በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ዘመኑን የዋጁ ጉልበት፣ ጊዜ እና ወጪ የሚቆጥቡ፣ ይበልጥ ምርታማ የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከምንም ጊዜ በላይ እንደ አሸን እየፈሉ እንዲሁም እየተስፋፉ ናቸው፤ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (በአይሲቲ) ዘርፍ የሚሰሩ ሲሆኑ፣ በምርምርና በፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የተሰሩ ስለመሆናቸው ብዙ አስረጂዎችን መጥቀስ ይቻላል።
ቴክኖሎጂዎቹ ችግር ፈቺ፣ የሰውን ልጆች የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያቀሉ፣ ለአጠቃቀም ቀላል እና ምቹ እንዲሁም የተለያዩ አማራጮች ያላቸውም ናቸው። በዚህም ረገድ የሚሰሩ የፈጠራና የምርምር ሥራዎች እየተበራከቱ እና እያደጉ መምጣቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች በመጥቀስ፣ ሥራዎቹ እንዲስፋፉ ምቹ ምህዳር በመፍጠር የምርምርና የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ሰዎችን ማበረታትንና መደገፍን እንደሚጠይቅ ያስገነዝባሉ።
በኢትዮጵያም በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመት የልማት እቅድ የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (የአይሲቲ) ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶት ዲጅታላይዜሽን ለማስፋፋት የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው፤ ይህን ተከትሎም ለውጦች የተመዘገቡባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። የፈጠራ ሀሳብ ላላቸውና ለባለልዩ ተሰጥኦ ሰዎች ትኩረት በመስጠት ለየት ያሉ ማዕከላት በማቋቋም ለማበረታታትና ለመደገፍ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
በቅርቡም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮርያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኮይኮ /KOICA/ ጋር በመተባበር በኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ (በአይሲቲ) ዘርፍ መነሻ የንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳቦች (startups) ያላቸውን ለማበረታታት እና ለመደገፍ የሚያስችል የኢኖቬሽን ማዕከል በመገንባት አስመርቋል።
ማዕከሉ በኢትዮጵያ አይሲቲ ፓርክ የተገነባ ሲሆን፣ ‹‹ኢኖቢዝ-ኬ ኢትዮጵያ›› “Innobiz-K Ethiopia Center” የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል። ኢኖቢዝ-ኬ ኢትዮጵያ ማዕከል የቢዝነስ እና የቴክኒክ ስልጠና፣ ፕሮቶታይፖችን የማዘጋጃ ማሽኖች፤ ለመነሻ የንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳቦች (startups) ቢሮ፣ የጋራ መስሪያ ቦታ፣ የቢዝነስ ሴንተር እና የቢዝነስ ትስስር ሥራዎችን ለመስራት የሚያስችሉ ስፍራዎችን የያዘ ነው። ማዕከሉ ፈጠራን በማጎልበት፣ መነሻ የንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳቦች ያላቸውን /ስታርታፖችን/ በማብቃት እና የኢኮኖሚ እድገትን በማፋጠን ረገድ ትልቅ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ የታመነበት ነው።
የ‹‹ኢኖቢዝ-ኬ ኢትዮጵያ›› የኢኖቬሽን ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ እንዳሉት፤ የማዕከሉ መገንባት የማህበረሰብ ችግሮች የሚፈቱ ቁልፍ ሀሳቦች የሚመነጩበትንና ሊያድጉ የሚችሉበትን ስነምህዳር መፍጠርን ያለመ ነው። ማዕከሉ ፈጠራን የሚያዳብር፣ ምርምርንና ልማትን የሚያበረታታ የፈጠራ ጅምሮች እና ኢንተርፕራይዞችን እድገት የሚደግፍ ምቹ አካባቢ ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው።
በኢኖቬሽን ዘርፍ ያሉ የፈጠራ ሀሳቦች በተለየ መልኩ ጥንቃቄ ይፈልጋሉ። መነሻ የንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳቦች (startups) አስፈላጊና የተቀናጁ ድጋፎችን እንደሚፈልጉ አቶ ሰላምይሁን ይናገራሉ። ማዕከሉም መነሻ የንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳብ (startups) ያላቸውን አንድ ላይ በማሰባሰብ እርስ በርስ የሚረዳዱበትንና የሚደጋገፉበትን ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር እንደሚረዳም ይገልጻሉ። ይህ ምህዳር /ኢኮ ሲስተም/ ምቹ የሥራ ከባቢ ከመፍጠሩም ባሻገር በትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዝ ያመላክታሉ። ቀደም ሲል ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት የሥራ ከባቢዎች የሚፈጠሩት በኢንቨስተሮች፣ በዩኒቨርሲቲዎች እና በኢንዱስትሪዎች አማካኝነት መሆኑን ጠቅሰው፤ እነርሱም የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው እየተሳሰሩና እየተደጋገፉ የሚሄዱባቸው ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ያደረጉ እንደነበር አስታወሰዋል።
‹‹የዲጅታል ሲስተሙ ከሚፈልጋቸው መሠረተ ልማቶች አንዱ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን የሚያበረታቱና የሚደግፉ ማዕከላትን ማስፋፋት ነው ››ያሉት አቶ ሰላም ይሁን፤ ‹‹የዚህ ማዕከል መገንባት ብቻ በቂ አይደለም። ብዙ እንደዚህ አይነት ማዕከላትን በከተሞችና በክልሎች ማስፋፋት ያስፈልጋል። ለዚህም ገና ብዙ ሥራ መስራት ይጠበቅብናል ›› ብለዋል።
ማዕከሉ እንደ ሀገር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው፤ መነሻ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ሀሳባቸው ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እና ትልልቅ ንግዶችን እየፈጠሩ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች እውን እንዲያደርጉ ማስቻል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ማዕከሉ ኢንኩቤሽን ማዕከላት ማሟላት ያለባቸውን ሁሉንም ነገሮች አሟልቶ የያዘ ነው ያሉት አቶ ሰላም ይሁን፤ ዘመኑን የዋጁ ሥራዎችን መስራት የሚያስችሉ ማሽኖች እንዳሉትም ጠቁመዋል። በጋራ የሚሰራባቸው ምቹ የሥራ ከባቢዎች፣ ሞዴል (prototype) የሚሰራባቸው ቦታዎች እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቢሮዎች፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የሕጻናት ማቆያ እና ሌሎች መሰል ሥራዎች የሚሰራባቸው ቦታዎች ማካተቱንም አመላክተዋል።
እንደ አቶ ሰላም ይሁን ማብራሪያ፤ በማእከሉ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን በማወዳደር ብቃት ያለው ሀሳብ ያላቸው ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ በማድረግ ስልጠናና የተለያዩ ድጋፎች እንዲያገኙ ይደረጋል። የፈጠራ ሀሳብ ሲባል ዝም ብሎ ሀሳብ ያለው ሳይሆን ለየት ያለ የኢኖቬሽን ሀሳብ ያለውን የሚያመላክት ነው። ኢኖቬሽን ስንል አንድ ሀሳብ ከሀሳብነት ተነስቶ ወደ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ አስተዋጽኦ የሚሸጋገር አዲስ ሀሳብ ነው። ሀሳቡ የማይሸጋገር ከሆነ ሀሳቡ ብቁ ወይም ጊዜውን የጠበቀ አይደለም ማለት ነው።
‹‹ማንኛቸውም ሀሳብ ያላቸው ሰዎች ይወዳደራሉ። ሀሳባቸው ተወዳድሮ የሚመጥንና ብቁ ሆኖ ከተገኘ አሸንፎ ይወጣል›› የሚሉት አቶ ሰላም ይሁን፤ ሀሳባቸው አሸንፎ ወደ ማዕከሉ የሚገቡትም የሚደረግላቸው ድጋፍ በአንድ ጊዜ የሚያቆም ብቻ ሳይሆን ተከታታይነት ያለውና እያደገ የሚመጣ እንደሚሆን ያመላክታሉ። አሁን ዋናው ነገር መሆን ያለበት ስነ ምህዳሩን /ኢኮሲስተሙን/ መፍጠር መሆኑን ጠቅሰው፤ ስነ ምህዳሩ እየሰፋ በሄደ ቁጥር የሰዎች የመፍጠር አቅማቸው እየጨመረ እንደሚመጣ አመላክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ሰላም ይሁን፤ ‹‹ኢኖቬሽን ለልማት›› በሚል መሪ ሀሳብ ከኮይካ እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም/ ዩኤንዲፒ/ ጋር በመተባባር እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። የማዕከሉ ሥራ በዚህ የሚያበቃ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ለስራው ቀጣይነት በጋራ እንደሚሰራም ገልጸዋል፤ ማዕከሉ የሚያስፈልጉት የአይሲቲ መድረኮች (platforms) እንዳሉ ይጠቁማሉ። አገሪቷን የሚወክል አንዱ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ ትልቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሰላም ይሁን፤ አጠቃላይ ኢኮ ሲስተሙን የሚወክል የመረጃ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ ያለው ሥራ ሲጠናቀቅ የተሻለ ኢኮ ሲስተም እንደሚፈጠር አስረድተዋል።
የኢኖቢዝ-ኬ ኢትዮጵያ ማዕከል የሜከር ስፔስና አይሲቲ ዩኒት አስተባባሪ ወጣት ታምራት ተክለ ማርቆስ በበኩሉ ማዕከሉ የኢኖቬሽን ፈጠራ ሀሳብ ያላቸው የሥራ ፈጣሪዎች ሀሳባቸውን ወደ ንግድ ለመቀየር እንደሚረዳቸው ይናገራል።
ታምራት እንደሚለው፤ ማዕከሉ ለመነሻ የንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳቦች (startups) ሞዴል (prototype) ለመስራት የሚያግዙ ዘመናዊ ማሽኖችና ቁሳቁስ ተሟልተውለታል። የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ሀሳባቸውን ይዘው ወደ ማዕከሉ ሲመጡ ሀሳባቸውን ወደ ተግባር በመለወጥ ወደሚታይ ነገር ለመቀየር የሚጠቀሙባቸው ዘመናዊ ማሸኖችም አሉት። ዘመናዊ ማሽኖቹ የፈጠራ ሀሳባቸውን እውን የሚያደርጉበት ሞዴል (prototype) ለመስራት የሚያግዙ 3ዲ ፕሪንተሮችን ጨምሮ እጅግ ዘመናዊ ማሽኖች ተገጥመውለታል።
‹‹ ማዕከሉ የፈጠራ ሀሳብ ላላቸውና ሀሳባቸውን እውን ለማድረግ ምቹ ከባቢና ድጋፍ ላጡ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል›› ሲል ታምራት ይናገራል፤ አንድ የመነሻ የንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳብ (startups) በንድፍ ያለውን ሀሳቡን ወደሚፈልገው ተጨባጭ ነገር ለመቀየር ማሽኖች እንደሚያስፈልጉት ጠቅሶ፤ እነዚህን ማሽኖች ማግኘት ካልቻለ ግን ሀሳቡ ሀሳብ ብቻ ሆኖ ከግብ ሳይደርስ ይቀራል ይላል። እነዚህን ማሽኖች መጠቀም የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ከተፈጠሩለት በሀሳቡ ሞዴል (prototype) መስራት ይችላል ሲል ያስረዳል።
መነሻ የንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳብ (startups) ያላቸውና የማዕከሉ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ሁሉ የማእከሉን ስልጠናዎችንና የተለያዩ ድጋፎችን ያገኛሉ። ይህ ብቻ አይደለም፤ በተለይ ዘመናዊ ማሽኖች በተገጠሙለት ክፍል ውስጥ የሚሰሩት ዋንኛ ሥራ ሀሳባቸውን እውን አድርገው ወደ ንግድ ከመለወጣቸው በፊት ሀሳባቸውን በሞዴል (prototype) አውጥተው በማየት ማስተካከል ያለበት ነገር ካለ እንዲያስተካክሉ እና ሌሎችም አስተያየት እንዲሰጡበት ለማድረግ እንደሚያግዛቸው ይገልጻል። ሀሳባቸው እውን የሚሆንበት በሞዴል (prototype) ማውጣት የሚችሉበት እንደሆነ ያስረዳል።
ዘመናዊ ማሽኖቹ የፈጠራ ሀሳብ እና ሥራው ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ንግድ ተቀይሮ ለገበያ በሚውልበት ጊዜም ለመጠቀም የሚገለግሉባቸውና የሥራ እድልም ለመፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን ታምራት ይገልጻል፤ ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ግን ወደ ማዕከሉ የሚመጣ መነሻ የፈጠራ ሀሳብ (startups) ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ የፈጠራ ሀሳብ ሆኖ ተወዳድሮ አሸናፊ ሊሆን የሚችል ሀሳብ መሆን እንዳለበት አብራርቷል።
እንደ ታምራት ማብራሪያ፤ የኢኖቢዝ-ኬ ኢትዮጵያ ማዕከል ዋና ዓላማ የንግድ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ወደ ማዕከሉ ገብተው ሀሳባቸው እውን እንዲሆን ከሀሳብ ተነስተው ወደ ገበያ እስከሚገቡ ድረስ ስልጠና አግኝተው፣ የፈጠራ ሀሳቡን ወደ ሥራ እንዲቀይሩ ማስቻል ነው። ለዚህም ማዕከሉ አስፈላጊውንና ተከታታይነት ያለው ድጋፍ ያደርጋል።
እስካሁን ማዕከሉ በሙከራ ደረጃ ሀሳብ ያላቸውን በስድስት ዙር አወዳድሮ አሸናፊዎቹን ተቀብሎ ስልጠና በመስጠት እና የተለያዩ ድጋፎች በማድረግ ሀሳቦች እውን እንዲያደርጉ እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል። ሀሳቦች ነጥረው በመውጣት ለአገር ኢኮኖሚም አስተዋፆኦ የሚያበረክቱት የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ሁሉ ሀሳባቸውን ወደ ንግድ የሚቀይሩበት ሁኔታ ሲኖር መሆኑን ይገልጻሉ። ማዕከሉ የፈጠራው ባለቤቶች ሀሳባቸውን ይዘው ሲመጡ ወደ ተግባር እንዲገቡ በሁሉም ረገድ እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
‹‹ከዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ሙያዎች ተመርቀው ለተግባር ልምምድ (internship) መውጣት የሚፈልጉ ተማሪዎች ማዕከሉን መጠቀም ይችላሉ›› የሚለው ታምራት፤ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ሀሳባቸው እውን እንዲሆን የሚፈልጉ ወጣቶች በማንኛውም ጊዜ ወደ ማዕከሉ በመምጣት መስራት ይችላሉ ሲልም ጠቁሟል። ማዕከሉም ለእነዚህ አካላት ሰልጠና በመስጠት፣ ቴክኒካዊ እና የተለያዩ ድጋፎች በማድረግ አብሮ በመስራት ዓላማቸውን እንዲያሳኩ እንደሚያደርግ ገልጾ፤ ትክክለኛ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ሀሳባቸውን ይዘው ወደ ማዕከሉ ቢመጡ እነርሱም ተጠቅመው አገርም ይጠቅማሉ ሲል አስገንዝቧል።
በተለይ ኢኖቬሽን ላይ ትኩረት ያደረጉ አዳዲስ መነሻ የፈጠራ ሀሳቦች ያላቸውና ማዕከሉ የሚያወጣቸውን የመወዳደሪያ መስፈርቶች የሚያሟሉ ሁሉ መወዳዳር እንደሚችሉ ጠቅሶ፣ በመስፈርቱ መሰረት ሀሳባቸው አሸናፊ የሆነ ወደ ማዕከሉ ገብተው ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ አመልክቷል። አቶ ታምራት ሀሳብ ያላቸው አካላት እንዲወዳደሩም ጥሪ አቅርቧል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም