ጭግግ ያለ ቀን ነው። ወይ አይዘንብ ወይ አይተወው ነገር ሰማዩ እንዳኮረፈ ውሎ አድሯል። የወጣቱ ባለባጃጅ ልብም ምንነቱን ባልተገነዘበው ምክንያት ከብዷል። ሁለት ቀናት ሙሉ ቅፍፍ እንዳለው ለሥራ ወጥቶ ይገባል። ታምሚያለሁ እንዳይል ምንም ዓይነት የህመም ሰሜት የለውም። ጤነኛ ነኝ እንዳይል ደግሞ ውስጡ የሆነ የታፈነ ነገር ወጥሮ ይዞታል።
ወጣት ነው። ጥሮ ግሮ የማደግ እልህን በልቡ የሰነቀ፤ የሰነቀውን ህልም ለማሳካትም ነጋ ጠባ የሚለፋ ታታሪ ወጣት ነው። በጥረቱ የኑሮን ዳገት የወጣ ለፍቶ ባጠራቀመው ገንዘብ ባጃጅ ገዝቶ ለተሻለ ሕይወት ለማግኘት የሚተጋ ሰው ነው። የሰው ባጃጅ ቢነዳም ነገ የራሱ እንደሚኖረው ግን ምንም ጥርጥሬ አልገባውም ነበር። ተስፋና ጥረት መጨረሻው ህልምን ማሳካት ነው ብሎ ያሰባል።
ፍቃዱ ተሾመ ይባላል። ይህ ወጣት ትህትናውና ሰው አክባሪነት መለያው ነው። በሥራው ወጤታማ መሆን ሲጀመር በጃጅና መኖሪያ ቤት ለመግዛት አስቦ ሌት ከቀን እየሠራ ነበር ገንዘብ የሚያጠራቅመው። በእለቱም አምሽቶ በመሥራት ለነገ እቁብ የሚከፍለውን ገንዘብ ለመያዝ አቅዶ ተንቀሳቅሷል። አንድ ሶስት ጊዜ በኮንትራት የተለያዩ ቦታዎች ሰዎችን እያደረሰ ተመላልሷል። የመጨረሻ ያለውን ሥራ እየጠበቀ እያለ ነው ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ ሲሆን ተሳፋሪዎች ወደ ባጃጁ ተጠግተው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጉልት ከሚባለው ቦታ በመሄድ ፍቃዱ ይነዳት የነበረውን ንብረትነቱ የሌላ ግለሰብ የሆነ ባጃጅ ተኮናትረው ወደ ቆሬ እንዲወስዳቸው ተስማምተው ከኋላ በመቀመጥ ጉዞ ጀመሩ።
እነሱን አድርሶ ወደቤቱ መግባት የጓጓው ፍቃዱ ፈጥነቱን ጨምሮ ወደተባለው ቦታ ሲገሰግስ የተደገሰለትን አልጠረጠርም። ሰዎቹም የማይተዋወቁ ይመሰል በዝምታ መንገዳቸውን ቀጥለዋል። ፈቃዱም የከፈተውን ለሰላሳ ሙዚቃ እያዳመጠ መንገዱን ብቻ እያሰበ ጉዞውን ወደፊት አደረገ።
ያልታሰበው ጥቃት
ወጣቱ ነገውን ውብ ለማድረግ የሚተጋ ህልሙን ብቻ የሚያስብ በትህትና ነገሮችን የሚያልፍ በመሆኑ ሰዎች ጥቃት ይሰነዘሩብኛል ብሎ አልጠረጠረም ነበር። በሰው ንብረት መክበርን ህልማቸው ያደረጉት ተሳፋሪዎቹ ጓደኛሞች ግን ፍቃዱ እንዳሰበው ሳይሆን በዝምታ ሥራቸውን ለመሥራት እየተዘጋጁ ነበር።
ፍቃዱ ደርበውና አያልሰው ዓባይ የተባሉ ሁለት ጓደኛሞች ነበሩ። ጓደኛሞቹ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት አስበው ሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ሲሆን ባጃጅ በኃይል ለመስረቅ ተስማምተው እና ተዘጋጅተው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጉልት ከሚባለው ቦታ በመሄድ ሟች ፍቃዱ ተሾመ ይነዳት የነበረውን ንብረትነቱ የሌላ ግለሰብ የሆነ ባጃጅ ተኮናትረው ወደ ቆሬ እንዲወስዳቸው ተስማምተው ሁለቱም ተከሳሾች ከሟች ኋላ በመቀመጥ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ባቱ ኮንደሚኒየም ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ደረሱ።
አካባቢው ጨለምለም ያለ ስለነበር ልክ ጨለማው ጋ ሲደርሱ 1ኛው ተሳፋሪ በምልክት ውጋው በማለት ለ2ኛው ተሳፋሪ ሲነግረው 2ኛው ተሳፋሪም የባጃጁን ሹፌር በቢላዋ አንገቱ ላይ ወጋው። ሁለተኛው ልክ ሲወጋው 1ኛ ተሳፋሪም ራሱን እንዳይከላከል በለበሰው ልብስ አንገቱ ላይ አንቆ ሲይዘው 2ኛ ተሳፋሪ በድጋሚ ሟችን ትክሻው አካባቢ ሲወጋው ሹፌሩ ከባጃጁ ላይ ወርዶ አስፓልት ዳር ላይ ይዘረጋል። ነፍስ ይዞት በደመ ነፍስ ከባጃጁ ቢወጣም ቆሞ ማምለጥ አልሆነለትም ነበር። በወደቀበትም በጣም ብዙ ደም ፈሶት ሕይወቱ እንዲያልፍ ሆነ፡፡
ሰርቶ የማግኘትን ህልም የሰነቀው ወጣት፤ ለባጃጁ ባለቤት ከሚያስገባው ገቢ በተጨማሪ እቁብ እየጣለ ሕይወቱን ለመቀየር የሚታትረውን ወጣት፤ የማይገባቸውን ሀብት ለመንጠቅ ሲሉ ሕይወቱን አጥፍተው በድቅደቅ ጨለማ አስፓልት ላይ ጥለውት ሄዱ። ሥራውን ሰርቶ ቤቱ ለመግባት የጓጓውን የባጃጅ ሹፌር እንደ አልባሌ እቃ ከገዛ ባጃጁ ውስጥ አውጥተው ሲጥሉት ምንም አልተሰማቸውም ነበር። ይልቁኑ ከአካባቢው በፍጥነት ተሰውረው ባጃጁን የሚሸጡበትን ሁኔታ ይነጋገሩ ገቡ።
ከዛም አንደኛው ተሳፋሪ ባጃጇን እየነዳ ወደ ወልዲያ አቅጣጫ ገሰገሰ። ባጃጇንም ወደ ወሎ ወልዲያ ወስደው ለመሸጥ አስበው ጉዞ የጀመሩት ነጣቂዎች ሸዋሮቢት ላይ አንድ ሰው ጠርተው የመጀመሪያው ሰው በፔስታል ጠቅልሎ የባጃጁን ሰሌዳ አስቀምጥ ብሎ ሰጥቶት ጉዞ ጀመሩ። ሰሌዳውን የተቀበለውም ግለሰብ እቃውን አስቀምጦላቸው አብረው ወደ ወልዲያ እየሄዱ እያለ ጨፋ ሮቢት ሲደርሱ ፖሊስ ይይዛቸዋል።
ፖሊስ ባጃጇን አስቁሞ ሲፈትሽ ሟችን የወጉበት ቢላዋ የተገኘ በመሆኑ ሰዎቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ይጀምራል። ሰዎቹ ባጃጁ ውስጥ ስለተገኘው ቢላ የማያውቁ መሆኑንና ሌላ ሰው ለተንኮል አስቀምጦባቸው ሊሆን እንደሚችል ቢናገሩም እየነዱ ያሉት ታርጋ ከየት እንደመጣች በመጠየቅ ሰዎቹም ንፁህ ይሁኑ ወንጀለኛ ለማረጋገጥ በአካባቢው ወደሚገኝ ማረፊያ ቤት ይወስዳቸዋል፡፡
የፖሊስ ምርመራ
በምርመራ ወቅትም ፍቃዱ ደርበው የተባለው 1ኛ ተከሳሽ ባጃጇን እየነዳ ወደ ወልዲያ ወስደው ለመሸጥ አስበው ሸዋሮቢት ላይ አንደኛውን የዐቃቤ ሕግ ምስክር ጠርተው 1ኛ ተከሳሽ በፔስታል ጠቅልሎ የባጃጁን ሰሌዳ አስቀምጥ ብሎ ሰጥቶት ምስክሩም ሰሌዳውን አስቀምጦላቸው አብረው ወደ ወልዲያ እየሄዱ እያለ ጨፋ ሮቢት ሲደርሱ ፖሊስ ይዟቸው ፖሊስ ባጃጇን ሲፈትሽ ሟችን የወጉበት ቢላዋ የተገኘ በመሆኑ በፈፀሙት ወንጀል በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 671/2/ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ክስ ሊቀርብባቸው እንደሚገባ ማስረጃውን አጠናክሮ ለዐቃቤ ሕግ ይልካል።
ፖሊስ እንደሚለው ታርጋው ከተደበቀበት እስከሚወጣ ድረስ ተከሳሾቹ ወንጀሉን መፈፀማቸውን ያላመኑ ሲሁን ይህም ምርመራው እንዲጓተት አድርጎት የነበር መሆኑን ያስረዳሉ። በስተመጨረሻም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በጥምረት በመሠራቱ የተነሳ የተሰረቀ ባጃጅ መኖሩን የባጃጁ ሹፌር መሞቱን መረጃ በማግኘታቸው ምርመራው ተጠናክሮ ቀጠለ።
በስተመጨረሻም የፎረንሲክ ምርመራም፤ የእምነት ክህደት ቃሉንና ሌሎች የቴክኒክና የታክቲክ ምርመራው ተጠናቅሮ ለዐቃቤ ሕግ ቀረበ።
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር
በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ ፍቃዱ ደርበው፣ 2ኛ አያልሰው ዓባይ፣ የተባሉ ሁለት ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት አስበው ሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ሲሆን ባጃጅ በኃይል ለመስረቅ ተስማምተው እና ተዘጋጅተው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጉልት ከሚባለው ቦታ በመሄድ ሟች ፍቃዱ ተሾመ ይነዳት የነበረውን ንብረትነቱ የሌላ ግለሰብ የሆነ ባጃጅ ተኮናትረው ወደ ቆሬ እንዲወስዳቸው ተስማምተው ሁለቱም ተከሳሾች ከሟች ኋላ በመቀመጥ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 02 ባቱ ኮንዶሚኒየም ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ 1ኛ ተከሳሽ በምልክት ውጋው በማለት ለ2ኛ ተከሳሽ ሲነግረው 2ኛ ተከሳሽም ሟችን በቢላዋ አንገቱ ላይ ሲወጋው 1ኛ ተከሳሽም ራሱን እንዳይከላከል በለበሰው ልብስ አንገቱ ላይ አንቆ ሲይዘው 2ኛ ተከሳሽ በድጋሚ ሟችን ትክሻው አካባቢ ሲወጋው ሟች ከባጃጁ ላይ ወርዶ አስፓልት ዳር ወድቆ ብዙ ደም ፈሶት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርገዋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ ባጃጇን እየነዳ ወደ ወልዲያ ወስደው ለመሸጥ አስበው ሸዋሮቢት ላይ አንደኛውን የዐቃቤ ሕግ ምስክር ጠርተው 1ኛ ተከሳሽ በፔስታል ጠቅልሎ የባጃጁን ሰሌዳ አስቀምጥ ብሎ ሰጥቶት ምስክሩም ሰሌዳውን አስቀምጦላቸው አብረው ወደ ወልዲያ እየሄዱ እያለ ጨፋ ሮቢት ሲደርሱ ፖሊስ ይዟቸው ፖሊስ ባጃጇን ሲፈትሽ ሟችን የወጉበት ቢላዋ የተገኘ በመሆኑ በፈፀሙት ወንጀል በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 671/2/ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ክስ ቀርቦባቸው ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በክርክሩም ሂደት የተለያዩ ቀነ ቀጠሮዎች እየተሰጠ ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ሲሰማ ቆይቶ ብይን የሚሰጥበትን ቀን ቆረጠ።
ውሳኔ
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷቸው ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ።
በተላለፈው ውሳኔ መሠረትም ሁለቱም ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት አስበው ወንጀሉን በመፈፀማቸው በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም