ጠቢባን እንዲህ ይመክራሉ፡፡ ዓለም በየትኛው መንገድ ስትጠራህ ቀድመህ አቤት በል፡፡ በዝምታ ብቻ ተውጠህ ችግሮችን መወጣት አለያም የደስታ ድርብርቦሽን ማጣጣም አትችልም፡፡ በዓለም ውስጥ ሳለህ ተንቀሳቀስ፤ ጠይቅ፤ በሌሎች ስትጠየቅ ደግሞ ምላሽ ስጥ፡፡ የመውጫህ አንዱ በር ሲዘጋ ሌላኛው በር ክፍት ሆኖ ሊጠብቅህ እንደሚችል ገምት፡፡ በግምት ብቻ ሳትቀር ሌላ መውጫ በር መኖሩን ተመልከት፡፡
በሩ ባይመችህም በመስኮቱ ሾልከህ ውጣ። አንዷ ቀዳዳ ስትደፈን ሚሊዮን ቀዳዳዎች በዙሪያህ መኖራቸውን ተመልከት፡፡ ሁሉም በውስጥህ የምትመኘውን ነገር ከልጅነቴ ጀምሮ አልተለማመድኩም፤ አልተማርኩትም አሊያም ደግሞ አብሬው አልኖርኩም አትበል። ዛሬ አንድ ብለህ ስትጀምር ትናንት ታሪክ ይሆንና ነገ እውነት ይሆናል፤ ዛሬ ደግሞ ትዝታን ያዘለ ሕይወት ማንፀሪያ ይሆናል፡፡
በትምህርትህ ስላልተሳካልህ፤ የስኬት መንገዶች ሁሉ የተዘጉ አይምሰልህ፡፡ በንግድ ዛሬ አልተሳካልህም ማለት ነገ ሲራራ ነጋዴ ሆነ ዓለም ላይ አንቱ ከተባሉ ቱጃሮች ተርታ ላለመሰለፍህ እርግጠኛ አትሁን፡፡ ጀንበር ስለጠለቀችና ብርሃን ለጨለማ ስፍራውን ስለለቀቀ፤ ፀሐይ በጭለማ ብርታት የተሸነፈች አይምሰልህ፡፡ ይልቁንም የህይወትን ዑደትና ፍርቅርቆሽ እልቆቢስ ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ተገንዘብ፡፡
ይህን ድራር አቦሆይ ተግብሮታል። ህይወት ላይ ታች እያለች ዥዋዥዌ ስትጫ ወትብህ ገመዱን ጠበቅ አድርገህ ተደሰት እንጂ አትከፋ፡፡ ሕይወት ወደ ቆላ ስታቆለቁልህ ደጋ መውጣት እንደምትችል በተግባር አሳያት። በድህነት አረንቋ ውስጥ ስትወረውርህ ማምለጥ እንደምትችል አሳያት፡፡
ህይወትን ተለማመዳት እንጂ አትለማመጣት፡፡ በአንድ ቀን አትሰልች፡ ፡ ልክ እንደ ድራር ክርር ብለህ ብርታትህን አሳይ፡፡ ኑሮ ተሸክማህ እንደ እንገዋላይ ከላይ ገውለል! ገውለል! አድርጋ ከቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ እንዳታስቀምጥህ አንተ ጨክነህ ዓላማህን አሳካው፡፡ ዛሬ በ‹‹እንዲህም ይኖራል›› አምዳችሁ ከትግራይ ክልል ሽረ አካባቢ ተወልዶ በልፋቱ ስሙ በዓለም የናኘ እንዲሆን ስለሚተጋው ብርቱ ወጣት ሕይወት ተሞክሮ ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡
ድራር አቦሆይ በ1978 ዓ.ም በትግራይ ክልል ከሽረ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኝ ዓዲዳዕሮ የምትባል ወረዳ ነው የተወለደው፡፡ ቤተሰቦቹ አርሶ አደር ናቸው። እርሱም እነርሱን እያገዘ ነው ያደገው።1999 ዓ.ም 10ኛ ክፍል ተፈትኖ ከዚያ ውጭ አልገፋበትም፡፡ ተማሪ ሳለ 50 ሳንቲም እየከፈለ ፊልም ይመለከት ነበር፡፡ በተለይ የቻይና እና ህንድ ፊልሞችን ሲመለከት ከፍተኛ የአካል እንቅስቃሴ ያይበት ነበር። ብዙዎቹ በቴክኖሎጂ ታግዘው የተከወኑ ስለመሆናቸውም አይገነዘብም ነበር፡፡ እናም ያየውን ሁሉ ይተገብር ጀመረ፡፡
