የውሃ አካላትን ከተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለመታደግ በቅንጅት መሥራት ይገባል

አዳማ፡- የውሃ አካላትን ከተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለመታደግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመተባበር የቆቃ ሀይቅ ተጠቃሚዎችንና ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በሀይቁ ላይ የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ የንቅናቄ መርሀ ግብር አስጀምሯል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ ተወካይ አቶ ማሙሻ ኃይሉ እንደገለጹት፤ ትልልቅ ሃይቆችና ወንዞች በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለጉዳት እየተዳረጉ በመሆኑ በቅንጅት በመስራት ከጉዳት መታደግ ይገባል።

በውሃ አካላት ላይ የሚከሰቱ መጤ አረሞችንና የሚለቀቁ ኬሚካሎችን ምንነት ማወቅ ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ የውሃ ብክነትንና ብክለትን ለማስቀረት የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በውሃ አካላት ደህንነትና በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በኃይል ማመንጨትና መጠቀም እንዲሁም በመጠጥ ውሃና በሳኒቴሽን ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አመልክተው፤ ውሃን ከብክነትና ከብክለት ለመታደግ በቆቃ ግድብ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ የህዝብ ንቅናቄ መርሀ ግብር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ጀምረናል ብለዋል።

መርሀ ግብሩ ግድቡ ላይ የተስፋፋውን የእንቦጭ አረም በማስወገድ ሀይቁ የሚሰጠውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግልጋሎቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል ያለመ መሆኑ አስታውቀዋል።
የቆቃ ግድብ ለመጠጥ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለኃይል ማመንጫ እያገለገለ ያለ ሀይቅ በመሆኑ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ ጠቁመው፤ በጽዳት ዘመቻው ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ምሁራን አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን በቀለ (ኢ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የኦሮሚያ ክልል ውሃ ቢሮ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ዋነኛው የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃን መንከባከብና መጠበቅ በመሆኑ በቆቃ ግድብ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው።

ከዚህ በፊት የአካባቢውን ማህበረሰብና ባለሀብቶችን በማሳተፍ በደንበል ሀይቅ የእንቦጭ አረም የማስወገድ ተግባር ውጤታማ መሆኑን ገልጸው፤ ከቆቃ ሀይቅ ላይም እንቦጭን ለማስወገድ የአካባቢው አልሚዎች የተዘጋጀውን ካርታ ተረክበው ሀይቁን በማፅዳት የውሃ ብክነትንና ብክለትን እንዲታደጉ አሳስበዋል።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፣ በ2014 እና በ2015 ዓ.ም በደምበል ሀይቅ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች በማሳተፍ 250 ሄክታር ማጽዳት ተችሏል።ይህም ወደ ገንዘብ ሲቀየር 15 ሚሊዮን ብር ያወጣል።

ከደምበል ሀይቅ በተወሰደው ተሞክሮ መሰረት በዘንድሮው ዓመት ደግሞ በቆቃ ግድብ 74 ሄክታር መሬትን ከእንቦጭ አረም ለማጽዳት ለ18 ባለድርሻ አካላት ካርታ መሰጠቱን አስታውቀዋል።

የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ የተዘጋጀውን ካርታ የርክክብ ሥነ-ሥርዓት እየተከናወነ ሲሆን፤ ካርታው የባለቤትነት ሳይሆን እንቦጩን ለማስወገድ፣ ክትትል ለማድረግና ሀይቁን በሕጋዊነት መጠቀም እንዲችሉ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You