
አዲስ አበባ፡– የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች/ በጎ አድራጎት ድርጅቶች አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ሥራዎችን እንዲሠሩ የሚፈቅድ ሕግ እየተዘጋጀ መሆኑን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ገለጸ። ባለስልጣኑ አዋጅ 1113/2011 መሠረት በማድረግ 12 መመሪያዎችን ሥራ ላይ መዋሉን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የሕግ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ብዛየነ ገብረእግዚአብሄር ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ እየተዘጋጀ ያለው የሕግ ማሕቀፉ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከሌሎች አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር አብረው መሥራት እንዲችሉ የሚደነግግ ነው።
የሕግ ማሕቀፉ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የገንዘብ፣ የአቅም ግንባታ፣ ልምድ ልውወጥ እና ሌሎች የተለያዩ ድጋፎች እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነም አስታውቀዋል።
በዝግጅት ምዕራፍ ያሉ የሕግ ማሕቀፎቹ በጎ አድራጎት ድርጅቶች አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ሥራዎችን ለመሥራት የሚችሉበት ፤ ሁለት እና ከእዛ በላይ ሆነው በመደራጀት በአንድ ጥላ ስር ሊያስተዳድሩ የሚችሉበት የህብረት እና የህብረት ህብረቶች ደንብ መሆኑን አመልክተዋል ።
የሚዘጋጀው ሕግ፤ ዓለም አቀፍ ሆነው ከዚህ በፊት በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የማይታቀፉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመዝግበው የመግቢያ ስምምነት ፈርመው የሚሠሩ ድርጅቶች የሚስተናገዱበት ይሆናል ብለዋል። ምዝገባው ሥርዓቱም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወጥቶ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
ለምሳሌ ኬንያ ላይ የተመዘገበ አንድ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገባ ከሀገር በቀል ድርጅት ጋር ክፍለ አህጉራዊ በሚል እንዲመሰርቱ፣ በአፍሪካ ላይ ለመሥራትም ያስችላቸዋል። ከአባሎቻቸው መብትና ጥቅም ጋር የተያያዘ ማናቸውንም ሕጋዊ ዓላማ ለማሳካት ሊመሰርቱ ያስችላቸዋል ብለዋል።
ለጋራ ግባቸው ስኬታማነት፣ አባሎቻቸውን ማስተባበር እና መደገፍ፣ የሃሳብ፣ የመረጃ እና የልምድ ልውውጥ ማካሄድ፣ የአባላትን አቅም መገንባት እና ሀብት ማሰባሰብ የሚሉ አጠቃላይና መሠረታዊ የሆኑ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩትም አመልክተዋል። የተሻለ አቅምም ለመፍጠር የህብረቶች ህብረት ለማደራጀት እንደሚያስችላቸው አስታውቀዋል። ረቂቁ ሕጉ ተጠናቅቆ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለስልጣኑ ለጽህፈት አገልግሎት የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶች በገበያ ጭማሪ ማሳየታቸውን ተከትሎ በአገልግሎት ክፍያ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች እንዳሉ አመልክተው ፤ ማሻሻያው በሚኒስትሮች ምክር የጸደቀ የክፍያ ማሻሻያ ደንብን የተከተለ ነው ብለዋል።
አዋጅ 1113/2011 መሠረት በማድረግም 12 የሚደርሱ መመሪያዎች ወጥተው ተግባር ላይ ውለዋል ብለዋል። አዋጁን ታሳቢ በማድረግ ፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶቹ ብቃትና አፈጻጸማቸው እንዲጨምር የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራታቸውንም አስታውቀዋል።
ባለስልጣኑ ሲቪል ማሕበራት የሕጉን ዓላማ ተገንዝበው እንዲሠሩ ለማስቻል ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ተግባራዊ መደረጉን ፤ ከድርጅቶቹ ጋር በትብብርና በመቀራረብ መሥራት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም አመልክተዋል።
በዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም