ስለነገው – ዛሬን በተስፋ

እንደመነሻ…

የዳውሮው ተወላጅ በራና በላንጎ ብርቱ ጎልማሳ ነው። ቤት ትዳሩን ለማጽናት አይሰራው፣ አይሞክረው የለም። ሚስቱን አክባሪ ልጆቹን ወዳድ ነውና ሌት ተቀን በሥራ መትጋት ብርቁ ሆኖ አያውቅም ፡፡

በራና ግዜው በጋ ሲሆን እጆቹ ባለሙያ ናቸው። አናጺ፣ ሆኖ ቤት ይገነባል። በሩን ጣራ መስኮቱን ይገጥማል። ግንበኝነትም አቅቶት አያውቅም። በየተፈለገበት ቦታ ተገኝቶ በወጉ ትዕዛዝ ይፈጽማል። ክረምት ደርሶ ዝናብ ሲጥል መሬት ሲርስ ደግሞ በራና አራሽ ገበሬ ይሆናል። አፈሩን እየፈነቀለ ዘር ይበትናል። አዝመራው ሲይዝ እሸቱ ሲደርስም የላብ የድካሙን አያጣም። አትክልት ፍራፍሬው፣ የጓሮው ጸጋ ናቸው። ብስል ከጥሬ እየቆረጠ ለገበያ በስፋት ያቀርባል።

እጀ ሰፊው ጎልማሳ ቤቱ ሙሉና ሰላም እንደሆነ ዓመቱን ይጨርሳል። የእሱ ምኞት ሁሌም ቤተሰቡን አጥግቦ እፎይታ ማግኘት ነው። ለዚህ ስኬታማ የሆነው በራና ለሆነለት ሁሉ ፈጣሪውን አይዘነጋም። ሁሌም እጆቹን ዘርግቶ ‹‹ተመስገን›› እያለ በምስጋና ይታትራል፡፡

ከአስራ አንድ ዓመት በፊት…

በራና ልጆች የእግዚአብሔር ጸጋ መሆናቸውን አሳምሮ ያውቃል። ለእሱ በተሰጠው ጸጋና በረከትም ደስተኛ እንደሆነ ዓመታትን ዘልቋል። በቅርቡ ደግሞ ባለቤቱ መንታ ሴት ልጆችን ወልዳ አሳቅፋዋለች። በራና ዳግም ባገኘው በረከት በልዩ ደስታ ተውጧል። ሁለቱ መንታ ልጆች በመልክ አንድ ናቸው። አንዷ ስትስቅ ሌላዋ ትከታላለች። የአንዷ ሕመም ደግሞ ለሌዋ ትኩሳቷ ነው፡፡

ይህ አይነቱ ባሕርይ የመንታ ልጆች ልማድ መሆኑን ቤተሰቡ ያውቃል። በዚህ ቤትም ሁለቱን መንታዎች እንደ አንድ አስማምተው እያሳደጉ ነው። በሀገሬው ወግ ልማድ በጾታ የማይመሳሰሉ መንታዎች ሲወለዱ ስማቸውን ከአንድ ቃል መዋስ ተለምዷል። ወንዱ ‹‹አበበ ››ተብሎ ቢሰየም፣ ሴቷን ደግሞ ‹‹አበበች›› ሲሉ ይጠሯታል።

በእነ በራና ቤተሰብ የተወለዱት መንታዎች ግን ጾታቸው አንድ አይነት ነው። እንዲህ መሆኑ መጠሪያቸውን ሊለያየው ግድ ብሏል። ‹‹መቅደስና ምርት ዓለም፣›› የሚል ስያሜ የተቸራቸው ሕጻናት ስማቸውን ይዘው ማደግ ጀምረዋል። መጠሪያቸው ቢለያይም ባሕርያችው አልተለወጠም። ሁሌም ውሏቸው በተመሳስሎ እንደተዋበ ይገለጻል።

ሁለቱ መንታዎች ዕድሜያቸው ከፍ ሲል ትምህርትቤት ገብተው ቀለም መቁጠር ጀመሩ ። የልብሳቸው አንድ መሆን ከመልካቸው ተዳምሮ ያያቸውን ሁሉ ያስገርም ይዟል። ቀረብ ላላቸው ደግሞ ባሕሪያቸው አይለያይም። ሁለቱም በአንድ አይነት ማንነት ይገለጣሉ። እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው ውለው ይገባሉ፡፡

ሁለቱ ውብ ልጆች ሁሌም ዓይን እንደሳቡ ነው። ያያቸው ሁሉ ይገረማል። የቀረቧቸው አንዳንዶችም እጅና ግንባራቸውን እየሳሙ ‹‹እደጉ፣ ተመንደጉ›› ይሏቸዋል። ምርትዓለምና መቅደስ ልጅነታቸው በደስታ ተጀምሯል። ከተማሪዎች መሀል በአንድ አይነት መልካቸው ከሩቁ ይለያሉ።

ድንገቴው ጥያቄ…

ከቀናት በአንዱ ለበራናና ባለቤቱ የደረሰው ድንገቴ ጥያቄ መልስ ሊያሻው ግድ ሆነ። ሁኔታው እንደ ወላጅ ቢያስጨንቅም ጥንዶቹ ‹‹እሺ ይሁን›› ከማለት ውጭ ምርጫ አጥተዋል። ለበራና ሚስት ታላቅ እህት የሆነችው ወይዘሮ ምርትዓለምን እንደ ልጅ እንድታሳድጋት ጠይቃለች። ይህ እውነት ባልና ሚስቱን በእምቢታ ሊያስከለክል አልቻለም። ጥንዶቹ ሌሎች ልጆችም አሏቸው። የምርታዓለም መንትያ መቅደስም ከእነሱ ጋር ነች፡፡

ውሳኔው…

ባልና ሚስቱ ሁሉን ቡረዱ ምንም ለሌላት ወይዘሮ ልጃቸውን ሊሰጡ ተስማሙ። ያለአንዳች ቅሬታም ‹‹ልጃችን ልጅሽ›› ትሁን ሲሉ በፍቅር አሳቀፏት። አሁን መንትያዎቹ እህትማማች ሊለያዩ ግድ ሆኗል። ከቀናት በኋላ ምርትዓለም ከመቅደስ ተነጥላ አክስቷ ወዳለችበት ወደ ወላይታ አመራች። በዚህ ከተማ ለእሷ ዕድሜ የሚመጥኑ ምቹ ሁኔታዎች አልጠፉም። በአክስቷ ቤት እየኖረች ትምህርቷን ትቀጥላለች፡፡

ከግዚያት በኋላ ትንሽዬዋ ምርትዓለም የአክስቷ ብቸኛ ልጅ ሆነች። የጎደለው ሞልቶ የታሰበው ሁሉ ተፈጸመላት። አዲስ ልብስና ጫማ ተገዝቶላት ትምህርትቤት ገባች። ከመንትያ እህቷ መነጠሏ ቢያጎድላትም ሕይወት አልበደለቻትም። እንደ ልጅ የተቀበለቻት አክስቷ መልካም እናት ሆነችላት፡፡

ምርትዓለም አሁን ትምህርትቤት ገብታለች። በዚህ ሥፍራ አዲስ ባልንጀሮች አሏት። አንዳንዴ እህቷን ስታስታውስ ትናፍቃታለች። አንድ አይነት ልብስና ጫማቸው፣ ተመሳሳይ ሕመምና ሳቃቸው ሁሉ ለእሷ ትዝታዋ ነው። እንዲያም ሆኖ የእናቷ እህት አክስቷ የጎዶሎዋ ሙላት ሆናለች። ፍቅር እየሰጠች፣ ተንከባክባ ማሳደጓን አልተወችም፡፡

እነ በራና ዳውሮ ላይ የነበራቸው ሕይወት እንደ ቀድሞው ቀጥሏል። አንደኛዋ ልጅ ከዓይናቸው ብትርቅም ሁሌም ድምፅዋን ይሰማሉ። አሁን ምርትዓለም የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ነገ አድጋ በዕውቀት ስትልቅ ሀገር ወገንን ትጠቅማለች። ይህ ይሆን ዘንድ የአሳዳጊ እናቷ ተስፋ ከእሷ አይርቅም።

ከቀናት በአንዱ…

አንድቀን ምርትዓለም ከትምህርት ውላ ቤት ስትገባ ያልተለመደ ጭንቀት ታየባት። እየደጋጋመ ቀኝ ጎኗን የሚወጋት ሕመም ስሜቱ ከፍ እያለ ነው። ሁኔታዋ ያሳሰባት አክስት ቀረብ ብላ ችግሯን ለማወቅ ሞከረች። ትንሽዋ ልጅ እጇን ከጎኗ አስቀምጣ ደጋግማ እያቃሰተች ነው። ይህ ችግር ከዚህ ቀድሞ ታይቶባት አያውቅም። ይህ የገባት ወይዘሮ ተዘናግታ ዝም አላለችም። የአደራ ልጇ ጭንቀት ቢጋባባት ሀኪም ዘንድ ልትወስዳት ፈጠነች፡፡

በሆስፒታሉ….

ሆስፒታል አድርሳ ማሳከም የጀመረችው አክስት ችግሩ የኩላሊት ኢንፌክሽን መሆኑ ተነግሯታል። ከቀናት በኋላ ግን በልጅቷ ላይ ሌላ ምልክት አስተዋለች። ይብራዓለም ከሽንቷ ጋር ተቀላቅሎ የሚወጣው ደም አስደንጋጭ የሚባል ነው። ይህ ምልክት ያልተለመደ ነውና አሳሳቢ መሆኑ አልቀረም። ጉዳዩን ፈጥና ለቤተሰቦቿ ማሳወቅ ነበረባት።

ይህን አስደንጋጭ እውነት የሰሙ የልጅቷ ወላጆች ፈጥነው ካለችበት ደረሱ። ፋታ የማይሰጠው ሕመም አሁንም ምርት ዓለምን እያስጨነቃት ነው። ችግሩ በዚህ ብቻ አልቆመም። ሕመም የከረመበት አንድ ጎኗ እያደር እብጠቱ ጨመረ። ወላይታ ከሚገኝ አንድ ሆስፒታል ሕክምና የጀመረችው ሕጻን አልጋ ይዛ ለቀናት መድሀኒት መውሰድ ጀመረች። ጥቂት ቆይቶ ግን ከሀኪሞች ሌላ ትዕዛዝ መጣ። የልጅቷ ሕመም ከፍ ያለ በመሆኑ ከፍተኛ ሕክምና እንደሚያስፈልጋት ታወቀ።

እንዴት…

ወላጆች ስለ ጉዳዩ ምንነት እንዴት ማለታቸው አልቀረም። በአንድ ኩላሊቷ ላይ የሚታየው ዕጢ ለጤናዋ አስጊ መሆኑ ተነግሯቸዋል። ይህን ውጤት ተከትሎ የሰሙት ሌላ ዜና ደግሞ ለመላው ቤተሰብ አስደንጋጭ የሚባል ሆነ፡፡

በትንሽዋ ልጅ ኩላሊት የተስተዋለው ዕጢ ጥቂት ከቆየ ውጤቱ የከፋ ሊሆን ይችላል። ፈጥና ሕከምና ካላገኘችም ችግሩ ተባብሶ ወደ ‹‹ካንሰር›› የመለወጥ ዕድሉ ሰፊ ነው። በአካባቢው ስለ ካንሰር አስከፊነት አብዛኞች ያውቃሉ። በእነሱ አጋጣሚ በዚህ ችግር ያለፈ ታማሚ ጡትን ጨምሮ እጅና እግርን አልያም ሌላው አካል ተቆርጦ እንደሚወገድ ሰምተዋል። ብዙ ግዜም መጨረሻው በሞት እንደሚቋጭ ጠይቀው ተረድተዋል። ይህን ሀቅ ጠንቅቀው የሚያውቁት ወላጆች ስለ ልጃቸው ጤና ሲባል ለአንዲት ቀን ማደር አልፈለጉም። የተሰጣቸውን የሕክምና ውጤት በጥንቃቄ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ተዘጋጁ፡፡

አዲስ አበባ …

‹‹ለሀገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ›› የሆነው አባት በራና አሁን ልጁን ይዞ አዲስ አበባ ገብቷል። በዚህ ቦታ ‹‹የእኔ›› ይለው የቅርብ ዘመድ የለም። እንዲያም ሆኖ ይህ ሀሳብ ሆኖ አላስጨነቀውም። ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደደረሰ ግዜ ሳይፈጅ አስቸኳዩን የምርመራ ሂደት አስጀመረ። ምርት ዓለም ከዕለት ዕለት ሕመሟ እየባሰ እደከመች ነው። ይህ ምልክት በራናን ክፉኛ አስጨንቆታል። ቀድሞ ከነበረበት ሆስፒታል የልጁ ትንፋሽ የረዘመው በተሰጣት መድሀኒቶች ነበር። በዚህ ሥፍራ ደግሞ አሁንም ለተጨማሪ ቀናት በውጭ መቆየት እንደሚኖርባት ተነግሯታል፡፡

እነሆ! የታህሳስ ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት ገብተዋል። በነዚህ አዲስ ቀናት አባት በራና አዲስ ለውጥን እየጠበቀ ነው። ለቀናት ከግቢው ውጭ ቤት ተከራይቶ ቆይቷል። አዲስ አበባ በጥየቃ የሀገሩን ልጆች አግኝቷል። እነሱ ግን በየአጋጣሚው የቤታቸውን መጥበብ እየነገሩት ነው። እሱም ቢሆን ታማሚ ልጁን ይዞ በእነሱ ላይ መደረብን አይሻም። ከአቅሙ በላይ ቢሆንም ለልጁ የሚያመቸውን አንዲት ክፍል ቤት ተከራይቶ ውሎ አደረ። የዕለት ወጪና መድሀኒቶች ኪሱን አሳስተው አቅሙን ይፈትኑት ያዙ፡፡

አንድ ቀን በድንገት ለጆሮው የደረሰው የስልክ ጥሪ ግን ምርትዓለምን ወደ ሆስፒታሉ እንዲያመጣት የሚያበስር ሆነ። አባት ለአንድ ወር ብሎ የከፈለው የቤት ኪራይ ከስድሰት ቀን በላይ አልኖረበትም። በቤቱ ጥቂት ቀናትን ብቻ አሳልፎ ወደ ሆስፒታሉ ሊመለስ ግድ ሆነ፡፡

አሁን ላይ አባት በራና በቂ ገንዘብ ያስፈልገዋል። እንዲያም ሆኖ ከአከራዮቹ የማይኖርበትን ቀሪ ክፍያ ‹‹መልሱልኝ›› ሲል አልጠየቀም። እነሱም ችግሩን አይተው ‹‹እንመልስልህ›› ብለው አላግደረዱትም። እሱ ግን ዓይኑን አላሸም። ‹‹ማቄን ጨርቄን ሳይል ገንዘቡን ትቶላቸው ወደ ሆስፒታሉ ገሰገሰ፡፡

የአንዷ ኩላሊት ነገር …

አባት ሥፍራው ሲደርስ ለልጁ ጠፍቶ የከረመው አልጋ በወጉ ተዘጋጅቶ ጠበቀው። በስቃይ የምትንገላታውን ትንሽዬ ልጅ አቅፎ ከመኝታው ላይ አሳረፋት። ምርትዓለም እስከዛሬ በሽንቷ ቀላቅሎ የሚወጣው ደም አሁን ተለውጦ ሙሉ ለሙሉ ወደ ንጹህ ደም ተቀይሯል። ይህ አይነቱ ምልክት ደግሞ ሀኪሞችን ወደ ውሳኔ እንዲፈጥኑ አጣደፋቸው፡፡

ሀኪሞች በልጅቷ ላይ ያስተዋሉት ለውጥ ቀናትን አላሻገራቸውም። አስፈላጊውን ሁሉ አድርገው ቀዶ ሕክምናውን አካሄዱ። አሁን ለትንሽዋ ልጅ ሲጠበቅ የነበረው ሕክምና ተከናውኗል። ይህ ሕክምና በውጤቱ የቀኝ ኩላሊቷን በማስወገድ ተልዕኮውን አጠናቋል፡፡

የታህሳስ 2017 ዓ.ም ቆይታ ለምርት ዓለም በብዙ መልኮች ተገለጠ። ሕመሟ በትክክል የኩላሊት ላይ ዕጢ በመሆኑ ካንሰር መሆኑን ተረጋግጧል። የተሰራላት ቀዶ ሕክምናም ለአንዲት የአስራ አንድ ዓመት ልጅ እንደዋዛ የሚታይ አይደለም። እንዲያም ሆኖ አባትና ልጅ የመጣውን ሁሉ በጥንካሬ በመወጣት ተጋፍጠውታል። እሷ አይቻል ይመስለውን ሕመሟን ችላ፣ እሱም የአባትነት መንፈሱን ተቆጣጥሮ የነገዋን ጀንበር ለማየት በቅተዋል፡፡

የሕጻኗ ሕክምና ገና አልተቋጨም። አሁንም ውስጥን በሚፈትኑ የስቃይ መንገዶች ለማለፍ መዘጋጀት የግድ ይላታል። ጠንካራዋ ብላቴና ለዚህ እጅ አልሰጠችም። የታዘዘላትን የኬሞ ቴራፒ ሕክምና ለመውሰድ በፅኑ ብርትታ ተገኘች። ምርትዓለም በርካታው የካንሰር ታማሚ የሚወስደውን የኬሞ ሕክምና በአግባቡ እየወሰደች ነው፡፡

ልጅቷ እስካሁንም ለአስር ግዚያት የኬሞ ሕከምና ተሰጥቷታል። ሕክምናው በባህርይው ብዙ ለውጦችን ያስከትላል። ምግብ መከልከል፣ ማስመለስ፣ ሀይለኛ ትኩሳት ማስከተልና ሙሉ ለሙሉ ጸጉርን መምለጥ ጭምር ምልክቶቹ ናቸው። አባት ከታሸጉ ምግቦች በመራቅ ተፈጥሯዊ ፍራፍሬዎችን ለልጁ በመስጠት ትንፋሽዋን አቆይቷል፡፡

ስለነገ ምን…

አባት ከዚህ ቀድሞ ስለልጁ ነገ ሀኪሞችን ጠይቋል። ሁሉም የሰጡት ምላሽ ብሩህ ተስፋን የሚያጭር ነበር። ልጁ በአግባቡ ሕክምናውን ከጨረሰች በቀዶ ሕክምናው ተቆርጦ የወጣው የካንሰር ሴል መልሶ አይተካም። ይህ ቃል ለአባት በረና ልዩ ጽናት ሆኖ ወደ ልጁ ተጋብቷል። አሁን ምርትዓለም ካንሰሩ ወደሌላው አካሏ እንዳይሰራጭ ተገቢውን ሕክምና እየወሰደች ነው፡፡

አባወራው ስለእሷ መኖር ቤት ትዳሩን፣ ሥራና እንጀራውን ትቷል። ለውድ ልጁ ሙሉ ግዜውን መስጠቱ ለአንዲትም ቀን የስሜት ጎዶሎ አላቀበለውም። ታህሳስ ላይ ሀገሩን የለቀቀ አሁንም ድረስ መገኛው አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሆኗል።

አባትና ልጅን በእንግድነት…

አባትና ልጅን ያገኘኋቸው በማቲዎስ ወንዱ ኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ውስጥ እንደ ቤተሰብ ሆነው ነው። በዚህ አፀድ እነሱን ጨምሮ በርካታ ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሕጻናትና ወላጆችቸው ያሻቸውን ግዜ መኖርና መታከም ይችላሉ፡፡

ይህን ሰፊ ዕድል በሰፊው ያበረከተው ይህ ማዕከል የነዚህን ቤተሰቦች ቁስል ለመረዳት ነጋሪ አስፈልጎት አያውቅም። የሁሉም እውነታ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆኖ ከእሱ ማንነት ጋር ዓመታትን ተሻግሯል። በራናና ልጁ ዛሬ የት ልኑር፣ ምን ልብላ ይሉት ጥያቄ አያስጨንቃቸውም። ጥያቂያቸውን ፈጥኖ የሚመልሰው ይህ ማዕከል ሁሌም ከአጠገባቸው ቆሞ ከጎናቸው ይራመዳል፡፡

አሁን ምርት ዓለም በማዕከሉ ወራትን አስቆጥራለች። ሕክምና በኖራት ግዜ ሆስፒታል አድርሶ አሳክሞ የሚመልሳት ወገን አላጣችም። የሚያስፈልጋት መድሀኒት በሙሉ በሶሳይቲው አባላት ሰፊ እጆች ሁሌም እየተበረከተላት ይገኛል፡፡

ይህ እውነት ትናንትን በተስፋ መቁረጥ ላለፉት ሁሉ አጋር መከታ ሆኖ አብሯቸው ይቀጥላል። እነበራናም ስለዚህ ሀቅ የወደፊቱን መልካምነት እያሰቡ ዛሬን በእፎይታ ማደር ይዘዋል፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You