ትራጀዲ ቦሪስ ጎዱኖቭ የታላቁ ባለቅኔ የአሌክሳንደር ሰርጌይቪች ፑሽኪን ሥራ ነው፡፡ፑሽኪን በሰሜኑ የሩሲያ ክፍል በግዞት ላይ በነበረበት ጊዜ ‹‹የቭጌኒ ኦኔጊን›› የተሰኘ ድራማዊ ሥራውን ለማጠናቀቅ አስፋፍቶ ይጽፍ ነበር። እ.ኤ.አ በ1825 በሚሃይሎቭስክ የገጠር መንደር በነበረበት ወቅት ደግሞ ‹‹ቦሪስ ጎዱኖቭ›› የተባለ ሌላ ታሪካው ትራጀዲ ደርሶ ለኅትመት አብቅቷል።
ሁለቱም፡ድርሰቶቹ የተመሠረቱት በሪያሊዝምና በሮማንቲዝም የአጻጻፍ ዘውጎች ላይ ነው፡፡እነዚህ የአጻጻፍ መልኮች በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በሩሲያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ የታወቁ የአጻጻፍ ፈለጎች ነበሩ፡፡ ሮማንቲዝም አንዱ የሥነ ጽሑፍ መገለጫ ሁኖ የታየው በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው፡፡
የሮማንቲሲዝም ደራሲያን ብዙውን ጊዜ በዘመናቸው ዓይን ሙሉ የሚታየውን እውነታ በመተውና የፖለቲካ ውዝግብን፣ ማኅበራዊ ፍጥጫን፣ የሕዝብ ጥቅም ተጻራሪ የሆኑ ኃይሎችን ችላ በማለት የፈጠራ ሥራቸውን ይሠሩ ነበር፡፡ ከአካባቢያቸው ፖለቲካዊ ሕይወት ጋር በቅርበት የማይገናኙ ተምኔታውያንና ተቃራኒ የሆኑ ገጸ ባሕርያትን በመሣልና በአፈታሪክ ከሚታወቀውና ለዘመኑ ትውልድ ከራቀው ኋላ ቀር ዘመን ጋር እያቆራኙ ድርሰት የመጻፍ ተሠጥዖ ነበራቸው፡፡
በሮማንቲሲዝም የሥነ ጽሑፍ ዘውግ ወይንም ፈለግ ሁለት ዓይነት መንገዶች ነበሩ፡፡ አንደኛው ንቁ፣ ስሱና ተራማጅ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ኋላ ቀር ወይንም ኢሥሉጣዊ የሚባለው ነው፡፡ በሩሲያ ሥነ ጽሑፍ ብያኔ መሠረት ተራማጅ የሮማንቲሲዝም ደራሲያን የሚባሉት እንግሊዛዊው ሎረድ ባይሮን፣ ሩስያውያኑ ፑሽኪንና ሌርሞንቶቭ ናቸው።
እነዚህ እምራን ደራሲያን በድርሰቶቻቸው አብዮታዊ አስተሳሰብ ያለውን ሥሉጥ ወይንም ተራማጅ ሐሳብ በማፍለቅ ከተጨቆነው ሕዝብ ጋር በአጋነት ከመቆም አልፈው ሕዝቡ ከጨቋኝ ገዥዎችና ቀማኞች ጋር ጦርነት አካሂዶና ተዋግቶ ነጻነቱን እንዲቀናጅ ሲታገሉ ኖረዋል፡፡
ኋላ ቀር ወይንም ኢሥሉጣውያን ደራስያን የሚባሉት ደግሞ ሻቶብርያን፣ ኖቪሊስና ዡኮቭስኪ ናቸው። እነዚህ ደራስያን ማኅበረሰቡ አድጎና ተመንድጎ ወደተሻለ የኑሮ ደረጃ እንደሚያመራ አያምኑም ነበር፡፡ ስለዚህ አንባቢ ዎቻቸው ከዘመናዊ ሕይወት አስተሳሰብ ርቀው ተጨባጭ ባልሆነው የሕልም ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ፣ ወይንም የራቀውን ዘመን ብቻ በዓይነ ኅሊና ወደኋላ እያዩና በዕዝነ ልቦና እያስታወሱ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ይገፋፏቸው ነበር፡፡
ሪያሊዝም /እውነታዊነት/ የተሰኘው የሥነ ጽሑፍ ዓይነት በአሥራ ዘጠነኛውና በሃያኛው ማዕከላዊ ክፍለ ዘመን ላይ ጎልቶ ታወቀ፡፡ የእውነታዊነት /ሪያሊዝም/ ደራስያን በሣሏቸው ገጸ ባሕርያት አማካኝነት አጉልተው ማሳየት የጀመሩት በአካባቢያቸው ያለውንና የሚኖሩበትን ማኅበራዊ ሕይወት ነው፡፡ ገጸ ባሕርያቱም ተራ ሰዎችን የሚወክሉ ናቸው፡፡
በሪያሊዝም ድርሰት ገጸባሕርያት የሚኖሩበትን ጊዜና ሕይወት የሚያንጸባርቁ ናቸው፡፡ በዚህ የሥነ ጽሑፍ ዓይነት ዋነኛ ትኩረት የሚሰጠው ለማኅበራዊው፣ ለፖለቲካዊውና ኢኮኖሚያዊው፣ ባህላዊው፣ ታሪካዊው ክንዋኔ ነው፡፡በተለየ የታሪክ አጋጣሚ የተለያዩ ሀገሮች ውስጥ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ትኩረት ያደርጋል፣ ድንበር ተሻግሮ ለእውነት ይቆማል፡፡
ፍሬድሪክ ኤንግልስ ስለዚሁ የሥነጽሑፍ ባሕርይ ሲናገር ‹‹ሪያሊዝም እውነትና ፍትሕን መሠረት አድርጎ በተለያየ ሁኔታ የተለያዩ ተግባራትን በዝርዝር ለማቅረብ የሚያስችል የሥነጸሑፍ ይትበሀል ነው›› ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ ‹‹ቦሪስ ጉዱኖቭ›› እና ‹የቭጌኒ ኦኔጊን›› በሚል የተደረሱት የፑሽኪን ድርሰቶች በሩሲያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ የሪያሊዝም ዓይነተኛ ምሳሌዎች ተደርገው ይታያሉ፡፡ የሪያሊዝም ደራስያን በሥራዎቻቸው የፊውዳሊዝምንም ሆነ የካፒታሊዝምን ሥርዓት አስከፊነት በማግዘፍ ነቅፈዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ የአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሪያሊዝም ሂሳዊ /ክሪቲካዊ ሪያሊዝም/ እየተባለ ይጠራል፡፡ በሩሲያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ የሂሳዊ ሥነ ጽሑፍ መሥራች ተደርጎ የሚታየው አሌክሳንደር ፑሽኪን ነው፡፡
ትራጀዲ ቦሪስ ጎዱኖቭ የእውነታዊ ሥነ ጽሑፍ /የሪያሊዝም/ ውጤት ነው፡፡ በዚህ ሥራው ፑሽኪን በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻና በአሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረችውን ሩሲያ ያንጸባርቃል፡፡ስለ ቦሪስ ጎዱኖቭ በበለጠ ለመረዳት የሚከተለውን ታሪካዊ ክስተት ማወቅ ይጠቅማል፡፡
እ.ኤ.አ በ1584 ለሥልጣን ስስት ሲል ልጁን የገደለውና በጨካኝነቱም ኢቫን ግሩዝኒ (አረመኔው) የተባለው ንጉሠ-ነገሥቱ ኢቫን ግሮዝኒ ሲሞት ፌዎዶርና ዲሚትሪ የተባሉ ሁለት ትናንሽ ልጆች ነበሩት፡፡ ወዲያው የመጀመሪያ ልጁ ፌዎዶር በአባቱ ምትክ የሩሲያ ንጉሠ ነገሥት ተብሎ ነገሠ፡፡ ዲሚትሪ ደግሞ በወቅቱ ሕጻን ነበር፡፡ ፎዎዶር በሽተኛና ደካማ ባሕርይ ያለው ሰው ስለነበር መንግሥቱን ለመምራት ተቸገረ፡፡
ስለሆነም አጠቃላይ የሀገሪቱ ሥልጣን የፎዎዶር ሚስት ወንድም በሆነው በመስፍኑ በቦሪስ ጎዱኖቭ እጅ ገባ፡፡ ቦሪስ ብልህ፣ ሸረኛ ፤ተንኮለኛና ኃይለኛ ሰው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1591 በኡግሊቼ ከተማ የ17 ዓመቱ ልጅና ወራሴ መንግሥት የሆነው ዲሚትሪ ሞተ፡፡ ሕዝቡ ደግሞ አልጋ ወራሹ ዲሚትሪ የተገደለው በቦሪስ ጎዱኖቭ መሆኑን ስለተረዳ ውስጥ ውስጡን ማማት ጀመረ፡፡ እ.ኤ.አ በ1598 ላይ ለይስሙላ በንጉሠ ነገሥትነት የተቀመጠው ፌዎዶር ሲሞት ቦሪስ ጎዱኖቭ የሩሲ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ ነገሠ።
እ.ኤ.አ በ1605 ‹‹የዲሜትሪን ዘውድ ለመከላከልና ለመውረስ የሚገባኝ ንጉሥ እኔ ነኝ፡፡ ስሜም ንጉሠ-ነገሥት ግሪጎሪ ኦትሪፒየቭ ይባላል።›› የሚል ጦረኛና መናኝ መነኩሴ ተነሥቶ ወደ ፖላንድ ተጓዘ፡፡ የፖላንዱ ንጉሥ ደግሞ ሊረዳው ፈልጎ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ጦርሠራዊት ሰጠው፡፡ ጦረኛው መናኝ ግሪጎሪ ከፖላንድ ዋርሶው ከተማ ተነሥቶና ሠራዊቱን መርቶ ሞስኮ ከተማ ሲገባ ውጊያ ሳይካሄድ በአልተጠበቀ ሁኔታ ቦሪስ ጎዱኖቭ ሞቶ ተገኘ፡፡
መሳፍንቱና መኳንንቱ ‹‹ሕጋዊው ወራሴ መንግሥት መጣልን›› እያሉ ራሱን ንጉሠ-ነገሥት ነኝ ያለውንና ጦረኛውን መናኝ ግሪጎሪን በክብር ተቀበሉት። ወዲያው ጦረኛው መነኩሴ የቦሪስን ሚስትና ልጁንም አስገደላቸው። ራሱን ‹‹ወራሴ መንግሥት ነኝ›› ያለው ግሪጎሪ ኦትሪፒየቭ ሞስኮ እንደደረሰ የሩሲያ ንጉሠ-ነገሥት ተብሎ ነገሠ፡፡ በንግሥና ላይ የቆየው ግን ለአንድ ዓመት ብቻ ሲሆን በታሪክ ‹‹የቀዳማዊው ዛር የዲሚትሪ ወራሽ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ እናም ፑሽኪን ይህንን ትራጀዲ የጻፈው ከላይ የሠፈረውን ታሪክ መሠረት አድርጎ ነው፡፡
አሌክሳንደር ፑሽኪን በዚህ ትራጀዲያዊ ሥራው እንዳሳየው ቦሪስ የ17 ዓመቱን ልጅ ዲሚትሪን በምሥጢር ያስገደለው ወራሴ መንግሥት እንዳይሆን ስላሰበና ስለተመቀኘው ነው፡፡ ብድር በምድር አትቀርምና ቦሪስ ነግሦ ሀገር ሲያስተዳድር ሌላ ተቀናቃኝ ተነሣበት፡፡ ይኸውም መነኩሴው ግሪጎሪ ኦትሪፒየቭ ነው፡፡
ጦረኛው መናኝ በሩሲያ መነኩሴ ይነግሣል የሚለውን የቆየ ተረት እውነት አስመስሎና በንግግር መልክ የተጻፈውን ታሪክ መሠረት አድርጎ ለመንገሥ የተነሣው ልክ በእኛ ሀገር ነገሥታቱና መሣፍንቱ ከንጉሥ ሰሎሞን ዘር እንወለዳለን እያሉ ለንግሥና ሲራኮቱ እንደኖሩት ሁሉ እርሱም ከሮማኖቭ ሥርዎ መንግሥት የምወለድ እውነተኛው የሩሲያ ንጉሠ ነገሥት እኔ ነኝ ብሎ ነግሷል፡፡
ፑሽኪን ስለቦሪስ ጎዱኖቭ ሲጽፍ ‹‹ብልህ፣ ሥልጣን ወዳድ፣ እውነተኛውን የሩሲያ አልጋ ወራሽ ገድሎ ንጉሠ ነገሥት የሆነ ተንኮለኛ ሰው ነው›› ብሏል። እኩይ ተግባሩም እስከ መጨረሻ ደስታ ያጎናጸፈው መሆኑን በቦሪስ አንደበት የሚከተለውን ስንኝ የተናገረ መሆኑን እናጤናለን። ‹‹ለስድስት ዓመታት፣ በዘዴ ነግሼ ገዛሁ በጸጥታ፣መንፈሴ ግን ያዝናል የለኝም ደስታ፡፡››
ስለቦሪስ ወንጀለኛነት የሩሲያ ሕዝብ በገሐድና በሥውር፣ በሹክሹክታ ሲናገር ንጉሠ-ነገሥቱ ጎዱኖቭ ሕዝቡን ጸጥ ረጭ ለማሰኘት አልቻለም። እናም ዝም ብሎ ታሪካዊ ፍርዱን ይጠባበቅ ጀመር። ሽማግሌው መነኩሴ ስለቦሪስ ወንጀለኝነት ደፍሮ ጽሑፍ በጻፈበት ወቅት ‹‹የሩሲያ ንጉሠ-ነገሥት ነኝ ብሎ የነበረው ሌላ ሰው እንደሚነሣበት ቦሪስ ተረዳ፡፡ መነኩሴው ንጉሥ ጦሩን እየመራ ወደ ሞስኮ በተጠጋበት ወቅት ደግሞ ቦሪስ ሞቶ ተገኘ። ብሏል።
ይህ ታሪካዊ ክስተት ለፑሽኪን ጽሑፍ መነሻ ሆኖታል፡፡ በቦሪስ ጎዱኖቭ ትራጀዲ በዋናውና ወሳኙ ሚና ተዋናይ ሆኖ የሚጫወተው ሕዝብ ነው፡፡ በፑሽኪን እምነት ሕዝብ በታሪክ ውስጥ ታላቅ ኃይል ነው፡፡ በሩሲያ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚኬድበት መንገድ ኋላቀር መሆኑን አሳይቶናል፡፡ የፖለቲካው ኋላቀርነት የግፍና የመከራ አገዛዝን እንደሚያራዝም ጭምር ይጠቁመናል፡፡
ለዚህም ቦሪስ ጎዱኖቭና ግሪጎሪ ሥልጣነ መንግሥት ለመያዝ የተጠቀሙበት ዘዴ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይሆን ጉልበት ነው፡፡ ፑሽኪን ሁለቱም የየግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ ሰው እየገደሉ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ማሰባቸው ኋላቀርነታቸውን ያመለክታል፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ ሕዝብ እንደሚያሸንፍና የጉልበት ገዢዎች አወዳደቅ ትራጀዲው እንደሚሆን ፑሽኪን በብዕሩ አጉልቶ ያስረዳናል፡፡
ፑሽኪን እንደሚለው የፖለቲካ ሥልጣን ከአንድ ወንጀለኛ ወደ ሌላው ጥፋተኛ፣ ወይንም ከቦሪስ ጎዱኖቭ ወደ ጦረኛው መነኩሴ ግርጎሪ ቢተላለፍም የተጨበጠ ለውጥ ግን ሊመጣ አልቻለም፡፡ መናኙ መነኩሴው ግሪጎሪ ጦሩን ይዞ ወደ ሞስኮ ሲገባ ቦሪስ በመሞቱ ሕዝቡ እሰይ ብድር በምድር እያለ ቢናገርም ግሪጎሪ የቦሪስን ባለቤትና ልጁን ጭምር በግፍ ባስገደላቸው ጊዜ በከፍተኛ ኀዘን ተዋጠ፡፡ የሩሲያ ሕዝብ ‹‹የዛር ዲሚትሪ ኢቫኖቪችን ነፍስ ይማር፣ ዐፈሩን ገለባ ያድርግለት›› እያለ የኅሊና ጸሎት አደረሰ። በዚህም ግሪጎሪና ሕዝቡ ሆድና ጀርባ ሆኑ። ዝምታ ሰፈነ። በዝምታም አማካኝነት ሕዝቡ ለግሪጎሪ ያለውን ጥላቻና ተቃውሞ ገለጠ።
ቦሪስ ጎድኖቭ በሩሲያ ሥነጽሑፍ ታሪክ በሪያሊዝም መሠረተ ሐሳብ ላይ የተመሠረተ የመጀመሪያው ሥራ ነው፡፡ ፑሽኪን በዚህ ትራጀዲያዊ ሥራው በአሥራ ስድስተኛውና በአሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የሩሲያ ማኅበረሰብ የነበረበትን የፖለቲካና የአስተዳደር ችግር አመልክቷል፡፡ ይሄ ሥራ ከሩስያኛ የተተ ረጎመ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2011
ታደለ ገድሌ ፀጋየ ዶ/ር