ወደ ጫካ እየሄደ ልምምድ ያደርግ ጀመር፡፡ በመሰል ስፖርት ላይ የተፃፈ መፅሐፍ እያነበበ ስፖርቱን ይሰራል እንጂ፤ በምክርም ሆነ በጤና በኩል የሚያግዘው አልነበረም፡፡ እስከ 2000 ዓ.ም ይህን ሲለማመድ ነበር፡፡ ስፖርቱን ‹‹ግዕዝ›› ብሎ ሲጀምረው ቢያንስ እንኳን በክልል ደረጃ ለበርካቶች አለኝታ እና መከታ ብሎም አርዓያ መሆን አለብኝ ከሚል እሳቤ እንጂ በዓለም አደባባይ ለመወዳደር ከማሰብ አልነበረም፡፡
ድራር ገና ልጅ ሆኖ ችሎታውን ለማሳደግ ብዙ ከመልፋት በዘለለ ሰዎች እንዲመለከቱ ጥረቶችን ያደርግ ነበር፡፡ በአካባቢው የዓመቱ ትምህርት ሲጠናቀቅና ሰኔ 30 አካባቢ የወላጆች በዓል ሲከበር የሰለጠኑ የሰርከስ ቡድን ስብስቦች ሥራቸውን ሲያቀርቡ እርሱም የራሱን ሥራ በግሉ ያቀርብ ነበር፡፡ በእጁ እስከ 50 ሜትር ይሄድና ተመልካቾችን ያዝናናል፡፡ በሂደት እስከ 100 ሜትርም በእጁ መሄድ ብሎም ከፍታ ቦታ መውጣትና መውረድ ጀመረ፡፡
ግንድ ላይ ወገቡንም ያስርና ተዘቅዝቆ ፑሽአፕ ይሰራል፡፡ መደበኛ ፑሽአፕም ይሠራል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በሁለት ሰዓት ውስጥ 10ሺ500 ፑሽአፕ ይሰራል፡፡ ከእነዚህ ልምዶች እና ውጤት በመነሳት ችሎታውን ሰፋ አድርጎ ማሳየቱን ተያያዘው፡፡ ከፍተኛ ክብደትን መሸከም፤ መጎተት እና መሳሳብ ሥራዬ ብሎ የሕይወቱ መሰረት አደረገው፡፡ በልምምድ ብዛት እጅ አፍ ላይ የሚያስጭኑ ትዕይንቶችን ይከውን ጀመረ-ድራር፡፡
በአሁኑ ወቅት በዱባይ ትልቁ ህንፃ ‹‹ቡርጂ ከሊፋ›› ያለማቋረጥ በእጁ ለመው ጣትና ለመውረድ ለመሄድ እየተዘጋጀ ነው። ይህ ህንፃ በዱባይ ውስጥ ቁመቱ ትልቁ ሲሆን 828 ሜትር የሚረዝም ነው፤ 200 ወለሎች አሉት፡፡ ታዲያ ይህንን ጀብድ ለመፈጸም አንድ ሰዓት ተኩል ይበቃኛል እያለ ነው፡፡ አሁን ለጉዞ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ 24 የዝግጅት ቀናትም ይቀሩታል፡፡
በመሰል ጀብድ አንድ ቻይናዊ 808 ሜትር በመውጣት የዓለምክብረ ወሰንን የያዘ ሲሆን፤ ድራር ግን በሰባት ሜትር አሻሽሎ ክብሩን በእጁ ሊያስገባ እያሰበ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሽረ ከተማ እና አካባቢው የሽኝትና ማነቃቂያ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው የሚናገረው። በዚህ ሥራው የተደመሙ አንዳንድ ሰዎች እስከ 10ሺ ብር ሸልመውታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዓዲዳዕሮ ከቤተሰቡ ጋር ነው የሚኖረው፡፡ ይህ ወጣት በሳምንት ሰባቱን ቀን እረፍት የለኝም ይላል፡፡ ከቀናቶቹ አንድም ቀን እንዲሁ በከንቱ የሚባክን ደቂቃ የለም፡፡ በደቂቃዎችና ሰዓታት ተከፋፍላ ጥቅም ላይ ትውላለች፡፡ አንድ ቀን መሳብ አንድ ቀን ደግሞ ማሳሳብ፤ አንድ ቀን መገልበጥ ሌላ ቀን መገለባበጥ እያለ ስፖርት ይሰራል፡፡
በሌላኛው ቀን መለጠጥ በቀጣዩ ቀን ደግሞ መሳብ መዝለል በአንዱ ቀን መሸከም በሌላው ቀን ደግሞ ከሸክም ነፃ የሆነ እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ ብቻ ያለዕረፍት ሰውነት መተጣጠፍና ጅምናስቲክ፣ የወገብ እና ሌሎች መገጣጠሚያዎችን ማሳሳብ፣ መሸከም፣ አንገት እንቅስቃሴ እና የመሳሰሉ ሥራዎች ያከናውናል፡፡ ይህም በሥራው ስኬታማ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ሰውነቱን በሰባቱም ቀናት ውስጥ በብዙ መንገድ ያዘዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ 62 ኪሎ ግራም ነው፤ የመጨመር ፍላጎትም የለውም፡፡ በመደበኛው ሳይንስ ስድስት ዓይነት ፑሽአፕ ዓይነቶች ቢኖሩም ድራር በልምድ ብዛት ወደ 16 ከፍ አድርጓል። እስካሁን ልምምድ ሲያደርግ የከፋ ጉዳት አልደረሰብኝም፤ ይህም በፈጣሪ ጥበቃ የሆነ ነው ይላል፡፡
ይህ አይታክቴ ሰው በአመጋገቡ ብዙም የተለየ አይደለም፡፡ በሶ ይጠቀማል፡፡ ሁሌም ዳቦ ይመገባል፡፡ ጭብጦ እና ቂጣ ያዘወትራል። ጭማቂና ውጤቶቹን ይጠቀማል፡፡ ብዙ ጊዜ ቂጣ ነው የሚበላው፡፡ አልኮል ባለበት ስፍራ ዞር ብሎ አያውቅም፡፡ ከውሃ ውጭ ወይ ፍንክች የሚል ሰው ነው፡፡ ውሃ፣ ውሃ፣ ውሃ፣ ውሃ በቃ ውሃ ብቻ! ሌሎች መጠጦችን አይደፍርም፤ አይፈልግም አያስብም፡፡ ግን ፈሳሽ ከተባለ ጁስ ይጠቀማል፡፡
ድራር 62 ኪሎ ግራም ቢመዝንም ከእርሱ በአምስትና ስድስት እጥፍ የሚበልጡ ክብደቶችን ይሸከማል፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ብርታቱን ከፍ አድርጎት አሁን ከሚሸከማቸው እና ከሚያከናውናቸው እንቅስቃሴዎች በላይ በመከወን ዓለምን ዓጃኢብ ለማስባል ይፈልጋል፤ ይህም እንደሚሆን እምነቱም ሆነ ብቃቱ አለኝ ይላል፡፡
ይህን ችሎታውን በአድናቆት ብቻ የተገደበ እንዲሆን አልፈለገም፡፡ የጉዞው መዳረሻ የድንቃድንቆች መዝገብ ጊነስ ቡክ ላይ ስሙን ማስፈር ነው፡፡ ድራር በዓለም ህዝብ ልብ እና አዕምሮ ውስጥ ሥፍራ ይኖረው ዘንድ ትልቅ መሻት አለው፡፡ እርሱ ይህን ሁሉ ጥረት እያደረገ፤ እንዲሁ ጎበዝ ልጅ ነበር፤ ምርጥ ስፖርተኛ ነው የሚሉ የአፍ መደለያዎችንና ሙገሳዎችን ብቻ ሰምቶ መቀመጥ አያስብም፡፡ በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ለዚያም በተለየ ሁኔታ ስሙ እንዲሰፍር ይፈልጋል፡፡ ባለ ብዙ ተሰጥዖ፤ ባለ ብዙ ሪኮርድ ሰው ለመባልም እየሰራ ነው። ለዚህም በልምምድ ወቅት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡
ሰው በአንድ ወቅት ገርሞት አጨብጭቦ እንዲሄድ ብቻ ሳይሆን ሁሌም በድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሙን ሊያሰፍር የሚያስችል ሥራ እየሰራ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ሰው በአድናቆት ብቻ ሊያቆም አልፈለገም፡፡ ከፊቱ ብዙ ነገር እንደሚጠብቀው ይገምታል። ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በርካቶች እርሱ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ለማስፈር ጥረት እያደረገ መሆኑን በመስማታቸው ከፍተኛ የማስተዋወቅና የማነቃቃት ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡
የአገሩን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ ለማስጠራት በእጅጉ እየለፋ ነው፡፡ ለራሱም ስመጥር ስፖርተኛ ሆኖ በቻይናዊው ስም የተያዘውን የድንቃ ድንቅ ክብር ሰብሮ የኢትዮጵያ ስም በስፍራው በደማቅ ቀለም እንዲከተብ እየተጋ ነው፡፡ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ከቻይናዊው ዜጋ ላይ ነቅለው ደጋግመው ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ብለው እንዲዘግቡ ይመኛል፡፡
ለዚህም የመንግሥት አካላት እና ሚዲያ ያልነጠፈ እገዛን ይፈልጋል። ታዲያ ለዚህ ጥረቱና ፍላጎቱ መንግሥትና የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ድጋፍ እንዲያ ደርጉለት ይጠይቃል፡፡ ከማንኛም አካል በላይ በተለያዩ አገራት የመንቀሳቀስ ፍላጎትና እቅድ ስላለው በየአገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች አሊያም ቆንስላዎች ተገቢውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉለት በእጅጉ ይሻል፡፡ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አጅበውት በኢትዮጵያዊ ባህል፤ በጀግና አነጋገር በርታ እንዲሉት አጥብቆ ይጠይቃል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም ለሌሎች ስፖርቶች የሚሰጡትን ሽፋን ለመሰል ስፖርቶች እንዲሰ ጡትና እንግዳ እንዲያደርጉ፣ በሙያው ላይ እውቀትና ልምድ ያላቸው አካላት ምክርና ሙያዊ እገዛ እንዲጨምሩለት ዕድል እንዲሰጥና ስኬት አመላካች ዘገባ ዎችን ቢሠሩ ይመኛል። በተቻለ መጠን አገሩን ለማስተዋወቅ በሚያደርገው ጥረት ሚዲያዎችም የራሳቸውን ሚና ቢወጡ ደስተኛ ነው። እንደሚሆንም ተስፋ ያደርጋል፤ ክንደ ብርቱ ድራር፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም ስኬትህን ከልቡ እየተመኝ፤ በሚዲያ በኩል የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት እነሆ ብሏል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር