
ጋምቤላ፡- ያለአግባብ ወጪ የሆነን የመንግሥት ብር በምርምራ አረጋግጦ ተመላሽ እንዲሆን ማድረጉን የጋምቤላ ክልል የሥነ-ምግባር እና ፀረሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ የሥነ-ምግባር እና ፀረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ቱት ንዑት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በጡረታ የተሰናበቱና የለቀቁ ሠራተኞች ሆነው ሳለ በስማቸው ደመወዝ እንደሚከፈል ተደርጎ ያለአግባብ የወጣ 430 ሺህ 260 ብር ለክልሉ ፋይናንስ ተመላሽ ተደርጓል። ገንዘቡ የተመለሰው ህብረተሰቡ የሰጠውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ የማጣራትና የማረጋገጥ ሥራ ከተከናወነ በኋላ ነው ብለዋል።
በአኮቦ ወረዳ የመንግሥት ሞተር ጀልባ በመግዛት ለግል ጥቅም ለማዋል የተንቀሳቀሱ ግለሰቦችም ተይዘው 5 ሚሊዮን 649ሺህ 888 ብር በክልሉ ፀረ ሙስና ቢሮ በኩል ለመንግሥት ገቢ ስለመደረጉ ኮሚሽነር ቱት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ማኔጅመንት ሳያጣራ እና እውቅና ሳይሰጥ የዳይሬክቶሬትነት ሥራ የተሰጣቸው አራት የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊዎች ለጊዜው የተሰጣቸው ሃላፊነት ታግዶ በውድድርና በመንግሥት መስፈርት መሠረት አካሄዱ እንዲስተካከል መደረጉንም አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ በክልሉ ሶስት ዞኖች እና አንድ ከተማ አስተዳደር በየዘርፉ የግንዛቤ ስልጠና ስለመስጠቱም ገልጸዋል።
በክልሉ የግዢ ክፍያዎች፣ የመንግሥት ክፍያዎች ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዲቀረፉ ለ54 ተቋማት የግንዛቤ ስልጠና መስጠት እንደተቻለና ግለሰቦች ብልሹ አሠራሮችን ሲመለከቱ በነፃ የጥቆማ ቁጥር 8623 ላይ እየደወሉ እንዲያሳውቁ መመቻቸቱን ጠቅሰዋል።
ለክልሉ ተቋማት አመራሮች የሥነምግባር መኮንኖች እና ፋይናንስ ባለሙያ በተመሳሳይ መልኩ ስልጠና እንደተሠጠም ገልጸዋል።
ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ኮሌጅ ደረጃ ላሉ ተማሪዎች ግንዛቤ እንደተፈጠረ አስረድተው፤ ከክልል እስከ ወረዳ ተቋማት አዳዲስ የሥነምግባር መኮንኖችን መዋቅር ማሟላት እንደተቻለም ጠቅሰዋል። ከክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጋር በሥነምግባር ኮሚሽን የጋራ ሰነድ ላይ ውይይት በማድረግ ለሁሉም ተቋማት ሥልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።
ውስብስብ የሙስና ሥራዎች መኖራቸው እና መረጃ ቀድሞ የመስጠት ችግሮች መኖሩ በሥራቸው ላይ ተግዳሮት የፈጠሩ ጉዳዮች እንደሆኑ አስረድተዋል። የሙስና ምርመራዎች ከሙስና ኮሚሽኑ የወጡ መሆናቸውና በፖሊስ ኮሚሽን ስር የሚታዩ መሆኑ አቃቤ ሕግ ወደ ፍትህ ቢሮ መሄዱ ለፈጣን የሙስና ምርመራ ተግዳሮት ሆኗል ብለዋል።
ሰዎች ፍርድ ሳይወሰን ሊፈቱ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለና የፍርድ ጊዜ በሚዲያ ያለመተላለፍ ችግር መኖሩን ጠቅሰዋል፤ ሙስናው ምንም ይሁን ምን በሚዲያ እንዲተላለፍ ቢደረግ ህብረተሰቡ ሊማርበት እንደሚችል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ በለውጡ ዓመታት ደንቦች፣ መመሪያዎችና አዋጆች ላይ ማሻሻያ ስለማድረጉም ጠቁመዋል። የክልሉን የሥነምግባር አደረጃጀት መመሪያ በማውጣት በ41 የትምህርት ተቋማት የሥነ-ምግባር ክበብ የማደራጀት ሥራ መሠራቱንም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
በኮሚሽኑ ባሉ ክፍት መደቦችም የሰው ኃይል እንዲሟላ በማድረግ የተቋሙን ተደራሽነት የማጠናከር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም