ አዳሪነት ፤ ማጅራት መቺነትና የመሳሰሉት ኢሞራላዊ እና ወንጀል ነክ ድርጊቶች የሚፈጸምባቸው ናቸው። ቁማር ቤቶች፤ጫት ቤቶች፤ ሺሻ ቤቶችና አረቄ ቤቶች የእነዚህ አካባቢዎች መገለጫዎች ናቸው።

በእነዚህ አካባቢዎች መሸት ሲል በቀላሉ ወጥቶ መግባት አይቻልም። እነዶሮ ማነቂያ፤ እሪ በከንቱና ውቤ በረሃ የመሳሰሉ ሰፈሮች ለእዚህ አባባል ምስክር የሚሆኑ ናቸው። ስማቸውም ከግብራቸው የተቀዳ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል።

ፒያሳን የመሳሰሉ አካባቢዎች ስማቸው ገናና ቢሆንም በገቢር ግን ስማቸውን የሚመጥን ገጽታ የላቸውም። ምንም አይነት ዘመናዊነት የማይታይባቸው ኋላቀር አካባቢዎች ከመሆናቸውም በላይ በስመ አራዳ ለዘመናት ድህነት ተጭኗቸው የቆዩ ናቸው ። ስምና ግብር በተራራቀበት በእነዚህ አካባቢዎች ሰዎች በአንዲት ክፍል ውስጥ ቆጥና ምድር ሠርተው ፤ መጸዳጃ ቤት ተጋርተው ፤ በአንዲት ክፍል አስር፤ አስራ አምስት ሆነው ተደራርበውና ተነባብረው የሚኖሩባቸው የድህነት ጥግ የሚታይባቸው የከተማችን አካል ነበሩ።

ስለሆነም ይህንን ነባራዊ ሀቅ ለመቀየር ከ2016 ዓ.ም መጋቢት ጀምሮ በሁለት ዙር የኮሪዶር ልማት እየተከናወነ ይገኛል። በመጀመርያው ዙር ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ በመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፣ ከቦሌ ተርሚናል ወደ ጎሮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አራት ኪሎ የሚወስዱ ኮሪዶሮች ተገንበተው አዲስ አበባን ውበት እና ዘመናዊነትን አላብሰዋታል።

በሁለተኛው የኮሪዶር ልማትም በስምንት አቅጣጫዎች ልማቱ ተጧጡፏል። ከወዲሁም ካሳንቺስ እና ጎሮን የመሳሰሉ አካካቢዎች እጅን አፍ ላይ በሚያስጭን መልኩ ተውበው የአዲስ አበባ አዲስ ገጽታ መሆን ችለዋል። የሌሎቹም አካካቢዎች ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን በከተማዋ ባደረግነው ቅኝት ለመረዳት ችለናል።

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በእስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You