
የብዕር ትሩፋቴን የሚያነቃቁ አንባቢዎቼን፤ ጽሑፌን የሚጠብቁ አለቆቼን በምናቤ እያሰብኩ ሃሳብ ሳምጥ፤ በብዕር ወረቀት ማረስ ቁምነገርነቱ ተሰውሮብኝ በመጠበብ ላይ እንዳለሁ ስልኬ አቃጨለ። የሜትር ታክሲ ሹፌሩ ወዳጄ ይርጋ የኋላው ነው። “ለጋዜጣ የሚሆንህ ማለፊያ ወግ ይዣለሁና በቀትር የገበታ ሰዓት እንገናኝ” ሲል ቀጠሮ አሲያዘኝ። በሰጠኝ አድራሻ እየተመራሁ ከተባባልነው ሥፍራ ስደርስ የማይሰስቱ እጆች ፍቅር፣ ያልነጠፉ ልቦች ጠብ እርግፍ ብለው አስተናገዱኝ። ይህስ እንደምን ያለ ትህትና ነው ከራስ በላይ ሰውን መውደድ? ስለሰው ዋጋ የከፈሉ ሸካራ መዳፎች፣ ትናንትን በጽናት ያለፉ፣ ዛሬን ለመኖር የሚኳትኑና ነገን ሩቅ አሻግረው የሚመለከቱ ብርሃን ፈንጣቂ አይኖች በተስፋ ተሞልተው ላስተዋላቸው ብርታትን ያጎናጽፋሉ፤ እኔም ባየሁት ነገር ተደንቄ ጉድ ትንግርት አልኩ በልቤ።በዚህም ሳላበቃ ይህን ከተብኩ ለአንባቢዎቼ።
የዛሬዋ ባለታሪክ እንግዳዬ ጣይቱ ጉዲሳ ገና በጨቅላነት የማለዳ እድሜዋ እናትና አባቷን በሞት ስለተነጠቀች ወንድ አያቷ ጉዲሳ ጎበና እና ሴት አያቷ ቀነኔ ፈይሳ ጋር አደገች። ከዚህም የተነሳ የምትጠራው በወላጆቿ ሳይሆን በአያቶቿ እንደሆነ አጫወተችኝ። የዕድሜን ጉዳይ ባነሳሁ ጊዜ ፊደል አልቆጠረች ቀለም አልወጋችምና “ቁጥሩን አላውቀውም፤ ብቻ የወሎ ርሃብ ጊዜ ነው የተወለድሽው ሲሉ ነግረውኛል” በማለት ስትነግረኝ ሁኔታዋን አይቼ መላ ምቴን ሳስቀምጥ ዓመተ ምህረቱ 1977 ላይ አረፈ።
በአያት እጅ ያደገ ልጅ ቅምጥል ነው ይባላል፤ ያንቺስ አስተዳደግ ምን ይመስላል? የሚለውን ጥያቄ የቆይታችን አቦል አደረኩት። ልጅነቷን የከብት ጭራ በመከተል የፈጀችው ጣይቱ እኩዮቿ ደብተር ይዘው ትምህርት ቤት ሲመላለሱ ስታይ ለመማር ያላት ፍላጎት በቁጭትና በዕልህ አገርሽቶ እንዲያስገቧት አያቶቿን ጠየቀቻቸው። እነሱ ግን አካሏ ሳይጠና ሃሳቧ ሳይሰላ ለማታውቀው ሰው በ15 አመቷ ለትዳር ዳረጓት። ይህም ሞራሏን ሰብሮ የኔ የምትለው ሁነኛ ተቆርቋሪ ዘመድ እንደሌላት ቆጥራ ባይተዋርነቷን አምና ተቀበለች። በዚህም ምክንያት ይመስላል ውሃ አጣጯ ሽፈራው አለሙ “ከእጅሽና ከግርሽ በቀር ምን ይዘሽ የመጣሽ መሰለሽ? ስንዝር መሬት ይሁን ኮሳሳ ጥጃ እንኳን መቀባበያ ማጫ አልሰጡሽም፤ ስለዚህ ስታኮርፊ መሸሸጊያ በከፋሽ ቀን መጠጊያ ዘመድ እንዳለው ሰው ሁሉ አፍሽን ሞልተሽ እኔ ጋር ለመሟገት አልታደልሽም። ድምጽሽን አጥፍተሽ አመልሽን አሳምረሽ ለመኖር ሞክሪ” እያለ ልቧን ሲያደማው ለመለያየት ብትሻም
“ኧረ ልጅ ማሰሪያው ኧረ ልጅ ገመዱ፣
ጎጆማ ምን ይላል ትተውት ቢሄዱ።”
የሚለው ሀገርኛ ተረት ደረሰባትና ጨዋታ ሳትጠግብ ቀልቧን ሳትሰበስብ የሦስት ልጆች እናት ሆነች፤ ባል ተብዬውም አማራጭ አልባ አድርጓት በልጆች ሰበብ ቀይዶ ያስቀመጣት መስሎት በአልኮል ናውዞ ሰክሮ በመጣ ቁጥር “አንቺ ወፍ ዘራሽ፤ መድረሻ ቢስ” እያለ የዱላ ውርጅብኝ ያዘንብባታል። እሷም ወላጆቿ ከሥሯ ሲጠፉ ያጣችውን ሙላት የራቃትን እምነት ታውቃለችና ያባት ፍቅር ሲጎድል የልጆቿ ሰብዕና እንዳይጎድፍ በመስጋት አቅም ከድቷት በራስ መተማመኗ ተሸርሽሮባት ጥርሷን ነክሳ ያፈገፈገ ጉልቻዋን ሰበሰበችው። የዘመመ ምሰሶዋን ደገፈችው። ይሁን እንጂ ጣይቱ ያሰበችው ቀርቶ ከባለቤቷ ጋር እህል ውሃቸው አለቀና ልጅነቷን በትና፣ ወዟን አንጠፍጥፋ፣ ደምና ላብ ገብራ ካቆመችው ጎጆ ስንጥር ሳትመዝ እፍኝ ጥሬ ሳትይዝ ውልቅ አለች።
ሰኔና ሰኞ ተገጣጠሙና የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ሞሰቧን ሲርበው “ቁራጭ የስጋ ዝምድና የመርፌ ያህል ትወጋ” ነውና እንጥፍጣፊ ተስፋ ይዛ እንዲያቆይዋት ስትጠይቃቸው “አረብ ሀገር ልትሄድ አይደል? እንኳን ለልጆቿ ለኛም ትተርፈናለች” ብለው በመመኘት እሽታቸውን ሰጧት። በለስ እንዲቀናት ፈጣሪዋን ተማጽና ከኩዌት ምድር ጥርኝ አፈር ዘገነች፤ ዳሩ ምን ይሆናል።
“ጎንደር አባ ጃሌው ከግንቡ ደርሼ፣
ያለ እድል አይሆንም መጣሁ ተመልሼ።”
የሚለው ሆድ በርባሪ የስንኝ ቋጠሮ ብሶት አዝሎ ሃዘኗን ቢያገዝፈውም የምትደረድረውን የክራሩን ጅማት ዜማ አላብሳ ለልቦናዋ ተስፋን በመመገብ የስደትን ኑሮ ተጋፈጠችው።
እድሏም ቀናና ፈርሃ እግዚአብሄር ያደረባቸው ሰብአዊነት የሚሰማቸው መልካም አሰሪዎች አጋጠሟት፤ “ሰው ለሰው ልብሱ ነው” የሚለውን ብሂል እያወደሰች ከምትልከው ገንዘብ ጋር በእናትነት ፍቅር የልጆቿን ጉንጭ በሥሥት ትዳብስ ጀመር። እንዲህ ያለው ሁኔታ ግን መዝለቅ የቻለው ለስምንት ወራት ብቻ ነው። የሀገሪቱ መንግሥት ኢትዮጵያውያን እንዲወጡ አዘዘና ጣይቱም ከሞቀ ያሠሪዎቿ ቤት ከተሻለው ክፍያ ለመነጣጠል በቃች። “ጠማማ እድሏ በምትሄድበት ሁሉ ቀድሞ እየደረሰ የተፋነው ምራቅ ሳይደርቅ ይኸው ተመለሰች” እያለ ቀዬው ሲዘባበትባት ስሜቷ ክፉኛ ተጎዳ። ይህን የተመለከተች ወዳጇ ሌላ ባህር ማዱ ጉዞ አሰናዳችላትና መልሳ የባህሬንን አየር ማገች። የሰው ፊት እየፈጃት የባይተዋርነት ወላፈኑ እየገረፋት በምትልከው ብር ከልጆቿ የዕለት ጉርስ አልፎ ቦታ እንዲገዙላት አስባ ነበር፤ ሆኖም ዘመዶቿ ያሰበችውን አላቆዩዋትም።
“እስከዛሬ ድረስ የሰው ውሃ ጠጣሁ፣
ከንግዲህ ሀገሬ ተቀበይኝ መጣሁ።”
ብላ ከስምንት የስደት ዓመታት በኋላ ሰበታን ተሻግሮ የሚገኘውን ናኖ ቀሬሳ ዞን ወልመራ ወረዳ ሱባ መንደርን ጫማዋ ሲስም ጥሩ የልጅነት ዘመን ያልከተበችበት የትዝታ ማህደሯ ጎረበጣትና እሷን ያጋጠማት ያለ እድሜ ጋብቻ ለልጆቿም እንዳይተርፍ ጓዟን ጠቅልላ አዲስ አበባ ከተመች። ኑሮን እሽሩሩ ብትለው ከተሜነት የከፋ ችግር እንጂ መልካም ገድ አልቸራትም። ሉላዊነቱ አይሎ እኩል መራመድ አቅቷት እድሏን እየረገመች ለምን እንዳላስተማሯት ስትጠይቅ የአለማየሁ እሸቴ “ተማር ልጄ” ዘፈን ፋሽን ቢሆንም የአጼ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ወድቆ የደርግ ሥርዓት ኮርቻውን ሲቆናጠጥ “ተማር ልጄ” የሚለው
“ዝረፍ ልጄ ዝረፍ ልጄ፣
መማር መመራመር ለማንም አልበጀ፣
ይኸው በዚያ ሰሞን ስልሳ ሰው አስፈጀ።”
በሚል ተተካና መማር እንደጥፋት ተቆጠረ፤ በዚህም ምክንያት እንዳላስተማሯት አያቶቿ ነገሯት። ጣይቱ ግን “ሆድ ይፍጀው” ከማለት ሌላ ቃል አልወጣትም። “ተከድኖ ይብሰል እንጂ በስደት ላይ እያለሁ አለመማሬ ከቴክኖሎጂ አሽሽቶ ሥራዬን እንዳላሳልጥ እንቅፋት ቢሆንብኝም ጥሩ አሠሪዎች ናቸውና የገጠሙኝ አንዲት አረብኛ ቃል ሳላውቅ በአካላዊ ቋንቋ ነው የቆይታ ጊዜዬን ፉት ያልኩት” ስትል ውሃ ተራጭታ ጭቃ አቡክታ ካደገችበት ቀዬ ወጥታ የአዲስ አበባው ትርምስ ሲውጣት መልመድ ቸግሯት በነበረበት ወቅት ያጋጠማትንና ሞት ያስመኛትን ክስተት አስከትላ አጫወተችኝ።
የንግድ ተቋማት በተዘጉበት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አካላት በቆሙበት፣ ሰው ከሰው እንዳይገናኝ በሩን በዘጋበት በዚያን በኮሮና ወቅት አዲስ አበባ ለጣይቱ “ኖር ዝለቂ” ያለቻትን ያህል ሙሉ የእንባ ጽዋ በቀር አላቆየቻትም። ምሬትን ስትጋት አጎቷ አንገት ማስገቢያ እንዲሆናት ለሽያጭ በቋፍ ላይ የሚገኘውን ትርፍ የኮንዶሚኒዬም ቤታቸውን እስከጊዜው ድረስ ለማረፊያነት ሰጧትና እንደወተት ከሚንጣት ሃሳብ ገላገሏት። “አንድ ነገር ቋሚ ንብረት አበጅተው ያቆዩኛል” ያለቻቸው ዘመዶቿ እንደጠላት ገንዘብ በትነውት ጸጸት ነውና ያቆዩዋት የልጆቿን ጉሮሮ ለመድፈን ተስፋ ሳትቆርጥ በቀራት ጥቂት ሳንቲም ምን ሥራ እንደምትጀምር ጠፍቷት ጭንቀት ሲገባት አጎቷ ደረቅ እንጀራ መሸጥን አመላከቷትና መቀነቷን አጠበቀች።
ጤፍ ልትገዛ ገበያ ገባችና ዋጋ አውቃ ገንዘብ ልታወጣ ባንክ ቤት ስታቀና ከቦርሳዋ የወሸቀችው የኤቲኤም ካርዷ የለም፤ ለካስ እንግዳ መሆኗን ልብ ያለ አንድ ባለመኪና ቀማኛ መንትፏት ኖሯል። ነገሩ እንዲህ ነው።
ባደገችበት ወግና ባህል ሽማግሌ የተጣላን ዋሽቶ የሚያስታርቅ ድሮና ኩሎ ለወግ ማዕረግ የሚያበቃ ነው። ሽበት የወረሰው ሰው ይሰርቀኛል ብላ እንዴት ልታስብ ትችላለች? ታክሲ ስትጠብቅ “ግቢ ልሸኝሽ የኔ እመቤት” አለ ሲጢጥ አድርጎ መኪናውን ካጠገቧ እያቆመ። እድሜውን በፊቱ መዝና ተንኮል አይኖረውም ብላ በማሰብ “ምን አለበት?” አለችና በመዝለቅ የጋቢናውን በር መልሳ ቀበቶ አጠለቀችና ከጎኑ ተደላድላ ተቀመጠች። ድንቢጧን መኪና እንደአገው ፈረስ ሲያሰግራት መሪው ላይ የከመረው ሰላሳ ሺህ ብር እግሯ ስር ሲጎዘጎዝ ልትሰበስብለት ባቀረቀረችበት አጋጣሚ ካጠገቡ ያስቀመጠችውን ቦርሳዋን ቢከፍተው ኤቲኤም አገኘና ከኪሱ ጨመረው። ጣይቱ ግን በየዋህ ልብ ሀገር አማን ብላ ከምትፈልገው ቦታ ስትደርስ አመስግና ወረደች። ታዲያ ይህን ሁሉ ጉድ ያወቀችው ከሦስት ቀናት በኋላ ጤፍ ገዝታ ልትከፍል ስትል ነው። የሥራ መጀመሪያ እርሾዋን አለኝ ያለችውን ጥሪቷን ሲሰርቃት ጠንካራና ብርቱ ሞራሏን እንዲሁም በተስፋ ጽናት ያቆመችውን ህሊናዋንም ጭምር ነበር የወሰደባት። እህል እህል የሚሉና ለሥራ ያልደረሱ ልጆችን ይዛ በባዳ መሃል ደረቷን እየደቃች “ሰው ነው የራበኝ” እያለች ስታነባ ሃዘኑን መቋቋም አቅቷት ጉልበቷ ከዳትና መሬት ያዘች። ሌባው ብሩን ወጪ ሲያደርገው የደረሳትን የጽሁፍ መልክዕት ያላየችው ማንበብና መጻፍ ስለማትችል እንደሆነ በነገረቻቸው ጊዜ የባንክ ሠራተኞች በሁኔታዋ አንጀታቸው እጅጉን ተላውሶ ከጉድለታቸው ቀነሱና መጽናኛ እንዲሆናት እጃቸውን ዘረጉላት። ሆድ እያለ ክንድን ተንተርሶ ለመተኛት አያስችልምና በተረጠበችው ገንዘብ እጇን ፈትታ ያሰበችው ደረቅ እንጀራ መሸጡ ተጀመረ። በቀን ሦስት መቶ እንጀራ የሚረከባት ሰው ለሥራ የፈጠራት ሌት ከቀን የማይደክማት ታታሪ ሴት መሆኗን አጫወተኝ። በእንዲህ መልኩ የጦፈው ገቢዋ ድንገት በተነሳ የእሳት አደጋ ሕይወቷን ዳግም የችግር አረንቋ ውስጥ ከተተው። ይህ አልበቃ ብሎ አጎቷ ፍቅረሰላም ቤቱን ሸጡትና አስወጧት። ራሷን ለማጥፋት ገመድና የመርዝ እንክብሎች አስቀምጣ ስታስበው ልጆቿ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ቢያጧት የሚሆኑትን እያሰበች እንባዋን ወደሰማይ ረጨች፤ ጸሎቷም መና አልቀረም። ፈጣሪ ሰምቶ የሰው መውደድ ሰጣትና የሰፈሩ ነዋሪ ከወረዳው መሥሪያ ኮንቲነር እንድታገኝ ካደረጉ በኋላ ስሜ አይጠቀስ ያሉትን ባለጸጋ አናግረው ባገኙት ድጋፍ መሥሪያ ቦታውን ከማደላደል ባሻገር ወረት ተረፋትና ከሻይ ቡና ጋር ቆሎ እየሸጠች ለቀዬው ሰው ወድቆ የመነሳት ምሳሌ ሆነች። ቃለመጠይቁን ያመቻቸልኝ ወዳጄ ይርጋ የኋላው ከራሷ ሦስት ልጆች አልፋ የተጣሉ ሁለት ልጆችን ከመንገድ አንስታ እያሳደገች እንደሆነ ሲነግረኝ ሀገሬን ፈጣሪ ያለደግ ሰው እንደማይተዋት አምኜ ተጽናናሁ። ለትንሽ ትልቁም የማይለወጠው አንደበቷ ፍቅርን ዘርቶ ቤቷ ለብዙዎች የናት ጓዳ ሆኖ ፈተናቸውን አሻግሯል፤ ይህም ምልክትነቷን አጽንቶ የተናገረችው ይደመጣል የሠራችው ይወደዳል። ምስለ ጣይቱ የዛሬ እንግዳዬ ስትቸገር መላ በመፍጠር ስትናደድ ቶሎ በመብረድ እልፍ የሕይወት ሰንኮፏን አራግፋ አዲስ ማንነት ለብሳለችና ከታሪኳ ተምራችሁ ራሳችሁን ሁኑ በማለት ጽሑፌን ቋጨሁ።
ሃብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም