
ኤች.አይ.ቪበዓለማችን መከሰቱ የታወቀው እ.ኤ.አ በሰኔ 1981 በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ በአምሥት ግብረ-ሰዶማዊያን ላይ ያልተለመደና አደገኛ የሳምባ ሕመም መከሰቱን ተከትሎ ነው። በቀጣይም በዚያው ዓመት በሐምሌ ወር ያልተለመደ ቆዳ ላይ የሚከሰት የካንሰር ህመም ወጣት ወንዶችን በኒው ዮርክና ሎሳንጀለስ ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ተከትሎ በተደረጉ ተከታታይ ጥናቶችና ክትትሎች አማካይነት ነው።
እ.ኤ.አ በ1983 ኤች.አይ.ቪ ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነትና ከደም ንክኪ በተጨማሪ ከእናት ወደ ፅንስ በእርግዝና፣ በወሊድና በጡት ማጥባት ወቅት የሚተላለፍ መሆኑን የአሜሪካ የተላላፊ በሽታዎች መቆጣጠሪያ (CDC) አሳወቀ። እ.ኤ.አ ከ1996-2002 ባለው ጊዜ ውስጥ በወቅቱ ለችግሩ ምንም መድኃኒት ካለመኖሩ ባሻገር ኤች.አይ.ቪ በከፍተኛ ማግለልና መድሎ እየታገዘ በመዛመት የዓለማችን ቁጥር አንድ የሞትና የህመም ምክንያት ሆኖ ነበር። ከዚህም የተነሳ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖችን በመደገፍ፤ ከጎናቸው የመቆምና ተባብሮ ቫይረሱን የመከላከልና መቆጣጠር አርማ በመሆን ቀዩ ሪባን እ.ኤ.አ በ1992 ይፋ ሆኖ እስከዛሬም በማገልገል ላይ ይገኛል።
በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚና ሶሻል ምክር ቤት (UN Economic and Social Council) አማካይነት ዘርፈ-ብዙ ምላሹን ለማጠናከር የተባበሩት መንግስታት የኤድስ ፕሮግራም (UNAIDS) እ.ኤ.አ በ1994 ተመስርቶ በ1996 በሙሉ አቅሙ ወደሥራ ገብቷል።
የአሜሪካ መንግሥት ኤች.አይ.ቪ ኤድስ በተለይ በአፍሪካ ሀገራት እያደረሰ የነበረውን ከፍተኛ ቀውስ በመረዳት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ እ.ኤ.አ ግንቦት 28/2003 የፕሬዚዳንቱ አስቸኳይ የኤድስ ሪሊፍ ፕላን (President’s Emergency Plan for AIDS Relief (PEPFAR) በአሜሪካ ኮንግረስ ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘቱ ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ፤ ለዓለም አቀፍ የፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምላሽ እንቅስቃሴዎችም መሰረት የጣለ ነው።
በተጨማሪም እ.ኤ.አ በ2002 የተቋቋመው ሌላው ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ምንጭ የሆነው ግሎባል ፈንድ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ መጀመሩ በሌሎች ዓለም አቀፍ ለጋሾችም ከሚደረጉ ድጋፎች ጋር ተደምሮ ዛሬ ለተገኘው ለውጥ ሚናው የጎላ ነው።
እ.ኤ.አ በ2004 የፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድኃኒቶች በአፍሪካ ባሉና በሌሎችም ሀገራት በነፃ ለመስጠት ይፋ የሆነበትና ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የተገኘ ወገኖች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በመሆን በህይወት መቆየት ብቻ ሳይሆን ወደ ቀድሞ ጤንነታቸው በመመለስ እንደማንኛውም ዜጋ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ሰዎች መሆን የሚችሉበት ተስፋ የፈነጠቀበት ጊዜ ነበር።
በኢትዮጵያ ያለውን የኤች.አይ.ቪ ታሪካዊ ዳራ ስንመለከት፣ ቫይረሱ መከሰቱ የታወቀበት ሂደት በሀገራችን እ.ኤ.አ በ1984 በሁለት የደም ናሙናዎች የተደረገ ምርመራ ኤች.አይ.ቪ እንዳላቸው በማረጋገጡ በሀገራችን መከሰቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ1986 የመጀመሪያዎቹ የኤድስ ህሙማን ሪፖርት ተደርገዋል። ይህም ኤች.አይ.ቪ በሀገራችን መከሰቱ የታወቀበት እንጂ የጀመረበት ጊዜ እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
በቀጣይም እ.ኤ.አ በ1985 ለውትድርና ለመመልመል በመጡ 5,565 ወጣቶች በተካሄደ የደም ምርመራን ያካተተ ቅኝት ከተመረመሩት 0.07 በመቶ ያህሉ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው መገኘቱ የወረርሽኙን እየተዛመተ መሄድ ያመለከተ ነበር። እንደሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ሁሉ ኤች.አይ.ቪ በማህበረሰቡ ዘንድ የእርግማን ውጤት ተደርጎ መወሰዱ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ለከፍተኛ መገለልና መድልዎ እንዲጋለጡ አስተዋፅኦ አድርጓል።
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እ.ኤ.አ በ1985 በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሀገር አቀፍ ግብረ-ኃይል የተዋቀረ ሲሆን የወረርሽኙን ሁኔታ የመከታተል፣ የትግበራ መመሪያዎችን የማዘጋጀትና ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያሉ አቅሞችንና ውስንነቶችን የማጥናት ሚና ተግባራትን ያከናውን ነበር። እ.ኤ.አ በ1987 በቡድን ደረጃ የተዋቀረው ግብረ ኃይል ወደ መምሪያ ደረጃ አድጎ የኤድስ መቆጣጠሪያ መምሪያ በሚል እንዲጠናከር ተደርጓል። በዚሁ ወቅት እ.ኤ.አ በ1987 በ23 ከተሞች በሚገኙ 6,234 ሴተኛ አዳሪዎች፤ እ.ኤ.አ በ1989 በአዲስ አበባ በሚገኙ ሴተኛ አዳሪዎች፤ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ1990 በአራት ትልልቅ ከተሞች በሚገኙ ሴተኛ አዳሪዎች በተደረጉ ጥናቶች በቅደም ተከተል 17 በመቶ፣ 16፣ 24.7 በመቶ እና 50 በመቶ በሚሆኑት ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝ መሆኑ መረጋገጡ ወረርሽኙ በጣም አሳሳቢ በሆነ ፍጥነት እየተዛመተ መምጣቱን ያመለከቱ ተጨማሪ ጥናታዊ ማስረጃዎች ነበሩ። በዚሁ አኳኋን ኤች.አይ.ቪ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ ህፃን፣ ወጣት፣ አዋቂ ብሎ ሳይለይ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በማጥቃት ከፍተኛ የጤና፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ችግር ወደመሆን ሊሸጋገር ችሎ ነበር።
ኤድስ በሀገራችን መከሰቱ ከታወቀ አንስቶ እ.ኤ.አ በ2004 የነበረው በኤድስ ምክንያት የሚከሰት የሞት መጠን ከፍተኛው ከመሆኑም በላይ የሕክምና ተቋማት በኤድስ ሕሙማን በመጣበባቸው በአገልግሎት አሰጣጥም ሆነ በጤና ዘርፍ ፋይናንስ አቅም ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ተፈጥሮ ነበር። ኤድስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትም ወላጆቻቸውን እያጡ ኤች.አይ.ቪን ጨምሮ ለበርካታ ችግሮች እንዲጋለጡ አድርጓል።
አሁን ላይ በዓለማችን እና በኢትዮጵያ በቫይረሱ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት ለመቀነስ፤ ጸረ-ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት በመደበኛነት በመውሰድ ቫይረሱን በደም ምርመራ በማይታይበት ደረጃ ማድረስ እየተቻለ ነው። እ.ኤ.አ በ2011 በተደረገ ጥናት መሰረት የፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ካለማቋረጥና በትክክል የሚወስድ ኤች.አይ.ቪ በደሙ የሚገኝ ሰው የቫይረስ መጠኑ አንድ ሺህ ሚሊ-ሊትር በታች ሲሆን ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍ ዕድሉ በከፍተኛ መጠነ የሚቀነስ መሆኑ መረጋገጡ ዓለም አቀፍ የፀረ-ኤች.አይ.ቪ ምላሹን ወደ አዲስ ምእራፍ እንዲሸጋገር አድርጓል።
እ.ኤ.አ በ2018 በተባበሩት መንግሥታት የኤድስ ፕሮግራም በተደረገ ጥናት መሰረት ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝባቸው ሰዎች በሚያደርጉት ትክክለኛ የጸረ-ኤች.አይ.ቪ ህክምና አማካይነት ቫይረሱ በምርመራ በማይገኝበት መጠን መቀነሰ የቻሉ በዚያው ልክ ቫይረሱን ወደ ሌሎች የማስተላለፍ ሁኔታን ማስቀረት መቻሉ ተገልጿል። የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ህክምናን በአግባቡ መከታተል የቫይረሱን የሥርጭት መጠን መቀነስ እንደሚያስችል ላለፉት ሃያ ዓመታት በነበሩት ተሞክሮዎች መረጋገጡን የዩ.ኤን.ኤይድ ጥናታዊ መረጃ አመልክቷል።
እ.ኤ.አ ከ2007 እስከ 2016 በተደረገ ጥናት በተቃራኒ ፆታ የግብረ- ሥጋ ግንኙነት አማካይነት የሚተላለፈው የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ከጥንዶቹ አንደኛው ቫይረሱ የሚገኝበትና በተደረገ መደበኛ ህክምና በምርመራ በማይገኝበት ደረጃ የደረሰ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ቫይረሱ በደም የማይገኝባቸው ናቸው፤ በእነዚህ በሺዎች በሚቆጠሩ ጥንዶች ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሦስት መጠነ ሰፊ ጥናቶች ተደርገዋል።
በጥናቶቹ መሰረት ቫይረሱ በደሙ የሚገኝ ሆኖ በትክክለኛ የጸረ ኤች.አይ.ቪ ህክምና ቫይረሱ በምርመራ በማይገኝበት ደረጃ መቀነስ ከቻሉት መካከል አንድም ሰው ለሌላኛው ከቫይረሱ ነፃ ለሆነ አላስተላለፈም። በዓለም አቀፍ ደረጃ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ሰዎች በሚያደርጓቸው መደበኛ ህክምና በአማካይ 47 በመቶ [35 እስከ 58 በመቶ] ሰዎች ቫይረሱን በምርመራ በማይገኝበት (ቫይራሊ ሰፕረስድ) ደረጃ አድርሰውታል። በመሆኑም ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች ጤናማ ሆነው እንዲቆዩና ከቫይረሱ ነፃ ከሆኑት ሰዎች ጋር ተመሳሳይ የእድሜ ጣሪያ እንዲኖራቸው አግዟቸዋል። በተጨማሪም የጸረ. ኤች.አይ.ቪ ህክምና በደም የሚገኘውን ቫይረስ በምርመራ በማይገኝበት ደረጃ በማድረስ ያለኮንዶም በሚደረግ ግንኙነት ቫይረሱን የማስተላለፍ መጠን በመቀነሱም ውጤታማ እየሆነ ነው።
የፀረ ኤች.አይ.ቪ ህክምና የመጀመሪያ ዓላማ፤ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ሰዎች ጤናማ ህይወት እንዲመሩ ማድረግ ነው። ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኝባቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች፣ የፀረ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ህክምና የቫይረሱን መጠን በመቀነስ ደረጃውን በጠበቀ ላቦራቶሪ አማካይነት በምርመራ በማይታይበት ደረጃ ማድረስ ያስችላቸዋል።
በትክክለኛ ምርጫ ላይ የተመሰረተ የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት፤ በደም የሚገኝ የቫይረስ መጠን በተከታታይ በርካታ ወራቶች እየቀነሰ ሄዶ በምርመራ በማይገኝበት ደረጃ ከደረሰ በኋላ የግለሰቡ ሰውነት ከበሽታ የመከላከል አቅሙ እንደገና ይታደሳል። በመሆኑም ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኝባቸው ሰዎች የሚደረገው ህክምና የተሻለ ጤናማ ህይወት እንዲመሩ ያግዛቸዋል፤ እንዲሁም በሥራ ገበታቸው ተመልሰው ሥራ መስራት የወደፊት ብሩህ ህይወታቸውንም መምራት ያስችላቸዋል።
የቫይረስ መጠን በምርመራ በማይ ታይበት ደረጃ በማድረስ ቫይረሱን የማስተላለፍ ሁኔታ ማስቀረት ለቻሉት ሰዎች ይህ መልካም ዜና ከመሆኑም ባሻገር፤ በዚህ ምክንያት ይደርስ የነበረውን አድሎና መገለልም ያስቀራል። በዚህ ሂደት ተገቢ ህክምና አድርገው ቫይረሱን ከማስተላለፍ ነፃ የሆኑ ሰዎች ከዚህ በኋላ ቫይረሱን እንደማያስተላልፉ በሚፈጠረው ግንዛቤ አማካይነት፤ የቫይረሱን ሥርጭት ከመከላከል አንፃር ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል።
ነገር ግን በጥናቱ ላይ በቀረበው መሰረት ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝባቸው ሰዎች ቫይረሱን ቀንሰው በምርመራ በማይታይበት ደረጃ ለማድረስ የሚችሉትና ቫይረሱን ወደ ሌሎች የማስተላለፍ ሁኔታን ዜሮ ላይ የሚያደርሱት የፀረ ኤች.አይ.ቪ ህክምናውን ለምን ያህል ጊዜ ከወሰዱ በኋላ እንደሆነ ተለይቶ በግልጽ አልተቀመጠም። በመሆኑም ህክምናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ሰዎች መድኃኒታቸውን ሳያቋርጡ መደበኛ ምርመራዎች ማድረግ እንዲሁም በየጊዜው የተደረሰበትን የቫይረስ መጠን ማወቅ አጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ በጥናቱ ተመክሯል።
ምንጭ:- የፌዴራል ኤች.አይ.ቪ መከላከልና መቆጣጠር ጽ/ቤት እና -UN aids.org አዲስ መን ሰኔ 9/2011አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2011